Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአገር ውስጥ የንቅለ ተከላ ሕክምና እንደሚሰጥ የማያውቁ ሰዎች አሉ›› ዶ/ር ሞሚና መሐመድ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ሕክምና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል ዳይሬክተር

በአገሪቱ ከሚገኙ ግዙፍ የመንግሥት ሕክምና ተቋም መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ አዳዲስ የሕክምና ዓይነቶችን በአገሪቱ በማስጀመር ይታወቃል፡፡ ሆስፒታሉ በኢትዮጵያ ካስጀመራቸው የሕክምና ዓይነቶች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ነው፡፡ ሆስፒታሉ እ.ኤ.አ. ከ2013 ዲያሊስስ፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ ደግሞ የንቅለ ተከላ ሕክምና እየሰጠ ይገኛል፡፡ እስካሁን በሺዎች ለሚቆጠሩ የኩላሊት ሕሙማን አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ አጠቃላይ የኩላሊት ሕክምናና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል ዳይሬክተሯን ዶ/ር ሞሚና መሐመድን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስንት ዓይነት የኩላሊት ችግሮች አሉ? የኩላሊት ሥራ ማቆም ችግርስ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ሞሚና፡- ሁለት ዓይነት የኩላሊት ሥራ ማቆም አለ፡፡ ኩላሊት እንደማንኛውም የአካል ክፍል ብዙ ዓይነት ችግር ይደርስበታል፡፡ እንደማንኛውም ሕመም ብዙዎቹ የሚታከሙ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን የሚወራለት ግን የመጨረሻ ደረጃ የደረሰው የኩላሊት ችግር ነው፡፡ የኩላሊት ሕመም ሲባል በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ቀድሞ የሚመጣው የኩላሊት እጥበት፣ የንቅለ ተከላ ጉዳይ ነው፡፡ ትክልል ባልሆነ መንገድ መረጃው ለማኅበረሰቡ ስለደረሰ ሰው ትንሽ ነገር አሞት ሲመጣ ጭንቀቱ ከባድ ነው፡፡ ጤናማ ናችሁ ተብሎ ተነግሯቸው እንኳን አያምኑም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰዎች ጎናቸውን ቢያማቸው፣ ኢንፌክሽን ቢያጋጥማቸው ኩላሊታቸው ጨርሶ ሥራ እንዳቆመ ነው የሚያስቡት፡፡ ስለዚህ የኩላሊት ሥራ ማቆም (Renal Failure) ሁለት ዓይነት እንደሆነ መጀመርያ ማወቅ አለብን፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ኩላሊት ድንገት ቀጥ ሊል ይችላል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በዲያሊስስ ከተካነው ያገግማል፡፡ ንቅለ ተከላ የሚያስፈልገው ችግሩ ሥር ሰዶ ኩላሊት ፈጽሞ ሥራ መሥራት ሲያቅተው ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ ለማኅበረሰቡ ስላልተላለፈ የኩላሊት ሕመም ሲባል ከባድ ጭንቀት ውስጥ ነው ሰዎች የሚገቡት፡፡ ‹‹ሁሉም ፊቱ ቀልቶ ፀጉሩ ቆሞ ነው እኛ ጋር የሚመጣው፤›› በአብዛኛው የሚታከሙ ብዙ ችግሮች ኩላሊት ላይ ይደርሳሉ፡፡ የጉበትና የልብ ሥራ ማቆም የሚያጋጥማቸው እኮ ይሞታሉ፡፡ ይኼ እኮ እየጮህኸ ያለው ዲያሊስስና ንቅለ ተከላ ሕክምና ስለተጀመረ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ብዙ የኩላሊት ችግሮች በሕክምና የሚድኑ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በዕድሜ ሳይገደብ የኩላሊት ሕመም በርካቶችን ያሰቃያል፡፡ ሕመሙን መከላከል የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶችንም የሚተገብሩ ጭምር ሲታመሙ ይታያል፡፡ ይህም የችግሩ መንስዔ ብዙ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ እንደ ባለሙያ የኩላሊት ደኅንነትን መጠበቅ የሚቻልባቸውን መንገዶች ቢዘረዝሩልን?

ዶ/ር ሞሚና፡- ትልቁ ነገር ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ነው፡፡ የኩላሊት ሕመምን ለመከላከል አመጋገባችንን ጤናማ ማድረግ፡፡ የጨው አጠቃቀምን በመጠኑ ማድረግ በተለይ ከ40 ዓመት ዕድሜ በኋላ ቅባታማ ምግቦች አወሳሰድን መመጠን፡፡ ቢቻል ደግሞ ጤናማ የሆኑ ቅባቶችን እየመረጡ መጠቀም፡፡ በተለይ ጣፋጭ ነገሮችን በተቻለ መጠን መቀነስ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ አብዝቶ መመገብ፡፡ እነዚህን ካደረግን በኋላ ደግሞ በሳምንት ቢቻል ለአምስት ቀናት በየቀኑ ለ30 ደቂቃና ከዚያ በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፡፡ በአግባቡ ውኃ መጠጣት፡፡ ክብደትና ቁመትን ማመጣጠንም ትልቅ ነገር ነው፡፡

ክብደት ለዓይነት ሁለት ስኳርና ለግፊት በሽታ ያጋልጣል፡፡ ግፊትና ስኳር ደግሞ ሥር ለሰደደ የኩላሊት ሕመም ምክንያት ናቸው፡፡ በአገራችን የአኗኗር ዘያችን እየተቀየረ ነው፡፡ በአብዛኛው በመኪና ነው ምንቀሳቀሰው፡፡ አመጋገባችን ፋስት ፉዶች እየሆኑ ነው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ባህላችን አይደለም፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች በተለይ በከተሞች አካባቢ የስኳርና የግፊት ችግሮች መጠናቸው እየጨመረ ነው፡፡ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ለሚኖሩ ዜጎች እነዚህ እንደ ችግር ላይነሱ ይችላሉ፡፡ ከገጠር የሚመጡ የኩላሊት ሕሙማን ግን ብዙ አሉ፡፡ ይህ ነው ምክንያቱ ብሎ መናገር የማይቻል የኩላሊት ድክመት ነው ይዘው የሚመጡት፡፡

የተለያዩ ምልክቶች የሚታዩት የኩላሊት የመሥራት አቅም እየደከመ ሄዶ ከአሥር በመቶ በታች ሲሆን ነው፡፡ ኩላሊት ማስወገድ የነበረበት ቆሻሻ በሰውነት ውስጥ ሲጠራቀም፣ ማዕድናት ሲዛቡ ነው ምልክት አይተው ለሕክምና የሚመጡት፡፡ በየጊዜው የጤና ምርመራ ማድረግን እንደ ባህል ካልወሰድን ማወቁ ትንሽ ከባድ ነው፡፡ እነዚህ ሥር ለሰደደው የኩላሊት መድከም መንስዔ የሚባሉ ናቸው፡፡

