Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትአንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ሲታወሱ

አንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ሲታወሱ

ቀን:

የዕድሜ ባለጠጋው አቶ ኃይለ ማርያም መኮንን፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከምሥረታቸው በቀዳሚነት ለሚነሱት ለግሪክና ለአርመን ክለቦች ከተጫወቱና በሕይወት ከሚገኙ ጥቂት ባለታሪኮች አንዱ ናቸው፡፡ ከ90 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የሕይወታቸው ምዕራፍ፣ በእግር ኳስ ስፖርት መስክ የእሳቸውን ፈለግ ለሚከተሉ ኢትዮጵያውያን ብዙ ያዩና ያሳዩ ብቻም ሳይሆኑ፣ የዕድል በሮችን የከፈቱ ስለመሆናቸውም የኋሊት ያስታውሳሉ፡፡

ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ከምትገኘው ትንሿ ጎጇቸው ሆነው፣ የዕድሜ ባለፀግነታቸው በእግር ኳሱ የነበሯቸውንና ያሳለፏቸውን የሕይወት ገጠመኞች እንደነበሩ ለማስታወስ ቢቸግራቸውም፣ በኢትዮጵያ የስፖርት ፕሮፌሽናሊዝም መስክ ቀዳሚ ከነበሩ አንጋፋ ባለውለታዎች አንዱ መሆናቸው ግን አይታበልም፡፡ በአማካይና በአጥቂ መስመር በመጫወት ትልቅ የሕይወት ተሞክሮ እንደነበራቸው ከታሪክ ማኅበራቸው እየጠቀሱ ካስረዱን ለመገንዘብ ችለናል፡፡

ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ እግር ውስጥ ታሪካቸው የሚመዘዘው አቶ ኃይለ ማርያም፣ በቡድን ደረጃ ‹‹ጥቅምት 27›› ለተሰኘውና መርካቶ አካባቢ ለነበረው ክለብ በመጫወት ስፖርታዊ ሰብዕናቸውን ማሟሸትና መገንባት እንደጀመሩ ያወሳሉ፡፡ በጊዜው የሕይወት ዕጣቸው ሆኖ፣ ስለእግር ኳስ ግንዛቤው እምብዛም ባልነበረበት ወቅት፣ ፖሊስ ክበብ አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው የመምህራን ማሠልጠኛ በሚገኝበት አካባቢ የጀመረው የእሳቸውና የኳስ ትውውቃቸው፣ ቀድሞ ከተጫወቱበት ከጥቅምት 27 ክለብ በወቅቱ ወደነበረው ወደ ጉምሩክ ክለብ ከዚያም አርመኖች ለመሠረቷቸው ክለቦች የመጫወት ዕድል እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡

- Advertisement -

አርመኖቹ በአቶ ኃይለ ማርያም ችሎታ ቢደሰቱም፣ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት በክለቡ የሚፈልጉትን ያህል እንዳይሠሩ እክል ሆኖባቸው ብዙ ጊዜ ያለ ጨዋታ ማሳለፋቸውን አይዘነጉትም፡፡ በወቅቷ አዲስ አበባ በንግድ የሚታወቁት አርመኖችና ግሪኮች በመሆናቸው፣ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረው የእኔ እበልጥ ፉክክር አቶ ኃይለ ማርያም ጨምሮ ስማቸውን አሁን ላይ የዘነጓቸውን ሦስት ሦስት የኳስ አዋቂ ሐበሾች በየቡድናቸው በማካተት ግጥሚያ አድርገው ነበር፡፡ ይህ ሲሆን፣ እሳቸውን ያሳተፈው የአርመኖች ክለብ የዋንጫ ባለቤት በመሆኑ፣ ለሸዋ ፖሊስ ቡድን ለመጫወት የቻሉበትን አጋጣሚ አይዘነጉትም፡፡

በዚያን ጊዜ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ በርካታ የአገር ውስጥ ክለቦች ብቅ ያሉበት ወቅት በመሆኑ፣ ለቅደስ ጊዮርጊስ የመጫወት ህልም ነበራቸው፡፡ እንዲህ እያሉም ለሌሎች በርካታ ክለቦች ወጣ ገባ በማለት የተጫወቱባቸውን ጊዜያት ከትውስታቸው ማህደር እየዘገኑ ያጫወቱን አንጋፋው አቶ ኃይለ ማርያም፣ ለመቶ ፈሪ በሆነው የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነውም የቀደምቱን ታሪክ በቻሉት መጠን የኋሊት  እየሳቡና እየገመዱ አውግተውናል፡፡

እንዲህ ያለውን ስፖርታዊ ማንነትና አንጋፋ ውለታ ለመዘከር እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የሰሜን አሜሪካው የኢትዮጵያውያን የስፖርት ማኅበር (ኤስኤፍኤንኤ) የባለውለታው ታሪክ ለመዘከር ለምሥጋና መታሰቢያነት ይሆን ዘንድ ወደ አሜሪካ እንዲያቀኑ ጋብዟቸው ነበር፡፡ ይሁንና ቪዛ ሊያገኙ ባለመቻላቸውና ጉዟቸው በመገታቱ ማኅበሩ ለመታሰቢያቸው ጥቂት የገንዘብ ሥጦታ ልኮላቸዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም በማኅበሩ በኩል የተደረገላቸውንና የተሰማቸውን ሲገልጹ፣ ‹‹ተረስቼ ነበር፡፡ ምሥጋና ይግባቸውና አስታወሱኝ፤›› በማለት ማኅበሩን አመስግነው፣ ወዳጅነት፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ ሕዝባዊ ማንነት ብሎም አንድነት የስፖርት መገለጫዎቹ በመሆናቸው የማያውቋቸው የአገራቸው ልጆች ታሪካቸውን አስታውሰው ስለዘከሯቸው ደስታቸው በገጽታቸውም በአንደበታቸውም ይንፀባረቅ ነበር፡፡

የዕድሜ ባለፀጋው ስፖርተኛ በቪዛ ምክንያት በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌሲቲቫል ላይ ባይሳተፉም፣ ተሳክቶላቸው ቢሆን ኖሮ ሊበረከትላቸው የነበረው 3,000 ዶላር፣ ማኅበሩ ለባለውለታዎች የሚያደርገው የዘወትር ድጋፍ ለአቶ ኃይለ ማርያምም እንዲደርሳቸው ያደረገው በኢትዮጵያ በሚገኙ ተወካዮቹ አማካይነት ሐሙስ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሆቴል በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ነበር፡፡ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያ መካከል የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ሰለሞን መኮንን (ሉቾ) ታድሞ ነበር፡፡

የአቶ ኃይለ ማርያምን የተጨዋችነት ዘመን ሙሉ በሙሉ ባያስታውሰውም፣ ከታሪካቸው በጥቂቱ የውጭ አገር ዜጋ ተብለው ድብደባ የተፈጸመባቸው ቀደምት  መሆናቸውን የገለጸው አቶ ሰለሞን፣ የገንዘብ ልገሳው ከውለታቸው አንፃር ኢምንት እንደሆነ ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞ ስፖርተኞች ኳስ የሚጫወቱት ለባንዲራ ክብር እንጂ እንደ አሁኑ ለመጦሪያ የሚሆን ገንዘብ ለማከማቸት አስበው ስላልነበር ነው ይላል፡፡

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ዘንድሮ ለ36ኛ ጊዜ መከበሩ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ፌስቲቫሎች እንደ አቶ ኃይለ ማርያም  ሁሉ ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች፣ ቪዛ አግኝተውና ተሳክቶላቸው የሄዱት በዝግጅቶቹ ታድመው ሲመለሱ፣ ያልተሳካላቸውም በማኅበሩ በኩል የገንዘብና መሰል ድጋፎች ሲደረግላቸው መቆየቱ ይታወሳል፡፡

አቶ ገበያው ታከለ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ለዓመታት በማገልገል አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኦሊምፒክ ኮሚቴ የክብር አባልና የጅምናስቲክ ፌዴሬሽን  የክብር ፕሬዚዳንት ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ማኅበርን በኢትዮጵያ ወክለው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

 በሰሜን በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ባዘጋጃቸው ፌስቲቫሎች ቀደምት ስፖርተኞች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና ለአገር በሠሩት ውለታ በተለይም አቅም ለሌላቸው ወገኖች ድጋፉ ሲያደርግ መቆየቱን የሚናገሩት አቶ ገበያው፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ከተጓዙበት ስፖርተኞች መካከልም መንግሥቱ ወርቁ፣ ካሳሁን ተካ፣ ሥራት ኃይሌ፣ ሥዩም አባተ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድና ሌሎችም እጅግ በጣም በርካታ ባለውለተኞች ዕድሉ የገጠማቸው ናቸው፡፡

ዘንድሮ ዕድሉን እንዲያገኙ የተመቻቸው አቶ ኃይለ ማርያም መኮንን ቢሆኑም፣ የአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ፣ እኚህ የቀድሞ ስፖርተኛ እዚያ ቢሄዱ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅማ ጥቅም በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የስፖርት አፍቃሪዎች የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በፌዴሬሽኑ አማካይነት ገንዘቡ ተልኮላቸው እንዲደርሳቸው መደረጉን አቶ ገበያው ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ዓላማና ተግባር ያነገበው ይህ ፌዴሬሽን፣ ለዚህ ዓይነቱ በጎነት የሚታጩ ኢትዮጵያውያን በቪዛ ምክንያት እንዳይጉላሉ በተለይም ከአሜሪካ ኤምባሲና ከሌሎችም ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር አሠራሩ የሚስተካከልበትን መንገድ ማበጀት እንደሚኖርበት አቶ ገበያው ያምናሉ፡፡ የዚህን ማኅበር ዕገዛ የሚፈልጉ በርካታ ባለውለታዎች እንዳሉ አክለው፣ ፌዴሬሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎችም  አካላት ጋር መነጋገር እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...