Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኤጀንሲዎች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰጡት መረጃ ከመደራደሪያነት የዘለለ ፋይዳ አላመጣም አሉ

ኤጀንሲዎች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰጡት መረጃ ከመደራደሪያነት የዘለለ ፋይዳ አላመጣም አሉ

ቀን:

‹‹ሕጋዊነትንና ሕገወጥነትን እያጣቀሱ የሚሠሩ ኤጀንሲዎች አሉ››

ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

‹‹በሕገወጥ ደላሎች የሚላኩ ሠራተኞችን አንቀበልም››

በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር

በኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ሰጪ ኤጀንሲዎች ማኅበር በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ላይ የሚያገኘውን መረጃ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት እየሰጠ ቢሆንም፣ መረጃው ከግል ጥቅም መደራደሪያነት የዘለለ ፋይዳ አለማምጣቱን አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ ይህንን የተናገረው ላለፉት ስድስት ዓመታት ታግዶ የቆየው የውጭ አገሮች ሥራ ሥምሪትን የሁለትዮሽ የሥራ ሥምሪት ውል በፈጸሙ አገሮች፣ በቂ ሥልጠና የወሰዱ የቤት ሠራተኞችንና በሌሎች የሥራ ዘርፎች የሠለጠኑ ሠራተኞችን ለመላክ መፈቀዱን አስመልክቶ በስካይ ላይት ሆቴል መስከረም 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባዘጋጀው የማሳወቂያ ዝግጅት ላይ ነው፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ ማኅበራቸው ሕጋዊ የሥራ ሥምሪት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል፣ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡ ዜጎች መብታቸው፣ ደኅንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች ሲወጡ ማኅበራቸው ግንባር ቀደም ግብዓት ሰጪ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ለማስፈጸም ሥልጣን ከተሰጠው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም በትብብር የሚሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ላይ ችግር ፈጣሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ የመንግሥትና የአገርን አደራ ለግል ጥቅማቸው የለወጡ ጥቂት ህሊና ቢስ የመንግሥት ሠራተኞችና ደላሎች ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ከልክሎ እያለ ሁለቱ አካላት በመቀናጀትና በመናበብ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትና በተለያዩ ኤምባሲዎች ደጃፍ ላይ በሠልፍ ተራ ይዘው የሚመለመሉትንና ከአገር የሚወጡትን ዜጎች ማየት በቂ ምሳሌ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ማኅበሩ ለሕገወጥ ደላሎችና አጋሮቻቸው እኩይ ተግባር ሳይንበረከክ ከመንግሥት ጎን በመቆም እንደሚታገላቸው ጠቁመው፣ ለመንግሥት የሚያቀርቡትን መረጃ በመውሰድና ለመደራደሪያነት ከማዋል ባለፈ ማስፈራሪያዎች ሳይቀሩ እንደሚደርሷቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሠራተኞችን እንደሚወስድ ተስፋ የተጣለበት የሳዑዲ ዓረቢያ የሥራ ሥምሪት በሚጠበቀው ደረጃና ባዘጋጁት የሠለጠነ የሰው ኃይል ልክ የተመጣጠነ ቪዛ ባለመለቀቁ ሥጋት ቢገባቸውም፣ በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር በኩል ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የኤጀንሲው ጥያቄ በሳዑዲ ዓረቢያ በኩል የሚፈልጉትን ያህል ቪዛ አለመለቀቁና የኤጀንሲ ባለቤቶች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መግባትና መውጣት የሚችሉበት ፈቃድ አለመስጠት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ሕጋዊ ፈቃድ ይዘው ወደ ዘርፉ የተቀላቀሉ ኤጀንሲዎች ሕጋዊ አሠራርን በመከተል መሥራት፣ ለሕግ ተገዥ መሆን፣ ለአገር፣ ለዜጎችና ለራሳቸው የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ቃል መግባታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ከተቀባይ አገሮች ጋር በሚደረጉ የገበያ ዋጋ ስምምነቶች ላይ ማኅበሩ የሚከተለው አቅጣጫ የዜጎችንና የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን በመረዳት፣ ከገበያ ዋጋ በታች ወርዶ በመሥራት የግል ጥቅምን ብቻ ማዕከል ካደረገ ሩጫ መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

መንግሥት በሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ግልጽና ሥውር እጆችን አደብ ለማስገዛት ይችል ዘንድ፣ የወጣውን አዋጅ የሚያስፈጽሙ አካላትና ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ተቀናጅተው እንዲሠሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለዘርፉ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡላቸው ጠይቀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የፌዴራል ፖሊስ ተወካዮች፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች ሲሆኑ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ሥራ ሥምሪት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ ሚኒስትሯን ወክለው ንግግር አድርገዋል፡፡   

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ በዜጎች ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ችግር በመመልከት መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት የውጭ ሥራ ሥምሪትን አስቁሞ ነበር፡፡ መንግሥትና የኤጀንሲዎች ማኅበር ባደረጉት ትኩረትና ግፊት፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈርሞ መላክ እንደተጀመረ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ማኅበሩን አመሥግነዋል፡፡ የኤጀሲዎች ቁጥር ትንሽ በመሆኑ አስፈላጊውን መሥፈርት የሚያሟሉ ኤጀንሲዎች እንዲጨመሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከመንግሥት ጋር በመተባበርም ሕገወጦችን መታገል እንዳለባቸው ጠቁመው፣ አሁንም ሕጋዊነትና ሕገወጥነትን እያጣቀሱ የሚሠሩ ኤጀንሲዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ያለ ምንም ርኅራኄ ሕጎችንና ደንቦችን ተፈጻሚ እንደሚያደርግ በማስጠንቀቅ፣ በሕግና ሕግ ብቻ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተሳተፉ በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ሚስተር ሳሚ ጃሚል አብዱላህ እንደተናገሩት፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢትዮጵያ ካላቸው የዘመናት ግንኙነት አንፃር በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በመመደባቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ የቤት ሠራተኞች፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የሚፈለጉት ሠራተኞች የቤት ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የሠለጠኑ በርካታ ሠራተኞች እንደሆኑም አክለዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሕጋዊ እንዲሆንና የሁለትዮሽ ስምምነት እንዲፈረም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) አመሥግነዋል፡፡    

ሠራተኞችን የሚመለምሉና የሚልኩ ኤጀንሲዎች ሕጎችንና የስምምነት ውሎችን ማክበር እንዳለባቸው፣ ይህንን ካደረጉ ኤምባሲያቸውም ሆነ የአገራቸው መንግሥት ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሕገወጥ ደላሎችን ከኢትዮጵያ ጀምሮ ለመዋጋት የአገራቸው መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፣ ሠራተኞችም ሠልጥነውና ችሎታ ኖሯቸው እንዲላኩ፣ በሥልጠና በኩል አስፈላጊ ከሆነ ለመርዳትም ፈቃደኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...