ኩላሊት በተለያዩ ምክንያቶች በድንገት ሥራ ሊያቆም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኩላሊትን በሚጎዱ መድኃኒቶች፣ ከሰውነት ውስጥ ከመጠን በላይ የሆነ ፈሳሽ (በተቅማጥና በትውከት መልክ ሊሆን ይችላል) ሲወጣ፣ ከቁጥጥር በላይ በሆኑ ኢንፌክሽኖች ምክንያት ኩላሊት ሥራውን ሊያቆም ይችላል፡፡ አኪውት ሬናል ፌይለር የምንለውን የኩላሊት ችግር ለተወሰነ ጊዜ ኩላሊትን ተክቶ በሚሠራው ዲያሊስስ የሕክምና ድጋፍ ካደረግን፣ ሕመሙን የፈጠረውን ችግር ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እስከቻልን ድረስ ሙሉ ለሙሉ የማገገም አቅም አለው፡፡ ሥር የሰደደ የኩላሊት ድካም ግን ምልክት የሚያሳየው እንዳልኩት የኩላሊት የመሥራት አቅም ከአሥር በመቶ በታች ሲወርድ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የዲያሊስስ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የመዳን አቅሙ አናሳ ነው፡፡ ጤንነታችንን በየጊዜው የምንመረመርበትን ባህል ማሳደግ አለብን፡፡ እንደ እኛ ባሉ አገሮች ብቻ ሳይሆን ባደጉት አገሮችም ሰዎች በአግባቡ ወደ ጤና ተቋማት ስለማይሄዱ ያለባቸውን ሕመም አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ግፊትን ብንወስድ 60 በመቶ የሚሆነው በሕክምና የተረጋገጠ አይደለም፡፡ ስለዚህ ግፊት እንዳለባቸው የሚያውቁ ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ስኳርም እንደዚያው ነው፡፡ በተለይ ዓይነት ሁለት ስኳር ያለባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ምልክት ማሳየት ሲጀምር ነው ለሕክምና የሚመጡት፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያለው የሕክምና ተደራሽነት ማኅበረሰቡ ጤናውን በየጊዜው የመመርመር ባህሉ እንዲያድግ የሚፈቅድስ ነው?

ዶ/ር ሞሚና፡- ዘመናዊ የሚባሉ የዲያሊስስ፣ የንቅለ ተከላ ሕክምናዎች በብዛት ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ አይደለም በሆስፒታል፣ በጤና ጣቢያ፣ በጤና ኬላዎችም ይኖራል ብለን ከምንጠብቃቸው ትንንሽ ነገሮች መካከል ግን የግፊት መለኪያ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ የእውነት ጤናቸው ካሳሰባቸው ግፊትን መለካት ያንን ያህል ከባድ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ታዳጊ አገሮችን እየፈተኑ ስለሆነ ጤና ሚኒስቴር እንደ ግፊት ላሉ የጤና ችግሮችም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ እንደ እኛ ባሉ ታዳጊ አገሮች ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ነው እንጂ የዲያሊስስ ሕክምናውን ለሚገባው ሁሉ በመንግሥት ደረጃ ይሰጥ ማለት ከባድ ነው፡፡ በአሜሪካ ከጠቅላላ ታካሚዎች መካከል የዲያሊስስ ሕክምና የሚደረግላቸው አንድ በመቶ ቢሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን በጀታቸውን በብዛት የሚወስድባቸው የዲያሊስስ ሕክምና ነው፡፡ ዲያሊስስ በባህሪው ውድ ሕክምና ነው፡፡ ለሚገባው ሁሉ በመንግሥት ኃይል ሙለ ለሙሉ ማድረስ ይቻላል ማለት ከዕውነት የራቀ፣ ተግባራዊ መሆን የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ሕሙማን ግን የመታከም መብት አላቸውና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲያሊስስ ሕክምናን በዚህ መጠን ውድ ያደረገው ምንድነው?

