Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውዥንብር ተጭነን መድረሻችን የት ነው?

ሰላም! ሰላም! አዳሜ እዚህ በዳቦ ስምና በልዩ ጥቅም ይነታረካል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደ ነገረኝ እዚያ ማዶ ወደ ካናዳ ነው አሉ። አንድ ልጅ ተወለደ። ተወለደ ሲባል ወንድ ነው መባሉ አይደለም። ሴትም አልተባለችም። ፆታውን እንኳን እኔ ቤተሰቦቹም አያውቁም። ለምን አትሉም? አድጎ ራሱ ይወስን ተብሎ ነዋ። የራስን ልዩ ጥቅም በራስ የመወሰን መብት እኛን ብቻ የሚያቋስል መሰላችሁ እንዴ? ‹‹ገና ዓለም በሞላ በዚህ ነፃነት በሚባል ፀበል ይሁን ደም፣ ግራ በገባን ስያሜ አብጣ ባትፈነዳ ምን አለ ባሻዬ ትላለህ፤›› ሲሉኝ ሰነበቱ አዛውንቱ ባሻዬ። ዜናውን ያበሰረን እንደ ነገርኩዋችሁ የባሻዬ ልጅ ነው። ‹‹አሁን እስኪ በአዲስ ዓመት ጅማሬ ላይ ሆነን ይኼን ወሬ ብለህ ታወራዋለህ?›› ስለው ባሻዬ፣ ‹‹ምኑን ተኖረ አንበርብር። ደግሞ ከዚህ ወዲያ ኑሮ ነው? ከዚህስ ወዲያ ብሞትም አይቆጨኝ፤›› ብለው ተነሱ ተቀመጡ። እንዲቺው ሲንጎራደዱ ዶፍና ብርድ ከች አለ። እዚያው በቅዝቃዜ ውስጥ ሆነን ነገር እየጠበስን በዓለም ጉዳይ መጠበሳችንን ቀጠልን።

‹‹አሁን እስኪ ፆታውን እያዩት ‘ዩ’ ይሉታል?›› አለ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ምን አሉት?›› አሉ ባሻዬ። ‹‹ዩ የሚለውን ፊደል ሰጡት፤›› ልጃቸው መለሰ። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ባሻዬ አሰገጉ። ‹‹አንኖውን ‘ወይም ያልታወቀ’ ለማለት ነው. . .›› ሲላቸው እንደ መኮሳተር ብለው ቆዩና ከት ከት ብለው ሳቁ። ‹‹አገሬ ገና ምኑን ዓይተሽ? ዛሬ በሰው ስም፣ በአደባባይ ስም፣ በብሔር ስትነታረኪ ነገ ደግሞ የፆታን ዕድል በራስ የመወሰን አዋጅ እናፅድቅ አናፅድቅ ብለሽ ትዘቅጪ ይሆናል፤›› ብለው ከወትሮው የእንቅልፍ ሰዓታቸው ቀደም ብለው አልጋቸው ላይ ወጡ። እንደ አወጣጣቸው ከሆነ ተመልሶ ለመውረድ ምንም ፍላጎት አልታየባቸውም። እግዜር ሲያሸክም ሰው አልችል አይልም ሆነና ነገሩ፣ ባሻዬ ማልደው ተነስተው ቤተ ክርስቲያን መሳማቸውን ልጃቸው በነጋታው በቴክስት ነገረኝ። ዕፎይ አልኩ። ምን ይባላል ታዲያ!

መቼስ ከዚህ በላይ የዘመን ማለቂያ የለም። የዚህን የፆታን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ጉዳይ እንግሊዞች ሰምተው (እነሱ እንደሆኑ አንዴ ነገር ሲይዙ አይለቁም) ለሦስተኛ የፆታ መደብ፣ ማለትም ያልታወቀ ያልተገለጸ ለሚለው ልዩ የመታወቂያና የፓስፖርት መደብ መዘጋጀት ይኖርበታል ሲሉ አፍታ አልቆዩም አሉ። ታዲያ ይኼን ሰምቶ አንድ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ጠባቂ ወዳጄ፣ ‹‹ምናለበት እነዚህ ብልፅግናቸው ኤክስፓየርድ ያደረገ አገሮች እንዲህ ዓይነቱን ዜና ከእኛ ቢደብቁት? እነሱ ኖረው ጨርሰው ነው። እኛ ገና መኖር ልንጀምር ነው። ‘ፌር’ አይደለም፤›› ብሎ አለቃቀሰብኝ። እንደ ዘንድሮ ዕንባና ዝናብ ቅጥ ያጣ ነገር አላየንም። ዓይንም የማያየው ጆሮ ማይሰማው የለም ቢባልም፣ አንዳንዴ አባባሉና አፈጻጸሙ ለያዥ ለገናዥ ያስቸግራል። ለመንግሥትና ለሕዝብም እንደዚያ መሰለኝ።

