Saturday, June 22, 2024

አዲሱ የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያና የባለሙያዎች ዕይታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ከ17 ዓመታት የጦር ትግል በኋላ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ኢትዮጵያን የመምራት ተራውን ከወታደራዊው የደርግ መንግሥት የተረከበው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ በተከተለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮትና በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ማስፈጸሚያነት ለተከታታይ አሥር ዓመታት ባስመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዲሁም ከድህነት ወለል ከነበሩበት ከፍ ባደረጋቸው ዜጎች ምክንያት መልካም ስም ማትረፉ ይነገራል፡፡ ከጅምሩ ‹‹ሲያዩት የማያምር ሲበሉት ያቅር›› ሆኖ በሕዝባዊ ምሬትና በወታደራዊ ትግል ከመንበረ ሥልጣኑ የተወገደው የደርግ መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእንፉቅቅ እንዳስኬደው የሚተች ሲሆን፣ ይኼንን የተንፏቀቀ ኢኮኖሚ ወደ ልማት በመቀየር ረገድ የኢሕአዴግ መንግሥት ጉልህ ፈተናዎችን እንደተጋፈጠና የተሻሉ ለውጦች እንዳስመዘገበ በማተት በበርካቶች ዘንድ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡

በጦርነት የተዳከመን ኢኮኖሚ ማንቀሳቀስ ላይ ከባድ ፈተና ገጥሞት ሳለ የምዕራቡን ዓለም በማር የተለወሰ የርዕዮተ ዓለም ጫናን መቋቋም ችሎ መቆየቱ የሚደነቅለት ባህርይ እንደሆነ፣ በርካታ ጸሐፍትና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚያው ልክ ትችት የሚያቀርቡበትም አሉ፡፡

በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም. የማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ) ባዘጋጀው የምክክርና የውይይት መድረከ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዕውቁ የኢኮኖሚ ባለሙያና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹አጠቃላይ የኢኮኖሚውን ልማት በሚመለከት ጥሩ የሚባል የኢኮኖሚ ዕድገት ቢኖርም የዓብይ ኢኮኖሚ (ማክሮ ኢኮኖሚው) በዋጋ ንረቱ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረቱና በዕዳ ጫናው ማሳያነት መረዳት እንደሚቻለው የተናጋ ሆነ፡፡ ዕድገቱ የተባለውን ያህል ድህነትንና በሀብታምና በደሃ መካከል ያለውን የገቢ ልዩነትን አላሸነፈም ነበር፤›› ሲሉ፣ በልማታዊ መንግሥት ጥላ ሥር ተመዘገበ የሚባለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ይተቻሉ፡፡

ዓብይ ኢኮኖሚው እንዲናጋ ያደረገውም በብድርና ገንዘብ በማተም ላይ የተመሠረተና ዘላቂ የወጪ አሸፋፈን ሥርዓት ያለመኖሩ፣ እንዲሁም በተገኘው ብድር ሊኖር የሚችለውን የመልማት ዕድል ያባከነ መሆኑ እንደሆነ በመጠቆም፣ ልማታዊ መንግሥቱ የጠራ ‹‹የንድፈ ሐሳብ መሠረት›› ያልነበረው መሆኑን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡

‹‹ዕድገቱ መዋቅራዊ ለውጥ አላመጣም፣ ስለሆነም ሥራ አጥነትንና ድህነትን የሚባለውን ያህል አልቀነሰም፤›› በማለት የሚተቹ ሲሆን፣ ‹‹መንግሥት የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም እንጂ የሠለጠነ የሰው ኃይልና የዕውቀት መሠረት አልነበረውም፡፡ የሠለጠነ የፖሊሲ ተመራማሪ፣ አማካሪና ባለሙያ ቢሮክራሲ የለውም፣ ጥራት ባለው ትምህርትም አልተፈጠረም፤›› ሲሉ ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ክፍተቶቹን ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥትን የኢኮኖሚ ለውጥ ተስፋ ገምግመው ስማቸውን ይፋ ሳያደርጉ በጽሑፍ ያስነበቡ አንድ ባለሙያ፣ በልማታዊ መንግሥት የማስፈጸሚያ ሥልት ተጠቅሞ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ላይ አተኩሮ ሲሠራ የቆየው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ‹‹ፈጣን የጠቅላላ የኢኮኖሚ ምርት ዕድገትን፣ የተሻለ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን፣ የማኅበራዊ አገልግሎት አቀራረብን ማሻሻልና ከፍ ያለ የውጭ መዋዕለ ንዋይ መሳብን አስችሏል፤›› በማለት፣ ‹‹በሌላ ወገን ከፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር የተደመሩ ከፍተኛ የድህነት ጫና፣ እየጨመረ የመጣ የሥራ አጥነት፣ መሻሻል ያቃተው የወጪ ንግድ፣ ከፍተኛ የዕዳ ጫናና እያደገ የመጣ የሀብት ልዩነት የሚያንገላታው ነው፡፡…ልማታዊ መንግሥቱ የራሱ ጠላት ነው ማለት ይቻላል፤›› በማለት፣ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ዕድገት ግድፈቶች ይጠቁማሉ፡፡

አክለውም በተንሰራፋው በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ የታገዘው ሌብነት ሳቢያ፣ ያላግባብ በተገኘ ሀብት ደሃውን ዋጋ ያስከፈለ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠርም ሆኗል በማለት ያመለክታሉ፡፡

በዚህ የተዛባ የኢኮኖሚ መሠረት ወደ ሥልጣን የመጣው የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. እነዚህን ችግሮች ለይቻለሁ፣ ለመቅረፍም አቅጃለሁ በማለት ‹‹አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም›› ዕቅድ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ ሪፎርም ይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ሁለት መልክ እንዳለው በማመላከት፣ አንደኛው ሁሉንም ያኮራ ፈጣን ዕድገት እንደሆነና ሁለተኛው ደግሞ ሕዝብን ያስመረረ ኢፍትሐዊነት መንሰራፋቱ ነው ብለው ነበር፡፡

አገሪቱን ከዝቅተኛ የመካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ለማሠለፍ በማለም በትምህርት ተደራሽነት፣ በጤናና በተለያዩ ዘርፎች አኩሪ ውጤቶች መመዝገባቸውን የቀረበው ሰነድ ቢያስረዳም፣ የታለመውን የመካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ የመሠለፍ ግብን ለማሳካት ግን ረዥም ርቀት መጓዝ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው አሥር ዓመት ያስመዘገባቸውን ስኬት ለማስቀጠልና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመወጣትና አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ እየተፈጠሩ ያሉ የዓብይ ኢኮኖሚ መዛባቶችን ማረቅ፣ መዋቅራዊ ማነቆዎችን ማቃለል፣ እንዲሁም አዳዲስ ዕድሎችንና የዕድገት ምንጮችን መፍጠር ያስፈልጋል የሚለውና በጽሑፍ አቀራረብ (ፓወር ፖይንት ስላይድ) የተዘጋጀው ሰነድ፣ ‹‹የፖሊሲና የተቋማዊ ማዕቀፎቻችንን ከፍ በማድረግ ድሎቻችንን ወደ ላቀ ደረጃ ማውጣት ያስፈልጋል፤›› በማለት ያትታል፡፡ የዓብይ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፎችን ከፍ በማድረግ ዘመናዊና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ልማት ማምጣት እንደሚያስፈልግ፣ ለመገንባት የሚታሰበውን ዘመናዊ ኢኮኖሚ መደገፍ እንዲያስችል ተቋማት ብቁና ግልጽ መሆን እንዳለባቸውም ሰነዱ ያስቀምጣል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡ፣ ከፍተኛ የድህነት ቅነሳ ብሎም የተሻሻለ የሰው ሀብት ግንባታና የመሠረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ስኬቶች እንደነበሩ የሚያስቀምጠው ይኼ ሰነድ፣ ዕድገቱ በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ የመጣ እንደሆነና በግንባታና በአገልግሎት ዘርፎች መስፋፋት የተገፋ ነበርም ይላል፡፡ ሆኖም የኢኮኖሚ ዕድገቱ መዋቅራዊ ለውጥን በማበረታታት ረገድ እምብዛም ውጤታማ እንዳልነበረ በማተት፣ የገቢ ዕድገት በዋናነት የተመዘገበው በሀብት ክምችት እንጂ በምርታማነት ዕድገት አልነበረም ይላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባጋጠሙ የዓብይ ኢኮኖሚ (ማክሮ ኢኮኖሚ) መዛባቶች ሳቢያ ኢኮኖሚው እየተፈተነ እንደሆነም በሰነዱ ታምኗል፡፡ ይኼ መዛባትም በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በውጭ ዕዳ ጫና፣ በተቆጠበ የግል ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት፣ እንዲሁም በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይገለጻል በማለት የኢኮኖሚውን ችግሮች ያስረዳል፡፡

በዚህ መንደርደሪያነትም ‹‹የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ለሥራ ፈጠራና ዘላቂ ዕድገት›› በሚል መርህ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮችና ፈተናዎች ለመወጣት ሁሉን አቀፍ በሆነና እርስ በርሱ በተናበበ ዕርምጃ መፍትሔ እንደሚሻ ሰነዱ ቃል ይገባል፡፡

ስለዚህም በዓብይ ኢኮኖሚ ላይ በሚደረገው ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የፋይናንስ ምንጭን ማሻሻልና የብድር ዘላቂነትን ማረጋገጥ እንደሚሳኩ በማለም፣ በመዋቅራዊ ማሻሻያዎች ደግሞ የንግድ ሥራ ማነቆዎችን ለማቃለል እንደሚሠራ በመግለጽ፣ የእነዚህ የሁለቱ ማሻሻያዎች ቅንጅት እምነትን ለመገንባትና ዕድገትን በማመጣጠንና ምርታማነትን በማሻሻል ረገድ ውጤት እንደሚያመጣ ያሳያል፡፡ ይኼም በሥራ ፈጠራ፣ በአካታች ዕድገት፣ በድህነት ቅነሳና ወደ ብልፅግና የሚወስድ መንገድ መቀየስ ላይ ያግዛል ይላል፡፡ በዘርፉ ማሻሻያዎች ደግሞ ዘርፍ ተኮርና ልዩ የሆኑ ተቋማዊና የገበያ ውድቀትን ለመቀልበስ ያግዛል ይላል ሰነዱ፡፡  

መንግሥት ይኼንን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለልማት አጋሮችና የውጭ አገር መንግሥታት እንደራሴዎች ጳጉሜን 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ባስተዋወቀበት ወቅት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዋና ጸሐፊ፣ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ እንዲሁም የልማት አጋሮች አስተባባሪ መንግሥታት በኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየትና በግልጽነት በማሳወቁ ያመሠገኑት ሲሆን፣ ይኼ ሪፎርም በዝርዝር ሲሠራ የሚታዩ ክፍቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ዝርዝር ዕቅድ ተሠርቶ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእያንዳንዱ ለውጥ ምክንያት ሊገኝ የሚችለው ጥቅም በገንዘብ ተሠልቶ እንዲቀርብም ጠይቀዋል፡፡

አዲሱን የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ የተመለከቱና ሰነዱ በቀረበበት መድረኮች የተገኙ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ የተደመጡ ሲሆን፣ ሰኞ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ሪሰርች ጌት በተሰኘው የጥናትና ምርምር ውጤቶች ገጽ ጽሑፋቸውን ያሠፈሩት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) አገር በቀል የተባለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቀረብ ብለው ሲመለከቱት የተባለውን ያህል እምብዛም አገር በቀል እንዳልሆነ፣ እንዲሁም የአይኤምኤፍ የታዳጊ አገሮች ማሻሻያ ሰነድ አንዱን እንደሚመስልና በቅርፅም ከዚያም እንደተቀዳ መረዳት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ይኼም የሆነው ማሻሻያ ሰነዱ በአገር ውስጥ ያሉ የኢኮኖሚ ችግሮችን ከመረዳት ስለማይጀምር ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህም የማሻሻያው ዳሳሰና ችግር ልየታ የተመሠረተው በተቀዳ ቅርፅ ላይ በመሆኑ፣ በመሬት ላይ ያሉ ጉዳዮችን አይዳሰስም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

‹‹ለአብነት ያህል የዕድገት ምንጭ በዋናነት የሀብት ክምችት እንደሆነ መገለጹ አሳሳች ነው፡፡ የሀብት ክምችት የዕድገት ድርሻ 1.6 በመቶ ብቻ እንደሆነና የጉልበት ሥራ 2.4 በመቶ፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂ አንድ በመቶ ብቻ ድርሻ እንደነበራቸው በእርግጠኝነት ይታወቃልና፤›› ሲሉም ሙግታቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይኼም የተሳሳተ ግምገማና የችግር ልየታ መንግሥት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውስጥ የተሳሳተ የትኩረት ሥፍራ እንዲመርጥ አድርጎታል፤›› በማለትም ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በዘለለም በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ ሰነዱ ዋና ዋና የዓብይ ኢኮኖሚ ችግሮችን ሳያካትት እንደቀረ ያመለክታሉ፡፡ የዘርፍ መዛባቶች በመኖራቸው የታለመው ዕድገት ከምግብ አቅርቦትና ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር ያልተጣጣመ መሆኑ እንደሚታይ፣ የልማት ፋይናንስ በውጪ ብድርና በበጀት ጉድለት እንደሚደጎም፣ እንዲሁም እርስ በርስ የማይጣጣሙ የመካከለኛ ጊዜና የዓመት ዕቅዶች መኖራቸው በሪፎርሙ አለመጤናቸውን አሳይተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን አገር በቀል የተባለውን ፖሊሲ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ሊመረኮዙባቸውን የሚገቡ መሠረታዊ ምንጮች ሳይለይ መፍትሔ ያቀርባል፤›› በማለትም ይተቻሉ፡፡

በተጨማሪም የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግሮት በመረዳት ረገድ ጉልህ ክፍተት እንደሚታይበት በማተት፣ ‹‹እነዚህን ለማስተካከል በሚል የቀረቡት ፖሊሲዎችም እንዲሁ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡

እሳቸው የመዋቅራዊ ችግሮች አናሳ የሰው ሀብት መኖሩ፣ በምግብ ዘርፍ የሚታዩ የምርታማነትና በውጭ አቅርቦት ላይ ጥገኛ መሆን፣ የወጪ ንግዱ ዘርፍ በአቅርቦት ችግር የተሸበበ መሆኑ፣ በገቢ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ መሆን፣ በውጪ የፋይናንስ ሀብት ላይ ጥገኛ መሆን፣ ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበት ፖለቲካዊነት እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

የማምረት አቅምንና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የገቢ መጠንና ሥርጭትን ማሳደግና ብሎም በምግብ ራስን መቻል፣ የገቢ ንግድ መቀነስና የውጭ ፋይናንስ ጥገኝነትን መቀነስ መፍትሔ ናቸው ይላሉ፡፡

ይኼንን ጉድለት ለማሻሻል ፖሊሲውን ከክፍተቶች አንፃር ዓይቶ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -