43 ሺሕ ‹‹ፓንዳ ፓክ›› ተለግሷል
የቻይና ሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸውና መንግሥት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን ድህነት ለመቅረፍ እንደሚሠሩና ለዚህም መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂን አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተማሪዎች ምገባ፣ በንፁህ መጠጥ ውኃና በሴቶች አቅም ግንባታ ዙሪያ ሲሠራ የነበረው ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨሪቲ አሊቬሽን (ሲኤፍፒኤ)፣ ከነሐሴ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ የራሱን ቢሮ መክፈቱን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት አምባሳደር ጂን፣ ቻይና ውጤታማ ከሆነችባቸው ሥራዎች ዋነኛው ድህነትን መቅረፍ መቻሏ መሆኑን አመልክተው፣ ሲኤፍፒኤ በኢትዮጵያ ቢሮ መክፈቱም፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ድህነትን ለመቅረፍ አጋር ሆና በቅርበት እንድትሠራ ያስችላታል ብለዋል፡፡ በቻይና ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመሥራት ዕድል እንደሚያገኙም አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ በተማሪዎች ምገባ ላይ ሲሠራ ከቆየው የእናት ወግ ማኅበር ጋር በመተባበር ሲሠራ የቆየውና እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተመረጡ አካባቢዎች የማኅበረሰብ ሥራውን ያከናወነው ሲኤፍፒኤ፣ ባሉት ፕሮጀክቶች 27 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የሲኤፍፒኤ ምክትል ፕሬዚዳንት ዋንግ ዢንዙ እንዳሉት፣ እ.ኤ.አ. በ1989 በቻይና የተመሠረተው ሲኤፍፒኤ፣ በቻይና ድህነትን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
ከቻይና የተገኘውን ልምድ በመያዝም በትምህርት፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪና ለአደጋ ምላሽ በመስጠት በኩል በሃያ አገሮች ውስጥ እየሠራ መሆኑን አስታውሰው፣ እስካሁንም ከ450 ሺሕ ሰዎች በላይ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ በሜይንማር፣ በኔፓል፣ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በኡጋንዳና በካምቦዲያ እየሠራ ሲገኝ፣ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ ከሌሎች ጋር በመተባበር ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከወር በፊት ደግሞ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ የራሱን ቢሮ መክፈቱን፣ ይህም በኢትዮጵያ በድህነት የተጠቁ ቦታዎችን ለመድረስ የሚሠሩትን ሥራ ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ ከዘላቂ ልማት ግቦች፣ ግብ ሁለት ዜሮ ረሃብ፣ ግብ አራት ጥራት ያለው ትምህርት፣ ግብ ስድስት ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የግልና አካባቢ ንፅህና፣ ግብ ስምንት ሥራና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም ግብ አምስት በፆታ እኩልነት ዙሪያ በኢትዮጵያ እየሠራ ይገኛል፡፡
ከአገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጀቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የተገበረው ፋውንዴሽኑ፣ እ.ኤ.አ. 2015 እስከ ነሐሴ 2019 ባለው ጊዜ 73 ሚሊዮን ብር በማውጣት 27 ሺሕ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አክለዋል፡፡
በተማሪዎች ምገባ በኩል፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሲንቀሳቀስ ከቆየው አዲስ ወግ ማኅበር ጋር እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ በ43 የመንግሥት ትምህርት ቤት የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎችን ምገባ ፕሮግራም ደግፏል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2018 ከዓለም አቀፉ ሪስኪዩ ኮሚቴ ጋር በመተባበር በጅግጅጋ ስደተኞች ካምፕ ለሚገኙ 2,352 ስደተኛ ሕፃናት በትምህርት ቀናት በቀን አንዴ እንዲመገቡ ማድረጉንም ሚስተር ዢንዙ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በ2012 ዓ.ም. በቀን ሁለቴ ለመመገብ ማቀዱን እንደ መልካም ጅምር የጠቀሱት ሚስተር ዥንዙ፣ ፋውንዴሽኑ ከእናት ወግ ማኅበር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ሲሠራ የቆየውን ፕሮጀክት ችግሩ ወዳለባቸው ክልሎች ወስዶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ከተማሪዎች ምገባ ባለፈ የውኃ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች የዝናብ ውኃ በማጠራቀም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል 80 የውኃ ማከማቻ ገንዳዎች መገንባታቸውን፣ ይህም በየአካባቢዎቹ የነበረውን የውኃ ችግር በአንፃራዊነት መቅረፍ እንዳስቻለ አክለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2019 ተጨማሪ 40 የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን፣ በዚህም ከአማራ ክልል የተመረጡ አካባቢዎችና ዝዋይ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ንፁህ ውኃ አቅርቦትን ለማጠናከር፣ የእጅ መታጠቢያ፣ የውኃ መጠጫና ውኃ ማጠራቀሚያ ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባ ‹‹ስፕላሽ ኢንተርናሽናል›› ከተባለ ድርጅት ጋር በ2019 ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ ለሁለት ዓመት በሚቆየው የትምህርት ቤት ዋሽ ፕሮጀክትም፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ 40 ትምህርት ቤቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የሴቶችን ኢኮኖሚ በማጎልበት ዙሪያ በአክሱምና ላሊባላ ለሚገኙ 100 ሴቶች በሽመና፣ ሸክላ ሥራና የድንጋይ ቅርፅ ማውጣት ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱን፣ በቀጣይ ከዩኤን ውሜን ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ሴቶች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተስማሚ የሆነ ግብርናን ለማስተዋወቅ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
በሚሠራባቸው 20 አገሮች፣ ‹‹ፓንዳ ፓክ›› ማለትም ሥዕል ደብተርንና ከለርን ጨምሮ የተሟላ የጽሕፈት መሣሪያ የያዘ ኮምፓስ፣ ማስታወሻ መያዣና አሻንጉሊት የያዘ የተማሪዎች ቦርሳ ስጦታ በመስጠት የሚሠራው ፋውንዴሽኑ፣ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቢሮ መክፈቱን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ፣ 43 ሺሕ ‹‹ፓንዳ ፓክ›› ቦርሳዎችን አስረክቧል፡፡
ቦርሳዎቹም በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ለተመረጡ ተማሪዎች የሚታደል ይሆናል፡፡ በርክክቡም ከቀዳማዊት እመቤት ቢሮ አቶ ሙሉቀን ፈንታን ጨምሮ ከትምህርት ቢሮና ከሲኤፍፒኤ ቻይናና አዲስ አበባ ቢሮ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