Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአሰላ ከተማ ልጆቼ ተገድለውብኛልና ታስረውብኛል ያሉ እናት ለዞኑ ፖሊስ አቤቱታ አቀረቡ

በአሰላ ከተማ ልጆቼ ተገድለውብኛልና ታስረውብኛል ያሉ እናት ለዞኑ ፖሊስ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

ፖሊስ የታሰረውን በግድያ ጠርጥሬዋለሁ ብሎ ፍርድ ቤት አቅርቦታል

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ ውስጥ ልጃቸው በፖሊስ እንደተገደለባቸውና ሁለተኛው ልጃቸው ደግሞ በጥይት ከተመታ በኋላ በቀዶ ጥገና ጥይቱ ከሰውነቱ ወጥቶ በእስር ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩ እናት፣ በልጆቻቸው ላይ  የተፈጸመው የወንጀል ድርጊት በገለልተኛ አካል እንዲመረመርላቸው ለአርሲ ዞን ፖሊስ ኮሚሽን ተማፅኖ አቀረቡ፡፡

የአሰላ ከተማ አስተዳደር በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል ስለተባለው ወጣት ምንም ያለው ነገር ባይኖርም፣ በጥይት ከተመታ በኋላ ኩላሊቱና ጎኑ ተጎድቶ ጥይቱ በቀዶ ሕክምና ወጥቶለታል የተባለውን ወጣት በመግደል ሙከራ ጠርጥሮ እንዳሰረው፣ ፖሊስ ለአሰላ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ በመግለጹ ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀበት ነው፡፡

‹‹በልጆቼ ላይ የተደረገው የወንጀል ድርጊት በገለልተኛ አካል ምርመራ ይካሄድልኝ፤›› በማለት አቤቱታቸውን ለአርሲ ዞን ፖሊስ ኮሚሽን ያቀረቡት አመልካች ወ/ሮ ድንቄ ኤጀርሳ ናቸው፡፡ የሟች አዲሱ ደምሴና በጉዳት ላይ እያለ ታስሮ የሚገኘው አቶ ኃይሌ ደምሴ እናት መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ ድንቄ በማመልከቻቸው፣ ድርጊቱ የተፈጸመው ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡00 ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቢሮው ተገኝተው ቢያመለክቱም ለአንድ ወር ያህል የተሰጣቸው መልስ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የአሰላ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምርያ አሰላ ወረዳ ሁለት ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በጥይት ተመትቶ ተገድሏል ተብሎ በወ/ሮ ድንቄ ስለተገለጸው አቶ አዲሱ ደምሴ ያለው ነገር ባይኖርም፣ በጥይት ተመትቶ ጉዳት ደርሶበት እያለ የዋስትና መብቱ ተነፍጎ በእስር ላይ ይገኛል የተባለውን አቶ ኃይሌ ደምሴን ‹‹በመግደል ሙከራ ጠርጥሬዋለሁ›› ብሎ ፖሊስ ነሐሴ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በአሰላ ወረዳ ፍርድ ቤት በማቅረብ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆበታል፡፡

ተጠርጣሪው አሰፋ ደምሴ በተባለ የፖሊስ አባል ላይ ሁከት በማንሳት በሽጉጥ ጭንቅላቱን፣ ሆዱን በጩቤና ፊቱን በዱላ በመምታት ጉዳት እንዳደረሰበት ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ጉዳት የደረሰበት የፖሊስ አባልም የማይናገር መሆኑንና ሊሞት እንደሚችልም በመግለጽ፣ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹እኛ ምንም አላጠፋንም፣ ፖሊስ ዝም ብሎ ነው የያዘን፡፡ እኔን በመሣሪያ ሲመታኝ ወንድሜ ወደ እኔ ሲመጣ መትቶ ገድሎታል፡፡ እኛ ምንም አላደረግንም፤›› በማለት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ተጠርጣሪውን ዋስትና በመከልከል፣ በአርሲ ዞን ማረሚያ ቤት እንዲቆይ የመጀመርያውን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፖሊስ በተሰጠው ተጨማሪ አሥር የምርመራ ቀናት የሠራውን በመግለጽ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተጨማሪ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡ ለተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ምክንያት ያደረገው ተጠርጣሪው በዋስ ቢፈታ ሊጠፋ፣ ማስረጃዎች ሊያሸሽ ስለሚችልና የመግደል ሙከራ የተደረገበት የፖሊስ አባል በፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል እየታከመ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ሪፈር ስለተባለ፣ በሞትና በሕይወት መካከል በመሆኑ ውጤቱ ተጣርቶ እስከሚታወቅ ድረስ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ ውጤት ከሰማ በኋላ 11 ተጨማሪ ቀናት በመፍቀድ፣ ተጠርጣሪው በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፖሊስ ከ11 ቀናት ቆይታ በኋላ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ ምርመራውን ስላላጠናቀቀ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው መጠየቁን ፍርድ ቤቱ ለተጠርጣሪው ገልጾለት አስተያየቱን ጠይቆታል፡፡

ተጠርጣሪው በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ወንድሙ በፖሊስ በጦር መሣሪያ ተመትቶ ሞቷል፡፡ እሱ ደግሞ ሁለት ጊዜ ተመትቶ ቁስሉ ሳይደርቅ ማረሚያ ቤት መሆኑን ገልጾ፣ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ የተጀመረው ምርመራ አለመጠናቀቁን ጠቁሞና ጉዳዩ ጠንካራና የወንጀል አፈጻጸሙ ከባድ መሆኑን ገልጾ፣ ምርመራ ለማጠናቀቂያ የአምስት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ፣ ለመስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

ፖሊስ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀርቦ ምርመራውን አለመጨረሱን፣ ተጠርጣሪው ለዘረፉ ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመሆን መሰማራቱን መረጃ ስለደረሰው፣ ግብረ አበሮቹን መያዝና ማጣራት እንደሚቀረው በማስረዳት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ 14 ቀናት በመፍቀድ ለመስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...