አሁን አሁን ሳስበው ባሻዬ ወደውም አይደለ አዘውትረው፣ ‹‹ከምታዩትና ከምትሰሙት ተጠበቁ ይላል መጽሐፉ. . .›› የሚሉኝ እላለሁ። ዘመነ ኢንተርኔት በየት በኩል። እንዲያውም አንዳንዴ ለማትሪክ ፈተና ሞጭላፊዎች ምሥጋና ይግባና (ብለን ብለን ለዚህ በቃን) የኢንተርኔት ‹ብሬክ› በዓመት በዓመት ባይኖረን ምን እንሆን ነበር? እውነቴን እኮ ነው። ጉዳ ጉዱ በዚህ ከቀጠለ በራሳችን መልካም ፈቃድ ‹ኢንተርኔት ይታሸግ› ብለን አደባባይ እንዳንወጣ እፈራለሁ። አለበለዚያ ግን ገና የመኖሪያ ቤት እጥረት ሳይወገድ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምና አከፋፈል ማስተር ፕላን ጉዳይ እንደ ካናዳ ያወዛግበን ከጀመረ፣ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ብለን የምናልፈው አይመስለኝም። እስኪ አስቡት ወደፊት ከተማችን ከየቤታችን የሚወጣውን ቆሻሻ በቅጡ ሰብስባ፣ በዓመት በዓመት በሺዎች በምታስመርቃቸው ምሁራን ልጆቿ ዕርዳታ ‘ሪሳይክል’ ከማድረግ አልፋ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ስትገነባ፣ የወንድ ነው የሴት? ወይስ ያልታወቀ ብላችሁ በር ስታንኳኩ? ሰው አለ ነው ሰው የለም መልሱ? አያድርስ ብለን እለፈው መሰለኝ!

እና እላችኋለሁ፣‹‹እሳት ከነደደ አመድ መች ይገዳል፣ እንዲህ ነው ሰው ሁሉ አጥፊውን ይወዳል፤›› ይባል ነበር አሉ ድሮ በአገራችን። አሁንማ ከቅኔና ከዓላማ ወደ ድለቃና ሽብር፣ ጥበብ ሳትቀር ፊቷን አዙራ በየት ብለን ቁምነገር እንሰማለን? ለነገሩ የሥራው ፀባይ ነው። “እንዴት?” አላችሁ። ጎሽ! ምነው ሁሉም እንደ እናንተ ሐሳብ ሳያስጨርስ ገና ለገና ለኮሜንት የተሰጠኝ ቦታ እያለ በፍረጃና በስድብ ጀምሮ ባይቋጭ። እውነቴን እኮ ነው! ‹‹ካልተደራጁ ወይ ካልተዛመዱ፣ ወይም የጥቅም አጋር ካልተሆነ ገና ለገና በዜግነት ብቻ ባዶ ቦታ በቀላሉ ስለማይሰጥ፣ ወገኔ ቁጭቱን በፌስቡክ ርስቱ ላይ መወጣት ተያይዞታል’ ነው የሚባለው፤›› ብዬ አንድ ወዳጄን ባወራው (ሲባል ነዋ የምሰማው)፣ ‹‹ፌስቡክ አትጠቀምም እንዴ?›› ብሎ ዞረብኝ። እኔ እኮ! ይህች መጠቀም የምትባል ነገር የማትገባበት ቦታ የለም በቃ? የምር! ለነገሩ ያለ መጠቃቀም ዘንድሮ ምንም ዓይነት ቦታ ላይ መቀመጥ፣ መቆም ወይም መወሸቅ አዳጋች ሆኗል። ታዲያ ይኼ ወዳጄ እኔን ‘ፌስቡክ’ የማይጠቀመው እንዳሻው እንዲቆርሰውና እንዲቆፍረው ያላግባብ የተሰጠው ቦታ ቢኖር ነው ብሎ ጠረጠረኝ።

‘በምን አወቅክ መጠርጠሩን?’ ብትሉኝ ሄዶ ‘ፌስቡኩ’ ላይ፣ ‹‹በአገሩ ባለርስቱ ጥቂት፣ ያውም ደላላ መሆኑን ‘ፌስቡክ’ ላይ በማየው ግፊያ አስተዋልኩ፤›› ብሎ መለጠፉን መጥተው ነገሩኝ። አቤት የፀብ አጫሪው ብዛት። እውነቴን ነው የምላችሁ ዘንድሮ እኮ እንደ ፀብ አጫሪው ብዛት ቢሆን ውሎአችን አጥፍቶ ማጥፋት መሆን ነበረበት። ግን ‘እሱም አውቆ ሰማይን አርቆ’ ሆኖ ነገሩ ንቆ ማለፍን ከየ ነፍሳችን ጋር ሰፋት። ይኼን ጊዜ የዘመኑ ቁምነገር በሚገባ ይከሰታል። ‘መተላለፍ ብሎ ነገር የለም’ ብለው በነፍስ የሚፈልጉን በዙ እኮ። ወሬው፣ ሐሜቱና ትችቱ በአጠቃላይ ሁለ ነገራችን ስለታጣቂዎችና አስታጣቂዎቻቸው፣ ስለማክረርና መበጠስ ሆነና አረፈው። ታሪክ በአሸናፊው እጅ ሲጻፍ ይኼው ዓለም እንደ ገልቱ ማኅበረሰብ እርፍና ማጭዱን ጥሎ፣ አፉን ደም ደም እስኪለው ስለጥፋት እያሰበና እያወራ ውሎ ማደር ጀመረ። እህ የት ይኬዳል?

ጊዜው እንደሚታወቀው ቤት ፈላጊ የበዛበት ነው። አንገት ማስገቢያ ጎጆ ከሚፈልገው እስከ ምቾት ያለው ቪላ ፈላጊ እኔ ዘንድ አይጠፉም፡፡ ይኼንን የቤት ችግር ለዓመታት ስለሰማሁ ውስጤ ሁሌም እንደ ጮኸብኝ ነው፡፡ ግን የደላላ ነገር ሆኖ እንጀራ መብያዬም ነው፡፡ ቤት ፍለጋ ላይ ታች ስል ጉድ ቆጠራ የተሰማራሁ ይመስል የማላየው ነገር አልነበረም፡፡ ቤት ፍለጋዬ ያተኮረው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ነው። ባለ አንድ መኝታ ሦስተኛ ፎቅ ላይ አለ ብለውኝ ለማየት እየወጣሁ፣ ሁለተኛው ደረጃ ላይ ስደርስ ‘ብሶት የወለደው ጫት ቤት’ የሚል ጽሑፍ ተመለከትኩ (መቼም አንዴ ጉድ አይጣችሁ የተባልን እኮ ነን)፡፡ አብሮኝ የነበረውን ሰው፣ ‹‹ምንድነው ይኼ?›› አልኩት እያየሁት እንደማያይ ሁሉ። ‹‹ጫት ቤት ኮንዶሚኒየም ላይ?›› ስለው፣ ‹‹ያውም ‘ብሶት የወለደው’ ነዋ!›› ብሎ ሊያሾፍብኝ ቃጣው። ፀሐዩ መንግሥታችን ያላየው (ምናልባት እያየ ያላየው) ጉድ ትላላችሁ፣ ከዚህ በላይ ምን አለ? ታዲያ እኔም አፌ አያርፍ ምን ስል ጠየቅኩ መሰላችሁ? ‹‹ኢሕአዴግ አገር እያስተዳደረ ዝም አለ በእውነት?›› ብለው፣ ‹‹ምን ይላል ይኼ ሰው? ከድህነት ወጥቶ ብልፅግና ውስጥ የገባ ምን ግድ ይለዋል?›› ብሎ ያ አብሮኝ ደረጃ የሚወጣው ሰው ተበሳጨብኝ። ‹‹አባባሌ ‘ብሶት የወለደው’ መባሉን ማለቴ ነው?›› ብዬ ብጠይቀው መልሼ፣ ‹‹እሱ ምን ግድ አለው ለእንዲህ ያለው ብሶት? በፊት ጫት የሚያስቅም ብሶት ሳይሆን ጫካ የሚያስገባ ብሶት ነው ቀልቡን የሚስበው፡፡ አሁን ደግሞ ከሀብታሞች ጋር እየዋለ ነው መሰለኝ ምቾት ብቻ ነው የሚታየው›› ሲለኝ፣ ጥያቄና መልሳችን ወዳልተፈለገ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እየተለወጠ በመሄዱ አቆምኩት። አገር ምድሩ ብሶት ሆኖም አይደል እንዴ ጎበዝ?!

በሉ እንሰነባበት። የቤትና ቤተኛው ወሬ ፍሪዳ ሊያስጥል ደርሷል። የቀናው ሊቀናው ያልቀናው በተራው እንቁልልጩን ሊጫወት ዛሬ መሽቶ ነገ ይነጋል። ተስፋ ካለ ሌላ ምን ይጠፋል? እንኳን እዚህ ደርሰን ድሮም በላሞቻችን ተማምነን ከደመና በላይ ወተት ያረጋን ነን። በቀደም የጣለው በረዶ እሱ ነው አሉ። እርጎ በበረዶ መልክ መገለጹ ለአዲስ አበቤ ቤት የለሽ የስቃዩ ግርሻ ሆኖ ይቆጠር ሲሉ ሰምቼ ሳቅ ትን እያለኝ ሰነበትኩ። ይኼው አሁን ደግሞ ብርዱ ደጅ አላስወጣ ብሎ እኔና የባሻዬ ልጅ አባቱ ዘንድ ማምሸት ጀምረናል። ማንጠግቦሽ አንዳንዴ ትቀላቀለንና በቆሎ ትጠብስልናለች። እና ባሻዬ እንደለመዱት ከእጃቸው የማትለያቸውን ሬዲዮናቸውን ይዘው ወሬ ያዳምጣሉ። በሳይንቲስቶች ዓለም እጅግ ብዙ ዓመት የፈጀ ጥናት ይፋ ሆነ ሲል፣ ባሻዬ ‘ቆይ!’ ብለው ጆሯቸውን ቀሰሩ። ‹‹ጥናቱም ለእንቅልፍ ዕጦት ሁነኛ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን ይፋ አድርጓል. . .›› ሲል ሬዲዮኑ ባሻዬ በሸቁ።

‹‹እኛ መንቃት እንጂ መተኛት አላቃተን። እነዚህ ሚዲያዎች ዘንድሮ ምን ነክቷቸዋል? እንደ ጀማሪ ልብስ ሰፊ ሲሰፋን እያጠበቡ፣ ሲጠበን እያሰፉ የውዥንብር ጭነት የሚጭኑብን በጤናቸው ነው? እኛስ የምንነዳላቸው ምን ሆነን ነው?›› ብለው ተቆጡ። ‹‹ይኼ እኮ ዓለም አቀፋዊ ጥናት ነው አባ፤›› ሲላቸው ምሁሩ ልጃቸው፣ ‹‹ወይድ! እኛ ዓለም ላይ መቼ ደረስን? ደርሰናል እንዴ? ንገረኝ እንጂ። እኛ ገና የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት ዕዳ ያልከፈልን፣ ደግሞ ከዚህ ብሶ በሰሞነኛ የፖለቲካ ፋሽን በዘርና በነገድ የምንዳቆስ፣ በስያሜ እሰጥ አገባ የማንግባባ ነን። ዓለም ይለኛል እንዴ? ዓለም እንቅልፍ ያጣው ጣጣውን ጨርሶ ነው። በልተው፣ ጠጥተው፣ ዘፍነው፣ ሠርተው፣ አፍርሰው ሲያበቁ የሚያደርጉት ሲጠፋቸው ‘ኑ ሦስተኛ ወገን ፆታ እንፍጠር’ ከማለት ደረሱ። ይኼ እንቅልፍ ነሳቸው። እኛ እኮ ገና አልነቃንም። እንዴ!›› እንዳሉ ዘለው አልጋቸው ውስጥ ገቡ። አውቆ የተኛ ሆኖብን ነው? ወይስ የእውነት አልሰማ ብለን ይሆን ይኼን ያህል ያንቀላፋነው? የሚለውን ጥያቄ ሳምንት ብንመለስበትስ? እስከዚያው ባሻዬ እንዳሉት በውዥንብር ጭነት በጅምላ አንነዳ ብንልስ? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት