ሰላም! ሰላም! እኔም ወግ ይድረሰኝ ብዬ በበዓሉ ሰሞን ሙክት በግ አርጄ ቤቴ የሠርግ አዳራሽ መስሎ ሰነበተ። ለአንድ ለሁለት ቀንም ቢሆን ‘ሰለብሪቲ’ ሆንኩ። ስንት ዓመት ተሸውጄ ኖሯል እያልኩ በውስጤ ጎረቤቶቼን ‘ብሉ… ጠጡ…’ ስል እኔ አንድ ጎድን ሳይደርሰኝ ድስቱ ባዶ ሆነ። ተመስገን ነው ለነገሩ። ዋናው ኪስ ነው። ዳሩ ቻይና ቦርቀቅ ቦርቀቅ ያለ ኪስ እየሰፋችልን የዘንድሮ ኪስ ቶሎ አይሞላም። ‘ከቻይና ሱሪ ነው ከእኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ችግሩ?’ ብዬ እንዳልጠይቅ ማንን አምኜ። ዘንድሮ እንኳን ‘ሲሪየስ’ ነገር የታመመ ለመጠየቅም መታወቂያ እያዩ ሆኗል አሉ። አያድርስ ነው። ባሻዬ፣ ‹‹ከመሸ መወለድ ትርፉ ይኼ ነው፤›› እያሉ ይቆዝማሉ። እሳቸው ደግሞ ሰሞኑን የስምንተኛው ሺሕን ነገር እንዲችው ሲያነሱ ሲጥሉ መዋል አብዝተዋል። ይኼን ዓይና ‘እውነትም ባሻዬ ሲመሽ ተወልደዋል’ እላለሁ። ምንማ ያደለው ሚሊዮንና ቢሊዮን ረብጣ ሲቆጥር፣ እሳቸው ስምንተኛው ሺሕ ላይ ‘ስታክ’ ማድረጋቸው ነዋ። እንዴት ነው ግን እንግሊዝኛዬ? መሻሻል ይታይብኛል አይደል? በተለይ ሰሞኑን ምን እንደታየኝ አላውቅም ‘ቮካብላሪ’ ጥናት ላይ በርትቻለሁ።
እንዲያው ሌላው ቢቀር ባሻዬን አንድ የውጭ አገር ጋዜጠኛ አግኝቷቸው፣ ‘እስኪ ስለስምንተኛው ሺሕ ያጫውቱን’ ብሎ መጠየቁ አይቀርምና ልዘጋጅ ብዬ እኮ ነው። መቼም ባሻዬ ከእኔ ወዲያ ምሁሩን ልጃቸውንም ቢሆን አምነው ለአስተርጓሚነት አይመርጡም። ትርጉምና አተረጓጎም ነዋ አገርን የበጠበጣት። ለነገሩ በአስተርጓሚም መናገራቸው እሳቸው ሆነው ነው። ይኼው አታዩም አስተርጓሚዎች ማን እንደ እኛ እያሉና ባልዋልንበት ዋሉ እያሉ ሲያስቁብን። ታዲያላችሁ ስለዘመኑ ጥቀርሻ፣ ስለዚህ በዘር ስለመቧደን፣ በጥቅም ስለመከፋፈል፣ በሃይማኖት ወገንተኝነት ስለመፋቀር (ወይ ፍቅር?) የምናገረውን በእንግሊዝኛ አጥንቼ ሳበቃ፣ ስምንተኛው ሺሕ ላይ ስደርስ በእንግሊዝኛ ምን እንደሚባል የሚነግረኝ ሰው ጠፋ። እናንተ ታውቁ ይሆን? ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝምʼ ሆነ እኮ!
ለእንቁጣጣሽ ማግሥት ባረድኩት አንድ ሙክት በግ ዝናዬ ከእትዬ ስርጉት እስከ ባሻዬ ቤት መናኘቱን አይቶ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹ይኼን ያህል ሰው የበግ አምሮት ካለው ለምንድነው በልማቱና በፈጣኑ ዕድገት ምክንያት የተፈጠሩ ፈጣን ልማታዊ ባለሀብቶች፣ መሬት እየተሰጣቸው በግ አርብተው በዓል ሲመጣ ለሰፊው ሕዝብ የማያድሉት?›› አለኝ። ዝም ብሎ ማደልና መታደል አለ እንዴ? ያውም በግ? ሆሆ። እስኪ አንዴ ʻበበግ ቤት በግ ገባʼ በሉማ። አይዟችሁ ግፋ ቢል አንድ ዓመት ቢፈጅባችሁ ነው። ሳልፈልግ የግዴን ዛሬ በበግ ዙሪያ ስላሉ ʻቲዎሪዎችʼ ላወራ ስለሆነ ያላረዳችሁ ምራቅ እየዋጣችሁ፣ ያረዳችሁ ግሳታችሁን ምንም ላላገሱት እያካፈላችሁ አዳምጡኝ። እኔ ምለው ግን ሰው እንዲህ በግ የማረድ ‹ሆቢ›ው ኃይለኛ ነው? ሆቢ ልበለው እንጂ። ድሮ ድሮ ሳስበው ደጉ ዘመን ደግ ሰው ብቻ ቀብሮ ያቃበረን ይመስለኝ ነበር። የምንፈራቸው፣ የምናዳምጣቸውና ምክራቸውን የምንሻው ሰዎችን ትዝታቸውን አሳቅፎን ያለፈብን ይመስለኝ ነበር። አሁን ሲገባኝ ለካ ፍየሎችን ከበጎች ጋር ቀላቅሎ ጭምር ነው።
ባሻዬ በዚህ አስተሳሰቤ የሚስማሙ አይመስልም። ‹‹ይኼ አስተሳሰብ…›› አሉኝ ለዘብ አድርገው ሲጀምሩ። ‹‹ . . . አንድም የትምክህት አንድም የድሮ ዘመን ናፋቂ ሰው አስተሳሰብ ይመስላል። ሁሉም ዘመን እንደ ልኩ እንደ ዑደቱ የሚታረዱ በጎች አሉት። በድሮና በዘንድሮ በጎችና አራጆች መሀል ያለው ልዩነት ምን መሰለህ አንበርብር? ድሮ በጎች የሕዝብ ናቸው። የአገር ናቸው። አገር ዜጋዋን በዋጋ ግዛኝ አትልም ነበር። ስለዚህ ከዓመት ዓመት በተቀመጥክበት፣ ሁለት ሦስት የእንጀራ ገመድ ሳይኖርህ በግ ቀርቶ በሬ ታርዳለህ። አሁን ግን የለውጥ ባቡር አለ። ባቡሩ ላይ ሳትሳፈር እንዲሁ በዋዛ የመስዋዕቱን በግ የሚያዘጋጅልህ ማንም የለም። የድሮ በግ ተውሰህ እንኳ ብታርደው እንደ ጌታው ነበር የሚቆጥርህ። ዘንድሮ እንደምታየው በካቦም አስረኸው ንቀቱ ንቀት አይደለም፤›› ሲሉኝ ሳቄ ትን ብሎኝ ልሞት ነበር። ላት በሰንሰለት ታስሮ አስቡት እስኪ ደጅ አላድርም ሲል። ኧረ ጌታቸውን የማይተማመኑ በጎች ብዛት የሕዝብ ቁጥራችንን በለጠው! በዚህ ላይ ሞገደኛ ፍየሎች ታክለውበታል!
ከባሻዬ ቅኔ ወደ እኔ የቀን ውሎ ስንሸጋገር ደግሞ ጭርታን እናገኛለን። ʻወደ ጭርታ ለምን ታሻግረናለህ? ቅኔው ላይ ጠበቅ አድርገህ አውጋንʼ የምትሉኝ ካላችሁ በውስጥ መስመር አነጋግሩኝ። ዘንድሮ እንኳን በውጭ ውስጥ ለውስጥም መስኮት ከፍተን ውጋቱን አልቻልነውም። ያልተናገርነውን ተናገሩ፣ ያላልነውን አሉ፣ ያልነውን አላሉም የሚሉን በዝተዋል። በጣም የማዝነው ሁሉም ስለሐሳብ ብዝኃነትና ልዩነት እያወራ ቆይቶ ሐሳባችሁ አልጥም ሲለው፣ ‹‹መቼ ነው የመለመሉሽ?›› ብሎ ያሽሟጥጣል። እውነቴን እኮ ነው። የባሻዬ ልጅ ሁሌም እንደሚያጫውተኝ ʻዴሞክራሲʼ የሚለው ቃል ምንጩ ከግሪክ ነው። ‹‹ከግሪክ ሥልጣኔ በፊት ደግሞ ኢትዮጲስ ጽሕፈት የጀመረች አገር ነች። በግሪክ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሐሳብ የተሸነፈው ቡድን አገር ውስጥ እንዲቀመጥ አይፈቀድለትም ነበር፤›› ሲለኝ ገርሞኝ አፌን ከፍቼ ነበር የማዳምጠው። ወይ ይሰደዳል ወይ ይወገራል!
አንዴ ይኼን ‘ፖዝ’ አድርጉና ቅኔ ቤት እንሂድ። እንዲህ የምንወዳትና የምንኮራባት አገራችን የቅኔ አድባር ናት። ቅኔ የብዙኃን፣ ቅቤ የጥቂቶች መሆኑንም ልብ በሉ። በቅኔ ቤት ደግሞ ሰላ ሰላ ያለ ሒስና ትችት እንኳን ሥጋ ለባሽ አማልዕክቱም አይቀርላቸውም። የስም አወጣጥና አወረራስ ላይ ካልሆነ በእኔ አስተያየት፣ በተለየት አብዮታዊ የመናገርና የማሰብ ባህል ከአቴና በፊት እዚህ እኛ አገር ቅኔ ቤቶች ነበረ ባይ ነኝ። ደላላ ብሆንም የተቻለኝን ያህል ታሪክ አጣራለሁ። አንዳንዶቻችን ለምን እንደሆነ አላውቅም በደረቁ ያለ ዜማ፣ ‘የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ’ ሲባል ቀዝቃዛ ነን። ሁልጊዜ ቁም ነገር በሆሆታ ተሞልቶ እንዴት ይዘለቃል? ታሪካዊት አገር ቅብጥርስ ምንትስ እያልን ገና ለገና መድረኩን በተቆጣጠሩት አፍ ልዩነት ተሰበከ’ ብለን ብስክስክ ስንል ግራ ይገባኛል። ወይ ባህር አልተሻገርን ወይ ታሪክ አላሻገርን መላው ጠፍቶ ቁጭ!
‹‹መጠላለፍ ሆኗል የእኔና አንቺ ነገር፣ ወይ አርፈን አልኖርነው ወይም አንሻገር፤›› ያለው ገበሬ መቼም የቻለውን ችሎ ነው። የእኔ ውድ ማንጠግቦሽ በቀደም፣ ‹‹ሥራ ላይ ቀዝቀዝ ብለህ ወሬ አብዝተሃል፤›› አለችኝ። ልክ መርጬ የማወራ ይመስል። አይገርማችሁም? እና ይህችም ቁም ነገር ሆና ተኮራረፍን። ከፍትፍቷ ፊቷ እያልኩ ደጅ እውላለሁ። ሥራው ቀዝቅዟል። መስከረም ቀዝቅዟል። በየካፌውና በየግሮሰሪው ወሬው ብቻ ደርቶ ያጋጥመኛል። ስለ ʻአሳይለምʼ ጠያቂው ብዛት፣ ስለፍትሕ ጠያቂው ብዛት፣ ስለመልካም አስተዳደር ጠያቂው ብዛት ሪፖርት ሳዳምጥ ተቀምጬ እቀራለሁ። የአገራችን ሰው ደግሞ እንደምታውቁት ባይጻፍለትም አንድ አባባል አምጥቷል። ‘ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም፣ በወሬም ጭምር እንጂ’ ማን ነበር ‘ከኩንታል ወሬ አንዲት ግራም ተግባር ትከብዳለች’ ያለው? ነገሩን ማለቴ ነው። ምን ይባል ታዲያ!
ይህን ብዬ ለብቻዬ ፈገግ ስል መገናኛ አካበቢ ቪላ ቤት የማጋዛው ደንበኛዬ ደወለ። የምንገናኝበትን ሥፍራ ወስነን ስልኩ ተዘጋ። ይኼ ደንበኛዬ የጥጥ እርሻ አለው። አዘውትሮ፣ ‹‹አገሬን በጥጥ ምርት ራሷን የቻለች ለማድረግ የበኩሌን እሠራለሁ፤›› ሲል ሰሚ ሰምቶ ይስቃል። በጎ ራዕይና ህልም እንደ ቅዠት በሚታይበት አገር አዳሜ ሳቁን ይጨርስና ‘መስሚያዬ ጥጥ ነው’ ብሎ ያልፈዋል። መስሚያቸው ጥጥ የሆኑ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰባቸው የመጡት ባሻዬ፣ ጆሯቸው ውስጥ ጥጥ መወተፍ አቁመው ሕመማቸውን ማዳመጥ መርጠው ተቀምጠዋል። የባሻዬ ፅናት ራሴን እንድፈትሽ ያደርገኝና ያሳፍረኛል። አንዳንዶች እንኳን በሽታቸውን ጤናቸውን፣ ሰላሙን፣ ብልጽግናውን ማዳመጥ ተስኖአቸዋል። መስሚያውን በጥጥ ደፍነው ተው ሲባሉ የሚብስባቸው፣ ያላሰቡትን ጀምረው ሰው ያላሰበውን የሚያሳስቡ፣ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩ ሰዎችና ጆሮዎች በበኩሌ ለመቁጠር ታክቶኛል። ʻአውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማምʼ የሚሉት ተረትም አድማሱ ሰፋ ይላሉ። እኔ ሲሉ የምሰማውን ነው። ሲሉ መስማት ከኩነኔ ቢያድን ከተጠያቂነት የሚያድን አይመስለኝም። አይመስላችሁም? እንዴት ነው አንድ በሉ እንጂ። ነው እናንተም መስሚያችሁ ጥጥ ነው? ግራ የገባ ነገር!
በሉ እንሰነባበት። ከጀርመን አገር የመጣውን የጥጥ ማዳወሪያ ካጋዛሁት በኋላ ከደንበኛዬ ጋር ተገባብዘን ተለያየን። ያው መገባበዝም ዘንድሮ ሰው አየኝ አላየኝ ተብሎ ሆኗል። በሰው ቁስል እንጨት የሚሰደው በምንበላው ምግብ፣ በምንጠጣው ውኃ ሊቆጣጠረን ሁሉ ሲያምረው እያየን ነው። መንግሥትን በአፈናና በፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር እየከሰሱ በትረ ሥልጣን ያልጨበጡ አምባገነኖች ራሳቸው አላስቀምጠን ብለዋል። እናም ደንበኛዬና እኔም የምንጫወተው ስለዚሁ ጉዳይ ነበር። ‹‹ጉድ እኮ ነው አንበርብር። ጭራሽ ስለምንሰማው ሙዚቃ፣ ስለምናየው ፊልም፣ ስለምንለብሰው ልብስ ቀለም፣ ውኃ ስለምንጠጣበት ብርጭቆ ቅርፅ፣ ሌላው ቀርቶ በእምነታችን ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ሊነግሩን የሚፈልጉ መጥተውልሃል። ወሬ እየፈተሉ፣ ወሬ እያያዳወሩ፣ ወሬ እየሸመኑ ሲለብሱ ውርደታቸውን ክብር አድርጎ የሚያሳያቸው መስታወታቸው እንዲሰበር ብቻ ነው ምኞቴ፤›› ሲለኝ እንደመተከዝ አልኩ። ለካ ከእኛ ሳይሆን ከመስታወታችን ነው ችግሩ ብዬ ውስጥ ውስጡን በሐሳብ ተያዝኩ። ጥያቄው መስታወቴ ማንን ነው የሚያሳየኝ? ይሁን እስኪ። የሆንኩትን ወይስ ነኝ ብዬ የማስበውን? ወይ መሆን ወይ አለመሆን፡፡ የመስታወቱን ነገር አደራ እንበል እንጂ፡፡ አለበለዚያ አንዳች ጉዳይ ባጋጠመ ቁጥር ‹‹ከነገሩ ፆም እደሩ›› እያልን፣ ውኃ ጭምር መፆም ከጀመርን ችግር አለ፡፡ ውኃ መፆም ደግሞ እርካታም ንፅህናም ያጎድላል፡፡ መልካም ሰንበት!