Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሞራል ግንባታ ላይ ነን!

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከመገናኛ ወደ ሳሪስ ነው። የትውልድ ድር ዛሬም በጉዞ ውስጥ እያደራና መልሶ ሌላ ትውልድ እያፈራ ሊቀጥል ሩጫ በሩጫ ሆነናል። በሚዘበራረቀው የአየር ንብረትና የአኗኗር ዘይቤ፣ በተደበላለቀ ስሜትና ቅጥ ባጣ ውጣ ውረድ ሰው ተጨናንቆ መንገዱን ያጨናንቃል። መኪኖች ባለፉ ባገደሙ ቁጥር ጥሩንባቸውን የሰው ጆሮ ውስጥ ያደበላልቁታል። ጩኸት በጩኸት። ሰሚ የለም እንጂ ለሚረባውም ለማይረባውም ይጮኻል። የድምፅ ብክለት ከአየር ብክለት ሳይተናነስ መንፈስ ይረብሻል። መንገደኛውም በምን እንደሚረበሽ ግራ እየተጋባ ራሱን መቆጣጠር ተስኖት መልሶ ከራሱ ጋር ይጣላል። ዓይን ብዙ ያሳያል ጆሮ ብዙ ያሰማል። የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ሸቀጦቻቸውን ከፍ አድርገው ይጣራሉ። ያሰበውም ያላሰበውም ዞር ብሎ ይቃኛል። የዘመኑ ጣራ የነካ ዋጋ ያራቆታቸው፣ ያዳካማቸውና ያቀጨጫቸው ዓይኖች እንደ ዋዛ አይተው መልሰው መንገዳቸውን ይጀምራሉ። ኑሮ ያታከተውና መላ ህዋሳቸውን የተሸከመው ሰውነታቸው ተረኛው ታክሲ ውስጥ አምጥቶ ሲያሳርፋቸው ‹‹ዕፎይ!›› ይላሉ ጮክ ብለው። ‹‹እፍ›› የተባለው አየር ተመልሶ ‹‹እፍ›› እስኪባል፡፡

ወያላውና ሾፌሩ የተሰወሩበትን ታክሲ ተሳፋሪዎች በአሰልቺ አሰሳ ፈልገው ሲያገኙት በአንዲት አዛውንት ጋባዥነት ይሳፈራሉ። ‹‹ግቡ! ግቡ!›› ይላሉ አዛውንቷ ፈገግ ብለው። የብስጭት ቀናት በአዛውንቷ አባባል የተገፈፉ ሲመስሉ ለአፍታ ፈገግ በሚሉት ተሳፋሪዎች ገጽ ላይ አጠናለሁ። ‹‹ዛሬ ወያላዋ እኔ ነኝ ግቡ ዝም ብላችሁ፤›› ይላሉ እሳቸውም ሳቅ እያሉ። እርጅናቸው ውስጥ ሁሉን ሞክሮ የናቀ የሕይወት ልምድ ያለ ይመስላል። ‹‹በአዲሱ ዓመት መክፈል የለም ምሬያችኋለሁ!›› እያሉ ጨዋታቸውንም ሥራቸውንም ቀጥለዋል። ተሳፋሪዎች ነገረ ሥራቸው እያዝናናቸው እርስ በርሳቸው ይንሾካሾኩ ጀምረዋል። ‹‹እኛ ጠርተን፣ እኛ ተሳፍረን፣ እኛው ትርፍ ተጭነን፣ እኛ ወራጅ አለ ብለን መቻላችን ግን ይገርመኛል። ስንት ይሆን የቻልነው?›› ሲል አንድ ቀጠን ያለ ወጣት ተሳፋሪ፣ ‹‹ምን ይገርማል? ልንገለገል በሄድንበት ሥፍራ ሁሉ አገልግለን መመለሳችን ዛሬ ይሆን የገባህ? አይ ወገኔ መቼ ይሆን ቶሎ የሚገባህ?›› ብሎ ይመልስለታል አጠገቡ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹እውነትህን እኮ ነው የተናገርከው። ሕዝብ እንዲያገለግሉ ተሹመው ራሳቸውን የሚያገለግሉ በዝተዋል። እኔማ አሁን አሁን ሹም በበዛ ቁጥር አይ ዕድላችን፣ ደግሞ የዚህ ቤት እስኪቃና በግል የምንከፍለው ግብር (ጉቦ ማለታቸው ነው) ስንት ይሆን እላለሁ። ግቡ! አዎ ሳሪስ ነው፤›› እያሉ አዛውንቷ ይናገራሉ። ‹‹የሚወራው ወግ ሁሉ ከፖለቲካና ከገንዘብ ራስ ላይ አልወርድ ያለው እውነት በኑሮ ውድነት ምክንያት ብቻ ነው?›› እያለ ከመካከላችን አንድ ጎልማሳ ሲጠይቅ እንሰማዋለን፡፡

