Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ጎፋ ማስቃላ ዮ››

‹‹ጎፋ ማስቃላ ዮ››

ቀን:

በጎፋ ብሔረሰብ በሰፊው ከሚከበሩ በዓላት አንዱ መስቀል ነው፡፡ ጎፋዎች የበዓላት አውራ ይሉታል፡፡ ለብሔረሰቡ መስቀል የአዲስ ዘመን መግባትን አብሳሪ ነው፡፡ መስቀል የተጣላ የሚታረቅበት፣ ሰላም የሚወርድበት፣ ያዘነ ሐዘኑን የሚረሳበት፣ የእርቀ ሰላም ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት በዓል ነው፡፡

‹‹ጎፋ ጋዜ ማስቃላ›› እየተባለ በድምቀት የሚከበረው ይህ ዓመታዊ በዓል፣ በፊት ለ15 ቀናት ይከበር ነበር፡፡ አሁንም ለ15 ቀናት ባይሆንም የአካባቢው ተወላጆች አደባባይ ወጥተው ‹‹ማስቃላ ዮ›› እያሉ ለተከታታይ ቀናት ሞቅ አድርገው ያከብሩታል፡፡ ‹‹ማስቃላ ዮ›› እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሰን እንደ ማለት ነው፡፡ የዘንድሮው መስቀል በዓልም በሳውላ ከተማ በደማቁ ተከብሯል፡፡

ለጎፋዎች የመስከረም ወር (ብሔረሰቡ ቋንቋ ጉስታማ ይባላል) የጭፈራና የደስታ ወር ነው፡፡ በዓሉን ለማክበር ከመስከረም 1 ጀምሮ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ለዚህም ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወንዶች የእርድ በሬን ለመግዛት ዓመቱን ሙሉ ሲቆጥቡ፣ ሴቶች ደግሞ ቡልኮ ለመሥራት ዓመቱን ሙሉ ኡጋሪ የሚባል ጥጥ ይፈትላሉ፡፡ የደመራው እለት እየተቃረበ ሲመጣም፣ ወንዶች ለደመራ የሚሆነውን የተመረጠ እንጨትና ለከብቶች መኖ ያዘጋጃሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕፃናትም በዚህ በዓል ‹‹ሎያ ባይ ሎያ ባይ

ሎያ ማስቃላ ባይ

ማስቃላ ኡፋይስ ላይ

ሙሲናይ ሀሹ ባይ›› እያሉ የመስቀል መምጣት የእነሱም ደስታ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ይህን በዓል ልዩ የሚያደርገው የተጣሉ ሰዎች ሳይታረቁ በዓሉን በፍፁም አለማክበራቸው ነው፡፡ መስቀል እርቅ የሚወርድበት ነውና እንኳን ሰው ባላንጣዎቹ ‹‹እንሽላሊትና እባብም አብረው ያድራሉ›› ይባላል፡፡

በጎፋ በዓመት አንዴ የመስቀል ችቦ ከተለኮሰ በኋላ ሐዘን የለም ይባላል፡፡ የበዓሉ ዕለት ለሞተ ሰው እንኳ አይለቀስም፡፡ ከደመራ በኋላ የማስረሻ ጭፈራ እየተጨፈረ፣ ለቀስተኛ በር ላይ ይዞራል፡፡ ሐዘን ይብቃ ተብሎም ይበሰራል፡፡ ሟቹ በመስቀሉ እሳት ተወስዷል ይባላል፡፡ ለቀስተኞችም ለቅሶውን አቁመው ‹‹መስቀላ ዮ›› እያሉ በዓሉን ማክበር ይቀጥላሉ፡፡ ይኼ ሥርዓት ሐዘናቸውን እንደሚቀንስ ተወላጆቹ ይመሰክራሉ፡፡

በጎፋ ብሔረሰብ ለመስቀል በዓል ለምግብና መጠጥ አዘገጃጀት የሚሰጠው ትኩረት ከሌሎቹ በዓላት ለየት ያለ ነው፡፡ ለመስቀል ተብሎ የሚወጣው ወጪ ለነገ የማይባል፣ ያለውም የሌለውም ሳይሳሳ የሚያወጣበት ነው፡፡

ከዋና በዓሉ በፊት የሚገኘው የደመራ ሥነ ሥርግት ትልቅ መልዕክት ያዘለ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት ከየቤተሰቡ አባት ወይም ታላቅ ልጅ ለችቦ የሚሆኑ የደረቁ ቀጥ ቀጥ ያሉ የችቦ ጭራሮዎችን ያዘጋጃል፡፡ ቀጥ ያሉ መሆናቸው ተምሳሌትነቱ ዘመኑ መልካም እንዲሆን፣ ከበሽታና ከመቅሰፍት እንዲጠበቅ፣ ልጆችም በአስተሳሰብና በአመለካከት ቀና እንዲሆኑ የማኅበረሰቡ መልካም ምኞት ነው፡፡ የሚጠቀሙትን የእንጨት ዓይነት ሶልዜ ይሉታል፡፡ ዋናው ትልቁ የደመራ እንጨት እርጥብ መሆን አለበት፡፡ ይህም ዘመኑ የጥጋብና የሰላም እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት የሚገልጹበት ነው፡፡ በደመራው እንጨት ጫፍ ላይ የሚታሰረው አደይ አበባ ደግሞ ተስፋ፣ ውበት፣ ዘር መኖሩንና የደመራው ሥነ ሥርዓት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ስለመሆኑ መልዕክት የሚተላለፍበት ነው፡፡ የችቦ አስተሳሰር እንደ ቤተሰቡ ቁጥርና ዕድሜ ይወሰናል፡፡ ይህም በመካከላቸው መደማመጥና መከባበር እንዲሰፍን ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡

በዚህ የደመራ ሥነ ሥርዓት ላይ ሴቶች አይሳተፉም፡፡ ሴቶቹ በደመራው ዕለት ገንፎ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ይላሉ፡፡ ገንፎው ከወተት፣ ከተነጠረ ቅቤ፣ ከአይብና ከበቆሎ ዱቄት የሚዘጋጅ ነው፡፡ ይህ ገንፎ ከተዘጋጀ በኋላ በአንድነት በመሰብሰብ እጃቸውን ወደ መሶቡ የሚሰዱበት ሥርዓት ከምንም በላይ ፈጣሪያቸውን የሚያስቡበትና የሚማፀኑነበት ነው፡፡ በሰፊ ማዕድ የሚቀርበውን ገንፎ ‹‹ማስቃላ ዩ›› እያሉ በጋራ ይቃመሱታል፡፡

የገንፎው ሥነ ሥርዓት ከደመራው ቀጥሎ የሚከናወን ነው፡፡ የችቦ አለኳኮሱ ለየት ያለ ነው፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ቀኑ ደንገዝገዝ ወይም ለዓይን ያዝ ሲል አባወራው በወንድ ልጆች ቁጥር ልክ የተከለውን ችቦ በመያዝ ምሰሶ ካለበት ጎጆ ቤት ውስጥ በመግባት ለገንፎ ከተጣደው ድስት ሥር ከሚነደው እሳት ሁሉንም ችቦዎች ይለኩሳል፡፡ ከለኮሱ በኋላ በቀኝ በኩል በመታጠፍ ምሰሶውን በመዞር የከብቶች ጋጣ እንዲሁም በቀኝና በግራ የቆሙትን ግርግዳዎች ‹‹ማስቃላ ዮ›› እያሉ በተለኮሰው እሳት እየነካኩ ወደ ደጅ ይወጣሉ፡፡

አባትም ማስቃላ ዮ እያለ ችቦውን በዕድሜ ደረጃቸው ካካፈለ በኋላ መሀል ላይ በመሆን በወንዶች ታጅበው ‹‹ማስቃላ ዮ ዳናው ዳና›› እያሉ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ አባት በመጀመሪያ ችቦውን ካስቀመጠ በኋላ ቀጥሎ ልጆች በዕድሜያቸው መሠረት ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ፣ ይጨፍራሉ፡፡ ችቦ ሲታሰርና ደመራው ሲተከል ከወንድ ልጆች መካከል በዕለቱ መገኘት ያልቻለ ቢኖር፣ የለም ተብሎ ደመራው ሳይወጣለት አይቀርም፡፡ ለሌሎች የሚደረገው በሙሉ ለእርሱም ይደረግለታል፡፡

ደመራው ከተለኰሰ በኋላ ማስቃላ ዮ! ዮ! እያሉ ወደ ቤት ተመልሰው ከእናት ከእህቶቻቸውና ከባለቤቶቻቸው ጋር ማስቃላ ዮ ከተባባሉ በኋላ እንደገና ችቦዎቻቸውን በመያዝ በባህላዊ መሪ ወደ ተተከለው ደመራ ቦታ ያመራሉ፡፡ እዚያው ማስቃላ ዮ እያሉ በባህላዊ መሪው ተመርቀው ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ባህላዊ መሪው የአገሩ ባላባት ‹‹ቢታ ብታንቴ›› ናቸው፡፡

ቢታ ቢታንቴ ማለት በአካባቢው ባለአባት (ባላባት) የዚያ ቀበሌ የመሬት አስተዳደርና ባህላዊ መሪ እንዲሆን የተመረጠ ወይም የተሾመ ሰው ማለት ነው፡፡

አሁን ላይ ያለው ንጉሥ ዓለማየሁ አደሴ ሲሆን፣ ለ12ተኛ ጊዜ የነገሠ ሰው እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የአነጋገሥ ሥርዓቱም እስኪሞት የሚዘልቅ ነው፡፡ ሲሞት ልጁ ወይም ታላቅ ወንድሙ ይነግሣል፡፡

ከአያት ቅድመ አያቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ይህ ሥርዓት፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አለው፡፡ ንግሥናውን የሚሰጡት ሞሬና የሚባሉ አንጋሾች ሲሆኑ፣ ንጉሡ ሊሞት ሲል ዘውዱን ወስደው በእንሰት ቅጠል ላይ ያኖሩታል፡፡ ቀጥሎም ንጉሡ ሲሞት በጊዜያዊነት በተዘጋጀ ዳስ ውስጥ ቀጣይ የሚነግሠውን  ተሸክመው ያስገቡትና እዚያው ዳስ ውስጥ የንግሥና ሥርዓቱን ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ቦርዴ የሚባል ባህላዊ መጠጥ ይጠጣል፡፡ ላምና ጥጃም በስጦታ መልክ ይሰጣል፡፡

ይህ ንግሥና ከመስቀል በዓል ጋርም ተያያዥነት አለው፡፡ የመስቀል በዓል ሲመጣ የተጣላና የተኳረፈ፣ የተጋደለም ይቅር ይባባላል፡፡ ይህም የሚሆነው አዲስ ዓመት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በማኅበረሰቡ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ቢታብታንቴ  የተጣሉ እንዲታረቁ ስለሚያስገድዱም ነው፡፡ ቢታ ብታንቴ ለማስታረቅ ሞክረው አሻፈረኝ የሚል ሰው በዚያው ዓመት ውስጥ ይሞታል የሚል እምነትም አለ፡፡ የዕድሜ ልክ ንግሥና የሚሰጣቸው ብታ ቢታንቴ አናታቸው ላይ ኮለቻ የሚባል ዘውድ ይደፋሉ፡፡

ከደመራ ሥነ ሥርዓቱ ጎን ለጎን እርዱ ይካሄዳል፡፡ እርዱ የሚከናወነው በአንድ ትልቅ ሰው ደጃፍ ላይ ነው፡፡ በእርዱ ሥነ ሥርዓት የእንሰት ቅጠል እንደ ሸራ ይነጠፋል፡፡ ይኼም የሚደረገው ዓመቱ እርጥብ እንዲሆን በመመኘት ነው፡፡ የእንሰት ጉዝጓዝ ላይም ሥጋው ተመድቦ የዓመት ሰው ይበለን ብለው በመመራረቅ ሥነ ሥርዓቱን ፈጽመው ይወጣሉ፡፡   

የጎፋ ብሔረሰብ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ካሉ 56 ብሔረሰቦች አንዱ ነው፡፡ ብሔረሰቡ የሚገኘው በደምባ ጎፋ ገዜ ጎፋ፣ በዛላ፣ በዑባ ደብረ ፀሐይ፣ በመሎ ኮዛ፣ መሎ ገዳ፣ በሳውላና ቡልቄ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በአጎራባች በምትገኘው ኦይዳ ውስን ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡

ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ516 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከክልሉ መቀመጫ ከሐዋሳ በ288 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጎፋ ዞን፣ የራሱ የሆነ ቋንቋና የባህል እሴቶች አሉት፡፡

የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮ የተመሠረተ በግብርና ኢኮኖሚ ላይ ነው፡፡ የተለያየ ምርቶችን ያመርታሉ፡፡ ከአገዳ ሰብሎች በቆሎና ማሽላ በስፋት ሲመረት በተለይ በበቆሎ ምርቱ ታዋቂ በመሆኑ ‹‹የበቆሎ እምብርት›› የሚል ስያሜ ተሰቶታል፡፡ ከሰብሎች ስንዴ፣ ገብስና ጤፍ፣ ከጥራጥሬ ሰብሎች ደግሞ ባቄላ፣ አተር፣ ቦሎቄና የተለያየ የጓሮ አትክልት ይመረቱበታል፡፡

የተለያየ ሰው ሠራሽ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች በጎፋ ዞን ይገኛሉ፡፡ ወንቧ ፏፏቴ፣ ሲርሶ ደን፣ ቦምቢ ዋሻና ፏፏቴ፣ የኢሊሊ ካዎ ቅሪት አካል፣ ግንድ አንሳው መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንዲሁም ሰሎ ሆምኦ (ጎሬ) ዋሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የጎፋዎች ቀደምት አባቶች የጣሊያንን ጦር በመስዋዕትነት ለመመከታቸው ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የሚለብሱት ባህላዊ ልብስ ላይ ሃያ ሃያ የሚሉትን ባለቀይ ቀለም ጥለት ይጠቀማሉ፡፡

ባህላዊ ልብሳቸው ላይ ቀይ ቀለም ተደርጎ ከታች ነጭና አረንጓዴ የከተላል፡፡ ነጩ ሰላምን ሲያመላክት፣ አረንጓዴው ደግሞ የብሔረሰቡ አምራችነትና የአካባቢው አረንጓዴ ተፈጥሯዊ አቀማመጥን ይወክላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...