ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሉሲ ኮንሰልተንሲ ከተባለ የግል ድርጅት ጋር በትብብር ሲሰጥ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና እንዲያቋርጥ ማሳሰቢያ ደረሰው፡፡ የትምህርት ፕሮግራሙን እንዲያቋርጥ የተወሰነው ዕውቅና የሌለው በመሆኑ እንደሆነ፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ምዘና ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ውሳኔውን ያስተላለፈው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ነው ተብሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሉሲ ኮንሰልተንሲ ከተባለው አዲስ አበባ ከሚገኘው የግል ተቋም ጋር በመተባበር ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር ዓመታት እንደተቆጠሩ፣ ነገር ግን ፕሮግራሙ ዕውቅና እንደሌለው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ምዘና ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በሚኒስቴሩ ውሳኔ መሠረት የትብብር ስምምነቱን ያቋረጠበትን ደብዳቤ፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ ካምፓሶች በትብብር ፕሮግራም ተቀብሎ ያስመረቃቸውን ተማሪዎች ዝርዝር፣ በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ዝርዝር፣ ዩኒቨርሲቲው ‹‹በፊት ከተገለጸው›› (ኤቢኤች) በተጨማሪ ከሉሲ ኮንሰልተንሲ ጋር በትብብር ለማስተማር የተፈራረመውን የውል ሰነድ፣ ያስተማረበትን ካሪኩለም፣ የተማሪ ምዘና ሥርዓት፣ አጠቃላይ የትምህርት አስተዳደሩን ፕሮፋይል ሰነድ እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡
ዕውቅና ስለሌለው ይቋረጥ የተባለው ከሉሲ ኮንሰልተንሲ ጋር ዩኒቨርሲቲው በትብብር ለሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም በ2010 ዓ.ም. ኤጀንሲው ዕውቅና እንዲሰጥ መጠየቁን፣ ኤጀንሲው በወቅቱ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴው (ኦንላይን የትምህርት ፕሮግራም በመሆኑ) አዲስ በመሆኑ ምክንያት ሕግ ባለመኖሩ፣ እንዲያውም ሉሲ ሕግ በማውጣት ይረዳናል የሚል ምላሽ እንደተሰጠ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኤጀንሲው ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ግን፣ ዩኒቨርሲቲው ከሉሲ ኮንሰልተንሲ ጋር በትብብር ለሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም ዕውቅና እንዲሰጠው የጠየቀው ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ደብዳቤው የተጻፈው መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ ደብዳቤው በደረሰው በአምስት ቀናት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው የተጠየቃቸውን መረጃዎች እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ከሁለቱ የግል ድርጅቶች ጋር ያለውን የፋይናንስ አስተዳደርና የትርፍ ክፍፍል መረጃ የሚያሳይ ሰነድም አያይዞ እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ በሚገኙ በሁለቱ የትብብር የትምህርት ፕሮግራሞች በመማር ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች፣ እንግልት እንዳይደርስባቸውና በቀጣይ ወደ ሌላ ተቋም አዛውሮ ለማስጨረስ እንዲቻል አስፈላጊውን መረጃዎች እንዲያቀርቡለት ኤጀንሲው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የተማሪ መታወቂያቸውን፣ የተማሩትን ትምህርት የመጨረሻውን ሴሚስተር ውጤት፣ እንዲሁም ለትምህርት የከፈሉበትን ደረሰኝ ለኤጀንሲው እንዲያቀርቡ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አሳስቧል፡፡
‹‹እኛ ይህንን የምናደርገው ለተማሪዎቹ አስበን ነው፡፡ ነገር ግን መታወቂያ ተቀብለው ሊሸኟችሁ ነው እያሉ ተማሪዎችን እያደናገሩ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር የምናደርገው ለተማሪዎች ጥንቃቄ ስንል ምንም ችግር እንዳይገጥማቸው ነው፤›› ሲሉ አቶ ታረቀኝ ገረሱ አስረድተዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሉሲ ኮንሰልተንሲ በጋራ ለመሥራት ስምምነት የተፈራረመው መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሆነ፣ በኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግና ማኔጅመንት፣ እንዲሁም በሃይዌይ ኢንጂነሪንግ 101 ተማሪዎችን ተቀብሎ በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም እያስተማረ እንደሚገኝ፣ ትምህርቱን የሚሰጠውም በኦንላይን እንደሆነና እስካሁን ያስመረቃቸው ተማሪዎች እንደሌሉ ታውቋል፡፡