ዶ/ር ሞሚና፡- የዲያሊስስ ሕክምና የዕድሜ ልክ ሕክምና ነው፡፡ ኩላሊት አንድ ጊዜ ሥራ ካቆመ በሳምንት ሦስት ጊዜ ዲያሊስስ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ቋሚ ወጪ ነው፡፡ ሁለተኛ የሕክምና ግብዓቶቹ በባህሪያቸው ውድ ናቸው፡፡ የሕክምና ግብዓቶቹን ከአምራቹ ገዝተው አትርፈው ነው ለኛ የሚሸጡት፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው የዲያሊስስ ሕክምናም እየተሰጠ ያለው በግል የሕክምና ተቋማት ነው፡፡ እነዚህ የግል ተቋማት ሕክምናውን ሲሰጡ ለራሳቸውም የተወሰነ ትርፍ ይዘው ነው፡፡ ነገር ግን እንደ አገር አንድ ተቋም ባለቤትነቱን ወስዶ ቢሠራበት፣ ከአምራች ኩባንያ ጋር በቀጥታ ተደራድሮ ግብዓቶችን መግዛት ቢችል፣ ዲያሊስሱን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጀቶች ድጋፍ እየተደረገ መስጠት ቢቻል አሁን ካለው የተሻለ ተደራሽነት ይኖረው ነበር፡፡ የሕክምና ግብዓቶቹ በባህሪያቸው ውድ ከመሆናቸው በተጨማሪ የግብይት ሰንሰለቱ ደግሞ ቀጥታ አለመሆኑ አገልግሎቱን ይበልጥ ውድ አድርጎታል፡፡ አገሪቱ ውስጥ የሚሰጠውን የዲያሊስስ ሕክምናን በኃላፊነት ተቀብሎ የሚመራ አንድ አገራዊ ተቋም ቢኖር ሕክምናውን ተደራሽ ማድረግ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከተጣራ ውኃ ጋር አደባልቀን የምንጠቀማቸውን ቅመማ ቅመም ኬሚካሎች በፈሳሽ መልክ በጀሪካን ነው ወደ አገር የሚገቡት፡፡ ፈሳሽን ትራንስፖርት ማድረግ ደግሞ በጣም ውድ ነው፡፡ ስለዚህ እዚሁ አገር ውስጥ ዱቄቱን እያስገቡ በመቀላቀል ለየተቋማቱ በማሠራጨት ዋጋውን ማውረድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ዱቄቱን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ በጥብጦ ለየተቋማቱ ማዳረስን በተመለከተ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ መረጃዎች አሉን፡፡ በእርግጥ በዚህ ረገድ ምን ያህል ርቀት መሄድ ተችሏል?

ዶ/ር ሞሚና፡- እስካሁን ድረስ ተግባራዊ መሆን የቻለ ነገር የለም፡፡ ዱቄቱን ወደ አገር ማስገባት ሲጀመር ሌሎች ተያያዥ ነገሮችም አብረውት ይመጣሉ፡፡ አንድ አካል ጉዳዩን ወስዶ በኃላፊነት ቢሠራ የምለውም ለዚህ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንድ የግል ተቋማት ዱቄቱን እያስገቡ በትንንሽ ሚክሰሮች እየሠሩ ዋጋውን ለማውረድ እየተፍጨረጨሩ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ጋ ግን የደኅንነትና የጥራት ጉዳይ ይመጣል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ስታንዳርድ ወጥቶለት ደኅንነቱና ጥራቱ በተጠበቀ መልኩ እየተዘጋጀ የሚሠራጭበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል፡፡ እስካሁን ድረስም እንዲህ በስፋት የሚሠራበት እንዳለም አላውቅም፡፡ እንዲሁ በጀሪካን የሚበጠበጥበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አገልግሎቱ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ወደፊት ግን በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል ታይቶ ሥርዓት የሚዘረጋለት ይመስለኛል፡፡ እንደ አገር ግን ጤና ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ ቢሠራበት ዋጋውን ማውረጃ ብዙ መንገዶች አሉ እላለሁ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አንዴ በብዛት ሲገዛ በራሱ ዋጋውን ተደራድሮ ማውረድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲያሊስስ ሕክምናውን ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውጪ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች እንዲሁም በተለያዩ የክልል ከተሞች መስጠት እንዲጀመር ታስቦ ወደ ሥራ ከተገባ ቆይቷል፡፡ አሁንም ግን የሕክምናው ተደራሽነት አሳሳቢ የሚባል ነው፡፡ በእርግጥ ሕክምናውን የሚሰጡ በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ምን ያህል ናቸው?

