Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ትልቁ በሽታ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ አለመሆን ነው፡፡ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነትም እንዳለበት ቢደነግግም፣ የፌዴራል መንግሥቱንም ሆነ ክልላዊ መንግሥታትን የሚመሩ ኃላፊዎች ተግባራዊ ሲያደርጉት አልታየም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት አሠራር ድብቅ፣ ለሐሜት የተጋለጠና አንዳንዴም አስማት ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ እየሆኑ ከፍተኛ ጉዳቶች አጋጥመዋል፡፡ ኢሕአዴግ በሚመራት ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመጥፋቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ፣ የሕይወት መስዋዕትነት ባስከተለ አመፅ የአስተዳደር ለውጥ ተደርጓል፡፡ ሥርዓተ መንግሥቱ ተናግቶ የሥርዓት ለውጥ ለማከናወን ግፊቱ ቢቀጥል ኖሮ፣ ኢትዮጵያን አሁን ባለችበት ሁኔታ ለማግኘት ያዳግት ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰላማዊ ሽግግር ተደርጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩት አስተዳደር፣ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ባለፉት 18 ወራት ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ሆና በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ ለማመን የሚከብዱ በርካታ አዎንታዊ ተግባራት የተከናወኑትን ያህል፣ አገርንና ሕዝብን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የጣሉ አሳዛኝ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል፡፡ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በትረ ሥልጣኑን ሲቆናጠጡ ባደረጉት ንግግር፣ ከሕዝብ የሚደበቅ ምንም ዓይነት የመንግሥት አሠራር እንደማይኖር ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አሁንም ግልጽነት የለም፡፡ ከራሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ቢሮዎች ለመረጃ ዝግ ናቸው፡፡ ከሚዲያዎች ጀምሮ ኢንቨስተሮችን አካቶ መረጃ የሚፈልጉ ወገኖች፣ ምን ያህል እንደሚሰቃዩ የደረሰባቸው በሚገባ ያውቁታል፡፡ ከመረጃው በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ተቋማትም ሆነ በክልሎች፣ ኢንቨስተሮች ችግር ሲገጥማቸው መፍትሔ ለመስጠት ያለው ተነሳሽነት ያሳዝናል፡፡ ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች ሲስተጓጎሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉ ማምረቻዎችና የማዕድን ማውጫ ሥፍራዎች ውሳኔ አግኝተው ወደ ሥራ መግባት ሳይችሉ፣ በጉልበተኞች ምክንያት ማምረትና ማጓጓዝ ሲያቅት፣ በአጠቃላይ ለንግድና ለኢንቨስትመንት መሰናክል የሆኑ ችግሮች ሲበረክቱና የሥራ ፈጣሪዎችን ሞራል ሲገድሉ ዝም ሲባል ግራ ያጋባል፡፡ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች መሥራት አቅቷቸው ሥራ ሲያቆሙና ሠራተኞችን ከእነ ቤተሰቦቻቸው ሲበትኑ ማን ነው የሚጎዳው? ያለ ጥርጥር አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት ምን እየሠራ ነው ብሎ አጥብቆ መጠየቅ የሚገባው፡፡

የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው የሚያስፈልገው፣ ሕግ የሁሉም ነገር የበላይ መሆን ስላለበት ነው፡፡ የአገራችን ሰው፣ ‹‹በሕግ ከተወሰደችብኝ በቅሎዬ ይልቅ ያለሕግ የተወሰደችብኝ ዶሮዬ ታንገበግበኛለች›› እንደሚለው፣ በሕግ የበላይነት ሥር የማይከናወን ድርጊት ውጤቱ ሕገወጥነት ነው፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም ማረጋገጥ ሲሆን፣ የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነትን ማስጠበቅም ያካትታል፡፡ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን በሌሎች የሚቀማ ከሆነ ግን፣ ጉልበተኞችና ሥርዓተ አልበኞች አገር ያተራምሳሉ፡፡ ማንም ሰው ጥያቄ የማቅረብ መብት ቢኖረውም፣ የጥያቄው አቀራረብ ግን ፍፁም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆን አለበት፡፡ የአገርንም ጥቅም እንዳይፃረር ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡ አንድ ኢንቨስተር በሕጋዊ መንገድ እየሠራ ሳለ፣ ከሕዝብ ጥቅም በተፃራሪ እየተጠቀመ ነው ከተባለ ሕጋዊ ማስረጃ ሊቀርብበት ይገባል፡፡ ከዚያ ውጪ ሥራውን በጉልበት እንዲያቆም ማድረግም ሆነ ማደናቀፍ ሕገወጥ ነው፡፡ ይህ በእርሻ፣ በማምረቻ፣ በማዕድን ማውጫ፣ በቱሪዝም፣ በሆቴል፣ በንግድና በመሳሰሉት የተሰማሩትን በሙሉ ይመለከታል፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ወገኖች የሚጠበቅባቸው ሕግ አክብረው እንዲሠሩ ብቻ ነው፡፡ ሲያጠፉም መጠየቅ ያለባቸው በሕግ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን የመንጋ ፍርድ ሰለባ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ለኪሳራ እየተዳረጉ ሥራ ማቆም የለባቸውም፡፡ የሚሠራን አላሠራ ማለት ወደፊት መሥራት የሚያስቡትን ጭምር ሐሳባቸውን እንዲለውጡ ያደርጋል፡፡ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ተነሳሽነት ይገድላል፡፡ ለአገሬ እሠራለሁ በማለት ዕውቀቱንና ሀብቱን ይዞ የመጣ ታታሪ ዜጋን ዕቃውን ሸክፎ ወደ

መጣበት እንዲመለስ ይገፋፋል፡፡ ለአገሩ ዜጋ ያልሆነ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል በማለት የውጭ ኢንቨስተሩም ይሸሻል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ኢኮኖሚውን መቀመቅ በመክተት የፖለቲካ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው መንግሥት ኃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ስለኢንቨስትመንትና ስለሥራ ፈጠራ መነጋገር አይቻልም፡፡

ሌላው መንግሥት የሚጠየቅበት ጉዳይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ የደረሳቸው ወገኖችን የሚመለከተው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች መንግሥት ባወጣው የቤት ግንባታ መርሐ ግብር መሠረት ተመዝግበው ሲቆጥቡ የነበሩ ናቸው፡፡ በሕጋዊ መንገድ የቤቶቹ ዕጣ ወጥቶ የዕድለኞች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ከሌላ ወገን በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት ዕድለኞች ቤቶቻቸውን መረከብ አልቻሉም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ተፈጠረ የተባለውን ችግር ፈትተው፣ ቤቶቹ ለባለቤቶቹ መተላለፍ አለባቸው፡፡ የይገባኛል ጥያቄ ያነሱ ወገኖችን በተመለከተም ሁለቱ የመንግሥት አካላት ቁርጥ ያለ ውሳኔ በመስጠት፣ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ እስካሁን ይህ ባለመደረጉ መንግሥት ምን እያደረገ እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብቱ የተረጋገጠው በሕግ ስለሆነ ሕግ መከበር አለበት፡፡ መንግሥትም አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ በማድረግ ይህንን መብት ማስከበር አለበት፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት በጎደለው ቁጥር፣ ከሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ይህ ጉዳይ በአንክሮ መጤን አለበት፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ በፍጥነት መውጣት ካልተቻለ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት ያስጨንቃታል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ክምችት እንቅልፍ ይነሳታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት የሕዝቡን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ በድርቅና በመፈናቀል ምክንያት ሚሊዮኖች አስቸኳይ ዕርዳታ ይለመንላቸዋል፡፡ ሰፊ ለም መሬትና ከፍተኛ የውኃ ሀብት ቢኖርም አሁንም ግብርናው ኋላቀር ነው፡፡ ደካማ የሆነው የአምራች ዘርፍ ከውጭ የሚመጡ የካፒታል ዕቃዎችንና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን መተካት አልቻለም፡፡ የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን አሁንም ከፍተኛ ጉድለት አለበት፡፡ ሌሎች ተጨማሪ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ለጋራ ራዕይና ዓላማ አንድ ላይ መሠለፍ አለባቸው፡፡ ሠልፉን ለማስተካከል ደግሞ የሕግ የበላይነት ትልቁ መሣሪያ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ላይ መተማመን እንዲቻል መንግሥት ግልጽነትን፣ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ከታች እስከ ላይ የማስፈን ግዴታ አለበት፡፡ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ ለሕግ የበላይነት መገዛት አለባቸው፡፡ መንግሥትና ሹማምንቱም እንዲሁ፡፡ ያኔ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ መንግሥትም አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽ ይሆናል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...