ታክሲያችን እንደ ሞላ ወያላውና ሾፌሩ ከየት መጡ ሳንላቸው ከች አሉ። ‹‹ተመልከት አንዱ በዘራው ሌላው ያጭዳል ማለት ይኼ ነው፤›› ይላል ጎልማሳው። አዛውንቷ ሳቅ እያሉ እያዩት ትከሻቸውን ይሰብቁለታል (ምን ይደረግ ነው ነገሩ)፡፡ ‹‹ለመሆኑ የት ሄዳችሁ ነው?›› ይጠይቃሉ አዛውንቷ። ‹‹የት አባታችን እንሄዳለን እማማ? እዚሁ ነበርን፤›› ይመልሳል ወያላው እየተቅለሰለሰ። ‹‹እኔ በሰበሰብኩት አንተ ስትከብር ዝም ብዬ ላይህ ነው?›› ብለው ፈገግታ የማይጠፋበት ፊታቸውን ወደ እኛ አዙረው ሲጠይቁት፣ ‹‹ምን ችግር አለው? ለስንቱ ዝም ያለ አፍ ለእኔ ቢከፈት አያስቀስፍ?›› ብሎ ይመልስላቸዋል። እሳቸውም ከት ብለው ይስቃሉ። ‹‹እውነት ብለሃል ልጄ!›› ብለው ደግመው ከትከት አሉ። ‹‹ለአንዳንዱ ዕንባ ለአንዳንዱ ሳቅ ሲፈጠር የተቸረው ይመስላል ልበል?›› ይላል መሀል ወንበር ላይ የተቀመጠው ጥያቄ የማያልቅበት ጎልማሳ። ሾፌሩ ታክሲውን ሊያንቀሳቅስ ከፊትና ከኋላ አጥብበው ከቆሙት ተራ ጠባቂ ታክሲዎች ጋር ይታገላል። ድንገት አምስት የሚሆኑ ወጣት ሴቶች ወያላውን ካልጫንከን ብለው ይለምኑት ጀመር። ወያላው ሊጭናቸው የዘጋውን በር መልሶ ከፈተው። ሰው ያጉረመርም ጀመር። ሾፌሩ ደግሞ፣ ‹‹በትራፊክ ፖሊስ ብያዝ አንተው ትለምነዋለህ?›› ብሎ ያስጠነቅቀዋል። ተናግረው ሳይጨርሱ ሳቅ የሚያፈርሳቸው ወጣቶቹ እየተንጋጉ ገቡ። ወያላው በሩን ከዘጋ በኋላ፣ ‹‹ደግሞ ለመለመን፣ ያደግነው በልመና የምናድገውም በልመና አይደል? መለመን ያቅተኝ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፤›› ይለዋል ሾፌሩን። አባባሉ ነገር ነገር ሲሸት ለራሱ እየታወቀው ይመስላል። አግቦና አሽሙር ዛሬም እንዳሉ ናቸው፡፡