ዶ/ር ሞሚና፡-  በግንባር ቀደምትነት የዲያሊስስ ሕክምና እየሰጠ ያለው የመንግሥት ሆስፒታል ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ነው፡፡ ሕክምናውን መስጠት የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2013 ሲሆን፣ በወቅቱ ሕክምናውን ይሰጥ የነበረው ማገገም ለሚችሉ ኩላሊቶች ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አገልግሎቱን የሚሰጥ ብቸኛው የመንግሥት ተቋም ነበር፣ የነበረው ማሽንና የሰው ኃይል በጣም ውስን ከመሆናቸው አንፃር ለብዙ ሰዎች መድረስ አይችልም፡፡ የሚያገግም ኩላሊት ያላቸው ሰዎች ሦስትና አራት ጊዜ ዲያሊስስ ቢሠራላቸው አገግመው ማሽኑን ለሌላ ታካሚ ለቀው የሚሄዱ ስለሆኑ መሰል ችግር ያለባቸውን ብዙዎች ለመድረስ የተያዘ ስትራቴጂ ነው፡፡ በዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕሙማንን ጠቅመናል፡፡ በመቀጠል ሆስፒታሉ የንቅለ ተከላ ሕክምና ጀመረ፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ያለ ዲያሊስስ ሕክምና ቢቻል ጥሩ ነበር ግን ብዙ ጊዜ ሕሙማን በጣም አርፍደው ሕመሙ ሥር ከሰደደ ስለሚመጡ በዲያሊስስ ላይ ካልቆዩ ቀጥታ ወደ ንቅለ ተከላ መግባት አይችሉም፡፡ ስለዚህም ዲያሊስስ የንቅለ ተከላ ሕክምናው አንድ ፓኬጅ ሆኖ የዲያሊስስ ማስፋፊያ ተደርጎለት አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅማቸው የሚሠሩ 33 የዲያሊስስ ማሽኖች አሉ፡፡

የዲያሊስስ ሕክምናውን እንደ ቅዱስ ጳውሎስም ባይሆን የተለያዩ የመንግሥት የሕክምና ተቋማት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ሚኒሊክና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እንዲጀምሩ ጳውሎስ ማሽኖችን ከማቅረብና ባለሙያዎችን ከማሠልጠን አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በባህር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታልም እንደዚያው፡፡ መቀሌ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል አገልግሎቱን እንዲሰጥ ሥልጠና በመስጠት ግብዓቶችን በማሟላት ጳውሎስ ዕገዛ አድርጓል፡፡ ሆስፒታሎቹ የሚሠሩበት መሥፈርት ግን ይለያያል፡፡ ጳውሎስ ዲያሊስስ የሚሠራው ለንቅለ ተከላ ሕክምና ዕጩ ለሆኑና በድንገት ኩላሊታቸው ለደከመ (አኪውት ኪድኒ ፌይለር) ላጋጠማቸው ነው፡፡ ሌሎቹ ማዕከላት እንዲህ በራሳቸው መሥፈርቶች ነው የሚሠሩት፡፡ አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉት የመንግሥት ተቋማት ዘውዲቱ፣ ምንሊክ፣ ባህር ዳር ፈለገ ሕይወትና አይደር ሆስፒታሎች ናቸው፡፡ ጅማና ሐዋሳ ሆስፒታሎች በመንግሥትና የግሉ አጋርነት (Public Private Partnership) አሠራር ከግሉ ሴክተር ጋር በመጣመር የተወሰኑ ማሽኖች ኖሯቸው አገልግሎቱን በቅርቡ እንደጀመሩ ሰምቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በቀን ለምን ያህል ሕሙማን የዲያሊስስ ሕክምና ይሰጣል?

