Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቦይንግ በአውሮፕላን አደጋ ለሞቱ መንገደኞች ቤተሰቦች 50 ሚሊዮን ዶላር ሊያከፋፍል መሆኑን አስታወቀ

ቦይንግ በአውሮፕላን አደጋ ለሞቱ መንገደኞች ቤተሰቦች 50 ሚሊዮን ዶላር ሊያከፋፍል መሆኑን አስታወቀ

ቀን:

ኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል

ክስ የመሠረቱ የቦይንግን ውሳኔ ተቃውመዋል

በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢንዶኔዥያ ላየን ኤር ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋዎች ለሞቱ መንገደኞች ቤተሰቦች ቦይንግ ኩባንያ 50 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊያከፋፍል መሆኑን፣ ሰኞ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

ቦይንግ ኩባንያ በሁለቱ አውሮፕላኖች አደጋ ለሞቱ 346 መንገደኞች በነፍስ ወከፍ ያዘጋጀውን 144,508 ዶላር ለሕጋዊ ወራሾች፣ እ.ኤ.አ. እስከ ዲሴምበር 31 ቀን 2019 ማከፋፈል እንደሚጀምር ገልጿል፡፡ ሒደቱንም ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ይፋ ማድረጉን ጠቁሟል፡፡

ገንዘቡን በተመለከተ ኃላፊነት በተሰጣቸውና ዋሽንግተን በሚገኙት ጠበቆች ኬን ፌይንበርግና ካሚሊ ኤስ ቢሮስ አማካይነት የካሳ ጥያቄው በሟቾች ቤተሰቦች ማቅረብ የሚቻል መሆኑን የገለጸው ቦይንግ ኩባንያ፣ ቤተሰቦች በምንም ዓይነት ሁኔታ የፍርድ ቤት ክርክር ውስጥ መግባት የለባቸውም ብሏል፡፡

የሟቾች ቤተሰቦች በ35 አገሮች ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ትክክለኛዎቹ ወራሾች በማግኘት ገንዘቡን ማስረከብ ፈታኝ እንደሚሆን ቦይንግ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦች ካሁኑ ሒደቱን እንዲጀምሩ አሳስቧል፡፡ የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ፣ የተዘጋጀው ገንዘብ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችን ለመደገፍ አንድ ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች፣ ወሬውን ከመገናኛ ብዙኃን ከመስማት ባለፈ የተነገራቸው ነገር እንደሌለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች የመሠረቱት ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ባዬ ደምሴ፣ ቦይንግ ኩባንያ በአሜሪካ ላሉ ሚዲያዎች መግለጫ መስጠቱን እንጂ ለእነሱ የተነገረ ነገር ባለመኖሩ፣ በቀረበው የካሳ ክፍያ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች ካሳውን በተመለከተ መስማማታቸውን ወይም ተቃውሞአቸውን የሚገልጹት፣ ቦይንግ ኩባንያ ቢያነጋግራቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ አሁን ማኅበሩ ለሟቾች ማስታወሻ የሚሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን፣ የሟቾች ልጆች ወደፊት ሲጠይቋቸው ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ማስታወሻዎች ከመሥራት ባለፈ፣ ማኅበሩ ከገንዘብና ከመሳሰሉት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን እንደማያከናውን ገልጸዋል፡፡

ቦይንግ ኩባንያ የሚያከፋፍለውን 50 ሚሊዮን ዶላር ካሳ በተመለከተ ክስ በመሠረቱ የሟቾች ቤተሰቦች የውጭ ጠበቆች ደግሞ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ በተለይ የሁለቱን አየር መንገዶች አውሮፕላን አደጋዎች ሟቾች ቤተሰቦች በመወከል በአሜሪካ 100 ያህል ክሶችን የመሠረቱ ጠበቆች፣ ቦይንግ ኩባንያ ያቀረበው ገንዘብ በቂ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

ምንም እንኳ በቦይንግ ላይ በተመሠረቱ ክሶች የቀረቡ የካሳ መጠን ጥያቄዎች ባይኖሩም፣ ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነ የሕግ ባለሙያዎችና ጠበቆች ተቋም ቦይንግ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መክፈል አለበት ማለቱ ታውቋል፡፡

ተቀማጭነቱ ቴክሳስ የሆነና የ15 ሟቾችን ቤተሰቦች በመወከል ክስ የመሠረተ የጥብቅና ድርጅት፣ ‹‹144 ሺሕ ዶላር ማንኛውንም ቤተሰብ ለመካስ በቂ አይደለም፤›› ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ይህ ገንዘብ መጠን የሟቾች ቤተሰቦችን እንደማያረካ፣ ቤተሰቦች የሚፈልጉት ግን ትክክለኛውን ምላሽ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

ቦይንግ ኩባንያ ለቤተሰቦች ከሚከፋፍለው ገንዘብ በተጨማሪ ለማኅበረሰቦች ለትምህርትና ለኢኮኖሚያዊ ድጋፍ 50 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ቢያስታውቅም፣ የሟቾች ቤተሰቦችን የወከሉ ጠበቆች ግን ለቤተሰቦች ተገቢው ክፍያ ያልተፈጸመበት አጉል ትርዒት ነው ሲሉ ቦይንግን ወቅሰዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዕገዳ ለማንሳት እስካሁን የጊዜ ገደብ አለመቀመጡን አስታውቋል፡፡ አገሮች ግን አስፈላጊውን የደኅንነት ሥራ አሟልተው ዕገዳውን በማንሳት አውሮፕላኖቹን ለማብረር መወሰን ይችላሉ ብሏል፡፡

‹‹የቅድሚያ የምንሰጠው ለደኅንነት ነው፡፡ ሥራው መቼ እንደሚጠናቀቅ የጊዜ ገደብ አላስቀመጥንም፡፡ የእያንዳንዱ አገር መንግሥት ግን አውሮፕላኑን ሥራ ላይ ለማዋል መወሰን ይችላል፡፡ ይህም አጠቃላይ የደኅንነት ሥራው ከተከናወነ በኋላ ነው፤›› ሲል በመግለጫው አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...