መሬቱ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሚገነቡ ቤቶች ይውላል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘንድሮ ለቤቶች ልማት የሚውል 1,500 ሔክታር መሬት ለተጠቃሚዎች እንዲቀርብ መወሰኑን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
ምንጮ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ ለቤቶች ልማት እንዲውል ከተወሰነው 1,500 ሔክታር መሬት ውስጥ አብዛኞቹ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንዲነጠቁ የወሰኑባቸውና ለበርካታ ዓመታት ለታለመላቸው ዓላማ ሳይውሉ ታጥረው የከረሙ መሬቶች ናቸው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት አዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲካሄድ መወሰኑ ሲታወቅ፣ ዘንድሮ ለቤቶች ልማት እንዲቀርብ የተወሰነው መሬት የሚውለው በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት በራስ አገዝ ለሚገነቡ ቤቶች የሚውል ይሆናል፡፡
በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች፣ መምህራንና የመንግሥት ሠራተኞች ዋነኞቹ እንደሚሆኑ ምንጮች አመላክተዋል፡፡ ዘንድሮ ለቤቶች ልማት እንዲቀርብ የተወሰነው መሬት፣ ሁለት መቶ በሚሆኑ ማኅበራት ሥር ለተደራጁ ቤት ፈላጊዎች የተጠቃሚነት ዕድልን ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል፡፡
በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መደራጀት የሚቻልበት ዝርዝር መሥፈርት እየተዘጋጀ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በማንኛውም የቤት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆነ ወይም ለመሆን የተመዘገበ፣ ወይም በከተማው ክልል ውስጥ መኖሪያ ቤት ያለው ወይም የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ያለው ነዋሪ፣ የቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ሆኖ መመዝገብ አይችልም፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት ግንባታውን በሁለት መንገድ እንዲፈጽሙ ሊደረግ እንደሚችል የገለጹት ምንጮች አንደኛው መንገድ የከተማ አስተዳደሩ እንዲገነባላቸው ማድረግ ሲሆን፣ ሌላኛው አማራጭ ደግሞ በራሳቸው መንገድ መገንባት ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እንዲገነባላቸው በሚወስኑ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ አስተዳደሩ የከተማውን መዋቅራዊ ፕላን መሠረት በማድረግ በመረጡት የቤት ዲዛይን ወጪና መሬት ቆጣቢ ቤት ገንብቶ እንደሚያስረክብ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በራሳቸው ለመገንባት ከፈለጉ ደግሞ፣ የከተማ አስተዳድሩ ባፀደቀው የቤት ዲዛይን ወጪና መሬት ቆጣቢ ቤት በመረጡት ሥራ ተቋራጭ ማስገንባት እንደሚችሉ ታውቋል፡፡
በዚህ መሠረት ቤት ማስገንባት የሚፈልጉ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት በመረጡት የቤት ዲዛይን መሠረት የግንባታ ወጪውን የተወሰነ መጠን በምዝገባ ወቅት፣ ቀሪውን ደግሞ መሬት ተዘጋጅቶ የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