ዶ/ር ሞሚና፡- ያሉን 33ቱም ማሽኖች በቀን በሁለት ሽፍት ይሠራሉ፡፡ ማታም አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኩላሊታቸው ድንገት ሥራ ያቆመባቸው ሕሙማን በየትኛውም ሰዓት ስለሚመጡ 24 ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በመንግሥት ተቋማት የሚሰጠውን የዲያሊስስ ሕክምና ወጪ 70 በመቶ መንግሥት ነው የሚደጉመው፡፡

ሪፖርተር፡- የንቅለ ተከላ ሕክምናው ከተጀመረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ይሁንና ካለው የሕክምና ፈላጊዎች ቁጥር አንፃር ብዙ ንቅለ ተከላ ሕክምናዎች አልተሠሩም፡፡ ይህ ከምን አንፃር ነው?

ዶ/ር ሞሚና፡- ሕክምናውን መስጠት ከጀመርን አራት ዓመት አልፏል፡፡ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ ስለማውቅ የሠራነው ሕክምና ቁጥር ትንሽ ነው አልልም፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ከደቡብ አፍሪካ ውጪ እንደኛ ፕሮግራም ስኬታማ የሆነም አላውቅም፡፡ ፕሮግራሙን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚቺጋን ከሚመጣ የቀዶ ጥገና ሐኪም ጋር ነው መሥራት የጀመርነው፡፡ ፕሮግራሙን ልንጀምር ስናስብ ሦስት ባለሙያዎች ብቻ ነው የነበርነው፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ሥርዓት ከዜሮ ተነስተን ዘረጋን፡፡ ይህ ረዥም ጊዜ ነው የወሰደብን፡፡ ምክንያቱም ሐኪሞች በሚሽን ከዚያ እየመጡ እንዲሠሩ ብቻ አልፈለግንም፡፡ ስለዚህ የንቅለ ተከላ ሕክምና መሥራት የሚፈልጉ የጠቅላላ ቀዶ ጥገና ሐኪሞች መለመልንና ከዚያ ከሚመጣው ሰርጂን ጋር አብረው ሥልጠና እንዲወስዱ አደረግን፡፡ ትልቁ ትኩረታችን የነበረው ሥርዓት መዘርጋት ላይ ነበር፡፡ ንቅለ ተከላ ሕክምናውን መሥራት በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ በአንድ ቀንም ብዙ መሥራት ይቻላል፡፡

ሕክምናው የተደረገላቸው በትክክል ከንቅለ ተከላው የሚጠቀሙ ሰዎች ናቸው ወይ? የሚለው መለየት አለበት፡፡ ከዚህ ባሻገርም ቀዶ ሕክምናውን ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለው ታካሚውንና ለጋሹን በትክክል ማዘጋጀት ሲቻል ነው፡፡ ቀዶ ሕክምናው ከተሠራ በኋላ ታካሚውን ለረዥም ዓመታት በቅርበት መከታተል የሚያስችል ሁኔታን መፍጠርና ክትትል ማድረግ ነው ፕሮግራሙን ውጤታማ የሚያደርገው፡፡ ቀሪው በጣም ወሳኝ ነገር ግን የአጭር ሰዓት ሥራ ነው፡፡ ንቅለ ተከላ ሕክምና የሚደረግላቸው ሰዎች የቅርብ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ እኛም ትልቁን ሥራ የሠራነው ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ስንፈጥር እንጂ ቁጥር መጨመር ላይ አይደለም፡፡ ዓላማችን ቁጥር መጨመር ቢሆን ኖሮ እስካሁን ብዙ መሥራት እንችላለን፡፡ ከቁጥርም አንፃር ሲታይ ግን ቅድም እንዳልኩሽ እንደ አጀማመራችን ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በመጀመርያው ዓመት ሃያ ሠራን፡፡ ከውጭ እየመጣ ያግዘን የነበረው ሰው የጤና እክል ገጥሞት ስለነበር ከሦስት ወር በላይ መምጣት አልቻለም፡፡ በሁለተኛው ዓመትም እንደዚያው፡፡ ከዚያ በኋላ  ግን እየጨመረ ሄዷል፡፡ አሁን ላይ በሆስፒታሉ የምንሠራ የኩላሊት ስፔሻሊስቶች ከአንድ ወደ ስምንት አድገናል፡፡ አራት የቀዶ ሕክምና ሐኪሞችም ደርሰዋል፡፡ ቀዶ ሕክምና ሲሠሩ ከውጭ የሚመጣው ሐኪም አጠገባቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ እንጂ እነሱ ናቸው እየሠሩ ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የንቅለ ተከላ ሕክምና የተደረገላቸው የዕድሜ ልክ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ነግረውናል፡፡ ከዚያ ውጭም የሚተከልላቸው ኩላሊትም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በሌላ መተካት ያለበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ረገድ ያሉትን ብዥታዎች ቢያጠሩልን?

ዶ/ር ሞሚና፡- የንቅለ ተከላ ሕክምና ለጋሽና ተለጋሽን ከማዘጋጀት ይጀምራል፡፡ ከዚያ ቀዶ ጥገና ከተሠራላቸው በኋላ እስከ መጨረሻ ታካሚዎቹ አብረውን ነው የሚሆኑት፡፡ ሰውነታቸው ውስጥ የሚገባው ባዕድ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሰውነታቸው አይቀበለውም፡፡ በዓይን የማናያት ጀርም ወደ ውስጣችን ስትገባ ሕመም በሕመም የምንሆነው ሴሎቻችን ያንን ጀርም ከሰውነታችን ለማስወጣት በሚገጥሙት ትግል ነው፡፡ በዓይን የሚታይ ትልቅ አካል ስናስገባም ዝም ብሎ አይቀበልም፡፡ ስለዚህ ኩላሊት ያለምንም ችግር እንዲቆይ የሚያስችል መድኃኒት በቋሚነት ይወስዳል፡፡ እነዚህ መድኃኒቶችም የራሳቸው ችግሮች አሉባቸው፡፡ ባዕድ ነገር የሚለዩት የሰውነታችን ክፍሎች ሰውነታችንን ከተለያዩ ኢንፌክሽኖች የሚከላከሉ ሴሎች ናቸው፡፡ መድኃኒቶቹ የእነዚህን ሴሎች የመሥራት አቅም ነው የሚያዳክሙት፡፡ ስለዚህ ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ሰዎች በቀላሉ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ይጋለጣሉ፡፡ ጤናማ ሰው ጋር ምንም ችግር ሳይፈጥሩ አብረው የሚኖሩ ጀርሞች የንቅለ ተከላ ሕክምና የወሰዱ ጋር ሲደርሱ አደገኛ ነው የሚሆኑት፡፡ በተለይ በመጀመርያ አካባቢ እንዲህ ያሉ መድኃኒቶች በብዛት ስለሚሰጣቸው በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ሙሉ ለሙሉ ይጫኑታል፡፡ ስለዚህ ብዙ መከላከያ መድኃኒቶች ለቫይረስ፣ ለፈንገስ፣ ለባክቴሪያና ለቲቢ ሳይቀር እንሰጣቸዋለን፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች ሲወሰዱም የራሳቸው ተጓዳኝ ነገሮች አሏቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ትልቅ ችግር ሆኖ ያየነው ኢንፌክሽን ነው፡፡ መድኃኒቶቹን የምንሰጣቸው ከመጠኑ እንዳያልፉ በየጊዜው እየታዩ ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኩላሊት ዕድሜ አላት በሌላ መተካት ይኖርበታል፡፡ ዕድሜዋ ግን ይለያያል፡፡ እስከ 30 እና 40 ዓመታት አብሮ ሊኖር ይችላል፡፡ እዚያው እየተሠራላቸው ዕድሜያቸው የሚያበቃም አሉ፡፡ በሕይወት ካለ ሰው የሚወሰድ ኩላሊት ግን በአማካይ ከ15 እስከ ሃያ ዓመታት ይቆያል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የኩላሊቱ ዕድሜ ሲያበቃ ሁለቴም ሦስቴም ተጨማሪ ንቅለ ተከላ ይደረግላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የንቅለ ተከላ ሕክምና ለማድረግ ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁ ምን ያህል ሰዎች አሉ?

ዶ/ር ሞሚና፡- ያንን ያህል የተጋነነ አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ የንቅለ ተከላ ሕክምና እንደሚሰጥ የማያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ ህንድ አሠርተው እኛ ጋር ለክትትል የሚመጡ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ እዚህ ላይ የመገናኛ ብዙኃን በደንብ መሥራት አለባቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ቢመጡስ አሁን ባለን አቅም ለሁሉም መድረስ እንችላለን ወይ? የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ወረፋ የምናስይዘው ለጋሽ ኖሯቸው፣ ምርመራውን አድርገው ለንቅለ ተከላ ዕጩ ተብለው ኮሚቴ ያፀደቀውን ነው፡፡ ሌሎቹን ወረፋ አናስይዝም፡፡ ምርመራውን ጨርሰው ንቅለ ተከላ እየጠበቁ ያሉት ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ሕሙማን ብቻ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም የሚጠብቁት ጊዜ ግን ትንሽ አይደለም፡፡ በወር የምንሠራው አራትና አምስት ነው፡፡ ስለዚህም ከስድስት እስከ ስምንት ወር ወረፋ ይጠብቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሕክምናውን ለመስጠት ያሉባችሁ ማነቆዎች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ሞሚና፡- ከቦታ ቀጥሎ ያለብን ትልቁ ማነቆ የግብዓት አቅርቦት ነው፡፡ ይህ ሁሌም የማዝንበት ጉዳይ ነው፡፡ ገንዘብ ስለሌለ መግዛት አይቻልም ቢባል ይገባኝ ነበር፡፡ እያስቸገረ ያለው ግን ሥርዓቱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ከባድ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው አገልግሎቶች ከተጀመሩ በኋላ የተለየ መንገድ ካልተፈጠረ አሁን ባለው የግዥ ሥርዓት እንዲቀጥሉ ማድረግ አሳሳቢ ነው፡፡ ከኪሳችን እያዋጣን የምንደጉምበት ጊዜ በጣም ብዙ ነው፡፡ ይኼ ሕክምና ደግሞ በአቅርቦት ላይ በእጅጉ የተወሰነ ነው፡፡ አዲስ ንቅለ ተከላ ላንሠራ እንችላለን፡፡ የተሠራላቸውን በሕይወት ለማቆየት ግን መድኃኒቱን ማግኘት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ሁሌ በእጥረትና በሰቀቀን ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ግብዓቶቹን ገዝቶ የሚያቀርበው የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ነው፡፡ ኤጀንሲው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሁሉንም የመንግሥት ተቋማት የሕክምና ግብዓቶች በሙሉ ገዝቶ ያቀርባል፡፡ እነሱ ላይ ያለው ጫናም ይገባኛል፡፡ ለዚህ የተለየ ሥርዓት ነው ሊዘረጋለት የሚገባው፡፡ ጨረታ አውጥተው ብዙ ወራት ፈጅቶ እነዚህ እነዚህ ምላሽ አላገኙም ተብሎ ተመላሽ ይደረጋል፡፡ እንደገና ሌላ ጨረታ ይወጣል፣ ሌላ ብዙ ወራት ይፈጃል፡፡ አንዳንዴ መድኃኒት አልቆ ደረሰ አልደረሰ ብለን ስንጨነቅና ሲያቃዥን የምናድርበት ቀን አለ፡፡ ሌላ የግዥ ሥርዓት ካልተፈጠረ በስተቀር በዚህ ሒደት እስከ መቼ ልንቀጥል እንደምንችል ያሳስበኛል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...