ታክሲው መንገዱን ይዞ መጓዝ ጀምሯል። ነገር ግን የሁላችንም ትንፋሽ ማለት ይቻላል በአንድ ከባድና ነጎድጓድ ድምፅ ተውጧል። ከአዛውንቷ ጀርባ መካከለኛ ወንበር ላይ የተቀመጠች ጠየም ወፈር የምትል ተሳፋሪ በሞባይል ስልክ እያወራች ነው። እያወራች ከማለት ግን እያደነቆረች ማለት ይቀላል። ሰው እርስ በርሱ እየተያየ፣ ‹ምነው መንግሥት የድምፅ ብክለትን ችላ አለው?› ይባባላል። አንዱ ደግሞ ይቀበልና፣ ‹‹ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባው ላይ ቂጥጥ አሉ፡፡ መጀመርያ የአየር ንብረት መዛባት ችግር መቼ አንድ ተባለ?›› በማለት ይመልሳል። ‹‹ቆይ! ቆይ! እኛስ ብንሆን በአካባቢያችን ዓይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን ሆነን የምናልፈው ብክለት የለምና ነው?›› ጎልማሳው ከኋላ መቀመጫ ይጠይቃል። ‹‹እውነት ነው!›› እያሉ አዛውንቷ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። ወያላው ተገርሞ ሲያየን ቆይቶ፣ ‹‹የአንድ ዕድር አባላትን ነው እንዴ የጫንነው?›› ብሎ ሾፌሩን ጠየቀው። ሾፌሩ አልመለሰለትም ሳቀ እንጂ። ‹‹ምነው የገዛ አየራችሁን አትተንፍሱት ልትለን ነው? ወይ ጉድ ከዚህ በላይ ነገር አለ?›› ሲሉ አዛውንቷ ወያላው፣ ‹‹ኧረ እኔ ምን አግብቶኝ? ቀጥሉ!›› ብሎ በግራ እጁ ውስጥ የያዘውን ዝርዝር መቆጣጠር ጀመረ። ‹‹እማማ ስንናገር የሚጠሉን፣ ዝም ስንል የሚንቁን፣ ስናዳምጥ የሚፈሩን፣ ንቀን ስንተው የሚከተሉን፣ ብቻ ምን አለፋዎት እንደ ዘመኑ የአየር ንብረት ባህሪያቸው ግራ የሚያጋባ አልበዙቦትም?›› በማለት ያ ጠያቂ መሳይ ጎልማሳ ሲጠይቃቸው፣ ‹‹እንዲያ በል አንተ!›› ብለውት በፉከራ ቃና አዛውንቷ አጨበጨቡለት። የአሁኑ እንኳ የብሽቀት ሳይሆን ይቀራል? 

በስልክ የምትነጋገረው ተሳፋሪ አናግራ እስክትጨርስ ትዕግሥት አጥቶ ይጠባበቅ የነበረው አጠገቧ የተቀመጠ ተሳፋሪ ልክ ስትጨርስ፣ ‹‹ምነው ምን አደረግንሽ በፈጠረሽ? ቀስ ብሎ መነጋገር ማንን ገደለ?›› አላት ጆሮውን እያሻሸ። ‹‹አየህ ዕድሉ ሲገኝ በደንብ መናገር አለብህ። የታክሲው ሠልፍ ወደ ቤታችን ላለመምጣቱ ምን ማረጋገጫ አለህ? ከቻልክ ተረፍረፍ አድርገህ የነገ የተነገ ወዲያውን መልዕክት ሳይቀር ማስተላለፍ ነው። ይኼን ቀርፋፋ ልማዳችንን አምኜ ልነግድልህ ነው?›› አለችው። ‹‹እንዲያ ነው ነገሩ? እኛ ምን አጠፋን ታዲያ የምንደነቁረው?›› ብሎ መልሶ ቢጠይቃት ዞር ዞር ብላ ዓይታን ስታበቃ፣ ‹‹ለሁሉም ባይሆንም ለአንዳንዱ ሰው ጆሮ በደንብ ጮኾ መንገር ነው ጥሩ። አቤት! አቤት! መንግሥትማ አንድ ትልቅ የሚሰማ ጆሮ ቢኖረው እንዴት አሪፍ ነበር? ደግሞ እኛስ ብንሆን ለሐሜትና ለወሬ እየተነቃቃን ለቁም ነገሩ ጊዜ ደነቆርን ማለትን መቼ ነው የጀመርነው?›› ብላው ውጪ ውጪውን ማየት ጀመረች። ‹‹ኧረ ስንናገር እየተሳሰብን፣ ስንኖርስ መቼም አልሆነልንም፤›› ይላል ከኋላ የተቀመጠው ጎልማሳ፡፡ አጠገቡ የተቀመጠው ደግሞ፣ ‹‹አይደል እንዴ?›› ብሎ የድጋፍ ድምፅ ይሰጣል። የድጋፍ ድምፅ ያስፈልገናል የሚሉን ደግሞ እኛን ባለ ድምፆቹን ረስተው የተውትን እንካ ሰላንቲያ ጀምረዋል፡፡

‹‹ቀስቃሹ ጥቂት የሚያንቀላፋው ብዙ ሆነ እንጂ እሱስ እውነቱን ነበር፤›› አለች ሴትየዋ ዓይኗን ከደጅ መልሳ፡፡ ‹‹ወንድሜ አሁንማ ቪዛና ሲስተም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነውልሃል እረፈው፤›› አለችው፡፡ ‹‹እንዴት?›› አላት ፈታ ያለ ጨዋታዋ መስጦት። ‹‹ምን እንዴት አለው? በስደት ስማችን ገኖ እየተነሳ በመሆኑ ‘ቪዛ’ የማግኘት ዕድልም እኮ አብሮ ይመናመናል። በኔትወርኩ ምክንያት የተፈጠረውን የሲስተም መናጋት ደግሞ ለቀባሪው ማርዳት ነው። ስለዚህ ከስንት በዋል ፈሰሶች ተርፎ በአጋጣሚ የምታገኘው ኔትወርክ የሚያስደስትህና በገፍ ከሚጓዙት ስደተኞች ተርፎ ቪዛ ሲመታልህ የምትደሰተው እኩል ሆኗል፤›› አለችና ብቻዋን ሳቀች። የቪዛውስ ግዴለም ባንክ ቤትና ኤቲኤም ሥር መሠለፍ የሰለቸው ስንቱን ይለው ይሆን!

ታክሲያችን መጓዙን ቀጥሏል። ወያላው ሒሳብ እያለ መፈናፈን አቅቶት ይንቆራጠጣል። ‹‹አዛውንቷ የለም! አንድም ሰው እንዳይሰጠው። እኔ ሰብስቤ አንተ ልትወስድ ነው? አመረርክ እንዴ አንተ ሰውዬ?›› ብለው ሲያናግሩት መናገር አቃተው። ነገሩ ያልገባቸው በትርፍ የተሳፈሩት ወጣት ሴቶች እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር። ‹‹የምር አንከፍልም?›› በማለት አዛውንቷን ሲጠይቁ እሳቸውም መልሰው፣ ‹‹ወደን ነው የምንከፍለው? የእስራትና የኃጢያት እንጂ የገንዘብ ምሕረት ማን ያውቃል?›› ብለው የሰውን አንገት በአዎንታ አስወዘወዙት። ወያላውም ቀልዱ እንዳበቃ አውቆ ሒሳቡን መሰብሰብ ጀመረ። ትርፍ ተጫኞቹ ጓደኛማቾች የየራሳቸውን እያወጡ መክፈላቸውን ቢያይ ደግሞ ጎልማሳው ጠያቂ፣ ‹‹እውነት እኮ ነው፣ ድሮ ተብሎ ያልቀረ ምን ነገር አለ? ሲስቁ አብሮ ሲከፍሉ ለየብቻ። ሲበሉ አብሮ ሲከፍሉ ለየብቻ። የገንዘብ ጊዜ ሁሉም ራሱን ቻይ ሆነ። ‘እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም› የሚሠራው አሁን ነው፤’ አለ። ‹‹ራስን መቻል መበረታታት ሲገባው አንዱ የሌላው ጥገኛ ለምን አልሆነም ማለትን ምን አመጣው? ግለሰብ ራሱን ካልቻለ አገር እንዴት ያድጋል?›› የሚለው አጠገቤ የተቀመጠ ታዳጊ ነው፡፡

ጉዞአችን እየተገባደደ ነው። ወጋችንም እየተገባደደ ይመስላል፡፡ አዛውንቷ ሁሉንም ካዳመጡ በኋላ ምክር ቢጤ ጣል ማድረግ ፈልገዋል፡፡ ‹‹ልጆቼ ለማንኛውም ጉዳይ ትልቁ መፍትሔ ሞራል ነው፡፡ በሞራል የተገነባ ሕዝብ በራስ መተማመን ይኖረዋል፡፡ ከሌብነትና ከሙስና የፀዳ ነው፡፡ አገርን ለማሳደግና ሕዝቡን ለማበልፀግ ወሳኙ ሞራል ነው፡፡ ሞራል ያለው ትውልድ በማንም አይበገርም፡፡ ሞራል ሲላሽቅ ኪሳራው ከባድ ነው፡፡ ሞራል ሲገነባ ግን እንኳን ለራሳችን ለሌላውም እንተርፋለን፤›› ሲሉ ወያላው፣ ‹‹እማማ መልካሙን እንዳሰሙን መልካም ይግጠምዎት፤›› ብሎ ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ሸኘን፡፡ እሳቸው በመውረድ ላይ እያሉ፣ ‹‹አሜን ልጄ! ሁላችሁንም መልካም ይግጠማችሁ፡፡ ከነገረኛ፣ ከሸረኛ፣ ከሴረኛ፣ ከራስ ወዳድና ከአገር አጥፊ ይሰውራችሁ. . .›› ብለው ተሰናበቱን፡፡ ትልቅና ጨዋ ይኑሩ፣ ትልቅና ጨዋ በሌሉበት ባለጌ ይፈነጥዛል፡፡ ለዚህም ነው ሞራል ገንቢ የሚያስፈልገን፡፡ በባለጌ ላለመዋረድ ሞራል መገንባት የግድ ነው፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት