[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ቢሮ ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- አዲስ ነገር ከጠፋ ሰነባበተ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- በቃ ሁሉም ነገር ቀዝቅዟላ፡፡
- ምን ክረምቱስ ቀዝቃዛ አይደል እንዴ?
- ክረምቱን እኮ በበርካታ ነገሮች ማሞቅ ይቻላል ኑሮን ማሞቁ ነው የከበደን፡፡
- እ. . . .
- ክቡር ሚኒስትር ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆነ እኮ ነገሩ፡፡
- አልገባኝም?
- በቃ መንግሥትም ዝም አለ፡፡
- ስለምኑ?
- ስለኢኮኖሚው ነዋ፡፡
- መንግሥትማ ፖለቲካው ላይ ተወጥሯል፡፡
- እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- ኢኮኖሚው ከተያዘ ፖለቲካው ቁልቁለት ነው፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ይኸው አሁን እኮ ዳገት የሆነባችሁ ለዚያ ነው፡፡
- ምኑ ነው ዳገት የሆነብን?
- ፖለቲካው ነዋ፡፡
- ምን ይደረግ ብለህ ነው?
- ለኢኮኖሚው መልስ መስጠት ነዋ፡፡
- እኮ እንዴት?
- የራሳችሁን ሀብታሞች ፍጠሩ፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር የቀድሞዎቹን ገዥዎች ስትራቴጂ ረሱት እንዴ?
- ምን ነበር?
- ፖለቲካውን የተቆጣጠሩት ኢኮኖሚውን በመቆጣጠራቸው ነው፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- እናንተም ተመሳሳይ ስትራቴጂ ካልተከተላችሁ አትዘልቁትም፡፡
- ይቻላል ብለህ ነው?
- ለምን አይቻልም?
- አሁን ሁሉ ነገር ተለውጧል፡፡
- ምን ተለወጠ?
- ለውጥ የለም እያልከኝ ነው?
- በወሬማ ለውጥ አለ ነው የሚባለው፡፡
- በተግባር የለም እያልከኝ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ወሬውን ከተቆጣጠራችሁት ተግባሩ ችግር የለውም፡፡
- እንዲያውም ተግባር ከሌለ ወሬ ብቻ ማን ይቀበለናል?
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት እኮ ኃይል አለው፡፡
- ቢኖረውስ?
- ኃይል ያለው አሸናፊ ነዋ፡፡
- የመንግሥት ኃይል ሕዝብ መሆኑን ረሳኸው?
- እኔም እኮ የምልዎት እሱን ነው፡፡
- ምንድነው የምትለኝ?
- የራሳችሁን ሕዝብ ፍጠሩ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- የራሳችሁን ሀብታሞች መፍጠር ነዋ፡፡
- እ. . .
- በቃ የእናንተን ሐሳብና ፖሊሲ የሚደግፉ ሰዎችን መፍጠር አለባችሁ፡፡
- እ. . .
- ስለዚህ መንግሥትን ከኋላ የሚደግፉ ባለሀብቶችን መፍጠር ነው፡፡
- አሁን እንደምትለው ቀላል ነው ብለህ ነው?
- ምን ችግር አለው?
- እንቅስቃሴው ሁሉ ተዳክሟል እያልከኝ እንዴት ይቻላል?
- በአሁን ጊዜ በሥራ ባለሀብት መፍጠር አይቻልም፡፡
- ታዲያ በምንድነው የምንፈጥረው?
- በዝርፊያ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የወጣቶች መሪ ጋር ስብሰባ ላይ ተገናኙ]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም ነህ?
- ምን ሰላም አለ?
- ምን ሆንክ? ሰላም አይደለህም?
- አገር ታማ ሰላም አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እ. . .
- አገር ታማ እኮ ማንም ሰላም ሊሆን አይችልም፡፡
- አገር ሕመም ላይ ሳትሆን ለውጥ ላይ ናት፡፡
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ለውጥ ላይ ነን ነው ያልኩህ፡፡
- መቼ ነው ግን የምታምኑት?
- ምኑን?
- ችግራችሁን ነዋ፡፡
- የምን ችግር?
- አገሪቱ ከዚህ በላይ ምን ትሁን?
- አልገባኝም?
- ሕዝብ እንደዚህ ተጨንቆ እየኖረ እናንተ ለውጥ ላይ ነን ምናምን ትላላችሁ፡፡
- ታዲያ ለውጥ ላይ አይደለንም እያልከኝ ነው?
- መጀመርያማ መስሎን ነበር፡፡
- ማለት?
- ለውጥ አለ ብለን ሁሉን ነገር ለመስዋዕት አቅርበን ታገልን፡፡
- ትክክል ናችኋ፡፡
- አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- ለውጥ ላይ ሳንሆን. . .
- እ. . .
- ነውጥ ላይ ነን፡፡
- በቃ ወጣቶች ደግሞ ትቸኩላላችሁ፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሁሉ ነገር በአንድ ጀንበር እንዲለወጥ ነው የምትፈልጉት፡፡
- እ. . .
- የእናንተ ትውልድ እኮ ፋስት ፉድ የሚወደው ለዚህ ነው፡፡
- አልገባኝም?
- ሁሉን ነገር በአንዴ ይወለድ ነዋ የምትሉት፡፡
- ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ ወጣት እያለሁ እንደ እናንተው ነበርኩ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የእኔ ግንዛቤ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ጭራሽ መንግሥት ወጣቱን የረሳው ነው የሚመስለው፡፡
- እንዴት ይረሳዋል?
- ከፖሊሲ ጀምሮ በሁሉ ነገር የወጣት ዘርፉ የተረሳ ነው የሚመስለው፡፡
- እ. . .
- መንግሥት ወጣቱን የሚፈልገው ለአብዮት ብቻ ነው፡፡
- ምን አልከኝ?
- ክቡር ሚኒስትር ወጣቱ ለምትሉት ለውጥ ዋነኛ ሞተር ነበር፡፡
- እሱ መቼ ይካዳል?
- አሁን ደግሞ ወጣቱ ከመንግሥት የሚጠብቀው ነገር አለ፡፡
- ምንድነው?
- ዳቦ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ዳያስፖራ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- የት ነው የማውቅህ?
- ከዚህ በፊት አውሮፓ ተገናኝተን ነበር፡፡
- ዳያስፖራ ነህ?
- አዎን ክቡር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንደ አንተ ዓይነት ሰው በጣም ነው የሚያስደስተኝ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ የመደመር ሐሳቡ ገብቶሃላ፡፡
- ምን አሉኝ?
- ባይገባህ ኖሮ እንዴት ወደ አገርህ ትመለስ ነበር?
- መቼ ተመለስኩ አልኩዎት?
- ለመዝናናት መጥተህ ነው እንዴ?
- እሱማ አገሬን ለማገልገል ነበር የመጣሁት፡፡
- ታዲያ ምን ችግር ገጠመህ?
- ሁሉ ነገር ያስፈራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አይደለም፡፡
- ለውጥ ላይ መሆናችንን አትርሳ፡፡
- ወይ ለውጥ?
- በለውጥ ላይ ደግሞ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔም ለውጥ አለ ብዬ ነበር የመጣሁት፡፡
- አሁን የለም እንዳትለኝ?
- እንደሚወራለት አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መቼም ዳያስፖራዎች ስትባሉ አቃቂር ማውጣት ትችሉበታላችሁ፡፡
- እኔ አቃቂር እያወጣሁ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን እያደረክ ነው?
- እውነቱን እየነገርኩዎት፡፡
- ምንድነው እውነቱ?
- በቃ ክቡር ሚኒስትር ሲስተም የሚባል ነገር እኮ የለም፡፡
- የምን ሲስተም?
- በቃ ሁሉም ሰው በአቋራጭ መክበር ነው የሚፈልገው፡፡
- እ. . .
- ሲስተሙ ራሱ በሙስና ላይ ነው የተመሠረተው፡፡
- እሱን ነዋ ማስተካከል ያለብን፡፡
- ከሙስናው ባለፈ ደግሞ የዘር ፖለቲካው ሲጨመርበት አደገኛ ነው፡፡
- ምን አልከኝ?
- ብቻ ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡
- ተው እንጂ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በአንድ ጀምበር ሚሊየነሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡
- እ. . .
- በሥራ ሳይሆን በዝርፊያ ማለት ነው፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- የኢኮኖሚ ዕድገት ምናምን የሚባለውም ተራ ወሬ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ሁሉም ነገር የተሳሳተ መሠረት ላይ ነው ያለው፡፡
- እ. . .
- ሰሞኑን ለመኪኖች ፍጥነት መገደቢያ ማሽን ይገጠምላቸው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
- እኔም ሰምቻለሁ፡፡
- በየቀኑ ለሚፈጠሩት ባለሀብቶችም ሌላ ማሽን ሊገጠምላቸው ይገባል፡፡
- ምን ዓይነት ማሽን?
- የሀብት መገደቢያ ማሽን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- ምን ሆነህ ነው የምታዛጋው?
- እርቦኝ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምሣ አልበላህም እንዴ?
- ምን ነበር እሱ ነገር ክቡር ሚኒስትር?
- ተጨዋች ነህ እኮ አንተ፡፡
- የኑሮ ውድነቱ ነው ተጨዋች ያደረገኝ፡፡
- ፖለቲካህን ጀመርክ ማለት ነው?
- አሁን አሁን ሳስበው ፖለቲካው ሳያዋጣ አይቀርም፡፡
- እንዴት?
- ይኸው እኛማ ከዕለት ዕለት ኑሮ እያላተመን እንሰቃያለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባለሀብቶች እንደ አሸን እየፈሉ ነው፡፡
- ምን ታደርገዋለህ?
- ነገርኩዎት እኮ ፖለቲከኛ መሆን ነው የሚያዋጣው፡፡
- ነው ብለህ ነው?
- ስነግርዎት በአንድ ጀንበር ባለሀብቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡
- ፖለቲከኞች ናቸው እንዴ?
- እዚያው ካምፕ ውስጥ ያሉ ናቸው ሲለወጡ ያየነው፡፡
- አንተ መቼም የማታመጣው ነገር የለም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በሹፍርና ጠብ ያለልኝ ነገር ስለሌለ በቅርቡ ሥራ እለቃለሁ፡፡
- ለምን?
- አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም፡፡
- ምን የሚባል ፓርቲ?
- ኢችፓ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- የኢትዮጵያ ችጋራሞች ፓርቲ!