Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋነኛ ባላቸው ጉዳዮች ላይ...

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋነኛ ባላቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ አወጣ

ቀን:

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋነኛ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማክሰኞ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው ባለ አሥር ነጥብ መግለጫ፣ ከመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ወዲህ ባደረጋቸው ስብሰባዎች ያከናወናቸውን ተግባራት አስታውቋል፡፡

አስተባባሪ ኮሚቴው በገባው ቃል መሠረት ባለፉት አሥር ቀናት በተመረጡ ስድስት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ማስረጃዎችን አጠናቅሮና የውይይት አርዕስተ ጉዳዮችን ለይቶ ልዑካንን በማሰማራት፣ ከክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጀምሮ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ መንግሥታዊ ኃላፊዎች ጋር ሲወያይ መሰንበቱን ገልጿል፡፡ በውይይቱም በዋናነት የተነሱ ያላቸውን አሥር ነጥቦች ዘርዝሯል፡፡

በዚህም መሠረት አንደኛ በጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ካህናትና ምዕመናን፣ እንዲሁም ለተቃጠሉና ለተዘረፉ አብያተ ክርስቲያን ካሳ እንዲከፈል፣ ሁለተኛ ርዕዮተ ዓለም መር ከሆኑ ስሁት ትርክቶች የተነሳ በሃይማኖታዊ ማንነታቸው ምክንያት ብቻ ለልዩ ልዩ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች ተዳርገው ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለሉ፣ ከኃላፊነት ቦታቸውና ከሥራ መደባቸው የተባረሩ፣ ዛሬም በዚሁ ጫና ውስጥ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ፣ ሦስተኛ የቤተ ክርስቲያንን ትክክለኛ ማንነትና አገራዊ ውለታ በአግባቡ የማይገልጹ፣ ሕጋዊና መዋቅራዊ ድጋፍ ያላቸው የሚመስሉ፣ ሌሎች እምነቶችን ለበቀል የሚያነሳሱ በአጠቃላይ ኦርቶዶክሳውያንን ለጥቃት ያመቻቹና ያጋለጡ ስሁት ትርክቶች እንዲታረሙ፣ አራተኛ ለሕዝብ አገልግሎት የተሰጣቸውን መንግሥታዊ ኃላፊነት ያላግባብ በመጠቀም በምመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ልዩ ልዩ ሥልታዊ ጫናዎችን ያደረሱ፣ ቀን ቀጥረው የተከሰቱና ለመከላከል የሚቻሉ ጥቃቶችን ያላስቆሙ፣ ይብስም ጥቃቶቹን ያቀዱና ያቀነባበሩ ባለሥልጣናትና በገቢርም የፈጸሙ ቡድኖችና ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ፣ አምስተኛ ጥቃቶቹና ጫናዎቹ እንዲገቱ ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡ ኦርቶዶክሳውያን፣ አቤቱታቸው ፖለቲካዊ መልክና ይዘት እየተሰጠው ለእስርና እንግልት መዳረጋቸው እንዲቆምና የታሰሩትም እንዲፈቱ፣ ስድስተኛ በልዩ ልዩ ሰበቦች ሽፋን በመንግሥት ኃላፊዎች ፖለቲካዊ ድጋፍ ጭምር በሙሉና በከፊል የተነጠቁ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች እንዲመለሱ፣ ለመመለስ የማያስችል ሁኔታ ካለ ደግሞትክ ቦታዎች እንዲሰጡ፣ ሰባተኛ ለአዲስ አብያተ ክርስቲያናት መትከያ፣ ለመካነ መቃብር፣ ለባህረ ጥምቀትና ለመስቀል ደመራ በዓል አከባበር እንዲሁም ለራስ አገዝ ልማት የሚውሉ ቦታዎች በሕግ አግባብ እንዲሰጡ፣ ስምንተኛ በተለያዩ አኅጉረ ስብከት የሚገኙና የተወረሱ የቤተ ክርስቲያን ቤቶችና ሕንፃዎች እንዲመለሱ፣ ዘጠነኛ በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሥር ለሚገኙ፣ በቀጣይ በሚደረስባቸው ስምምነቶች ለሚመለሱናዲስ ለሚሰጡ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና/ወይም ደብተር እንዲሰጥ፣ አሥረኛ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን በሕግ አግባብ የተፈቀደላቸውን የሥርዓተ እምነት ነፃነት በመጋፋት እየደረሱባቸው የሚገኙ ጫናዎች እንዲቆሙ የሚሉት እንደሚገኙበት ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በእነዚህ ነጥቦች መነሻነት የየክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞኖችና የልዩ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች በተገኙበት በተካሄዱ ውይይቶች በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በስፋት በመወያየት ከሞላ ጎደል መግባባት ላይ መደረሱን፣ የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት የጊዜ ገደብ መቀመጡን፣ አፈጻጸማቸውን በቅርበት ለመከታተልና ቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት ለመሥራት ከመንግሥትና ከየአኅጉረ ስብከቱ የተውጣጡ አካላት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙን፣ በክልሎቹ በተቋቋሙት የጋራ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት በየዞኖቹ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መካከል ጉዳይ ተኮር ጥልቅ ውይይቶች እንዲደረጉ ከስምምነት መደረሱን ኮሚቴው በመግለጫው ገልጿል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ መግባባት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል በመንግሥት በኩል በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትንና የምዕመናን ቤቶችን መልሶ ግንባታዎች በመጀመር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተነጠቁ ይዞታዎችን በመመለስና የይዞታ ማረጋገጫ ለሌላቸው የአብያተ ክርስቲያን ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በመስጠት ተግባራዊ ምላሾች መጀመራቸውን ጠቁሟል፡፡ በአስተባባሪ ኮሚቴው የቀረቡ ጥያቄዎች የተሟላና ተገቢ ምላሽ እስከሚያገኙ ድረስ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ ኮሚቴው ከተደረጉት ውይይቶች በፌዴራል መንግሥትም ደረጃ መታየት የሚገባቸውን ችግሮች በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚነጋገር መሆኑን፣ ቀደም ሲል ቃል በገባው መሠረት ለየጉዳዮቹ የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ተከትሎ ዝርዝር ዘገባ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡

ኮሚቴው በተንቀሳቀሰባቸው ቦታዎች ሁሉ ተገቢ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማቅረብ፣ ተወካዮችን በመመደብ፣ በውይይቶችም በንቃትና በመሪነት በመሳተፍ አስተዋጽኦ ላደረጉ የአኅጉረ ስብከት ሕፈት ቤቶች፣ በተዋረድ ለሚገኙ የማኅበራትና የአገልጋዮች ኅብረት፣ የውይይት መድረኮችን ከማመቻቸት ባሻገር ለልዑካኑ መልካም አቀባበል ላደረጉ የመንግሥት አካላት ከፍተኛ ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡

‹‹ከሁሉም በላይ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የኮሚቴውን ጥሪ በመቀበል ከኮሚቴው ጎን በመሆን ለሰላማዊ ሠልፍ ራሱን በማዘጋጀቱ፣ ሠልፉም እንዲዘገይ ኮሚቴው ያስተላለፈውን መልዕክት በመቀበል ምላሹን በትዕግሥት በመጠበቁ ከፍተኛ ምሥጋናችንን እናቀርባለን፡፡ በቀጣይም መላው ሕዝበ ክርስቲያን የኮሚቴውን ሪፖርትና መልዕክት በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤›› በማለት ኮሚቴው መግለጫውን ቋጭቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...