Tuesday, January 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሁሌም የተሻለ መንገድ አለ!

በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለራሱም ሆነ ከአብራኩ ለወጡ ልጆቹ፣ እንዲሁም በተለያዩ ሥፍራዎች ለሚገኙ ወገኖቹ የሚመኘው ጤና፣ ሰላምና ብልፅግና ነው፡፡ ይህ በተለያዩ ብሔሮች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶችና በመሳሰሉት ገደብ የማይደረግበት በጎ ምኞት ነው፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት አዲሱ ዓመት ከባተ በኋላ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ የብሔረሰቦች አዲስ ዓመቶች፣ ወዘተ. በተለያዩ ሥፍራዎች እየተከበሩ ነው፣ ይከበራሉ፡፡ የበዓላቱ  ባለቤቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ወገኖችም በተለያዩ መንገዶች መልካም ምኞታቸውን ከመግለጽ ባሻገር፣ የተለያዩ ዕገዛዎችን በማድረግና ተሳታፊ በመሆን አብሮነትን ያሳያሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘመናትን የተሻገረ አብሮነትና አለኝታነት የኢትዮጵያውያን የጋራ መገለጫ ነው፡፡ የጋራ እሴቶችና መስተጋብሮች መሠረትም ነው፡፡ አሁንም በዚህ ዓይነቱ ጨዋነትና አስተዋይነት የተሞላበት ስሜት መቀጠል ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚያምርባት ልጆቿ በአንድነትና በእኩልነት መንፈስ ሲተባበሩ ነው፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም ጎን ለጎን ሆነው ተረዳድተው መፍትሔ ሲያመነጩ ነው፣ አገራቸውን ከተዘፈቀችበት የዘመናት ድህነትና ኋላቀርነት መንጭቀው ለማውጣት ሲረባረቡ ነው፣ ከመሰሪነትና ክፋት ከተጠናወተው ራስ ወዳድነት በመራቅ በአንድነት ለመሠለፍ ሲችሉ መጪው ጊዜ ከመቼውም በበለጠ የተሻለና ቀና ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያውያን ትልቁ ችግር ድህነትና ኋላቀርነት ነው ሲባል እንደ ቀልድ መታየት የለበትም፡፡ የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ ለማግኘት እጅግ በጣም ፈታኝ የሆነበት ሕዝባችን ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሰላም አንዱ ሌላኛውን አስገብሮ የሚያመጣው ሳይሆን፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ከጉልበትና ከሥርዓት አልበኝነት የፀዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዳ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለውይይትና ለድርድር የሚሆን አሳታፊ ምኅዳር ማስገኘት አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ተከብሮ እኩልነት በግልጽ የሚታይበት ሊሆንም ይገባል፡፡ ከዚያ ውጪ መንግሥት ባለበት አገር በስመ አክቲቪስትነትና የመብት ተሟጋችነት፣ ሕዝቡ ውስጥ ቅራኔ መዝራትና ክፍፍል መፍጠር አገርን ሰላም ይነሳል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ በመደበኛ ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ ትስስር መረቦች ሐሰተኛ ወሬዎችን በመፈብረክ፣ አንዱን ወገን በሌላው ላይ በመቀስቀስ፣ ንፁኃንን ለአደጋ የሚዳርጉ ግጭቶችን በመቀስቀስና የደሃ አገር ንብረት በማውደም የአንድ ጎራ የበላይነትን ማምጣት አይቻልም፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት አጥፊ ፖለቲካ ማራመድም ወደ ተሻለ መንገድ አይወስድም፡፡ በትዕቢትና በጥጋብ በመወጠር አገር ማተራመስም ለማንም ዕርባና የለውም፡፡

የሕዝብ ፍቅርና ክብር የሚገኘው ለአገር የሚጠቅምና በታሪክ የሚታወስ ተግባር መፈጸም ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ የግል ፍላጎትንና ዓላማን በብሔርና በእምነት ጭምብል ጋርዶ አገር ማተራመስና ሕዝብን ግራ ማጋበት መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ለነገሩ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ ኃይሎች ፍላጎት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ማጋበስ፣ ወደፊት ሊጠቅም የሚችል የፖለቲካ ኃይልን በግርግር ሥልጣን ላይ ለማውጣት መረባረብ፣ በነጋ በጠባ ሴራ መጎንጎን፣ ተቃራኒ ተብሎ የሚታሰብ ወገንን ስም ማጥፋትና ቢቻል ማስወገድን ጭምር ያካተተ ዘመቻ ማድረግ ነው፡፡ ችግርን ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ ጉልበት ላይ ማተኮርና ማስፈራራት በዚህ ዘመን አይታሰብም ቢባልም፣ በግልጽ በአደባባይ የሚታየው ግን ይኸው እውነታ ነው፡፡ ከትናንት የተበላሹ ድርጊቶች መማር ያቃታቸው አንዳንድ ወገኖች፣ ከኋላ ያሠለፉትን ኃይል ተማምነው ሲያስፈራሩና መንግሥትን ጭምር አላሠራ ሲሉ በጣም ይደንቃል፡፡ ትናንት ለነፃነትና ለእኩልነት እንጮህ ነበር ሲሉ የነበሩ ዛሬ የጉልበተኝነትን መንገድ ሲያያዙት ያሳፍራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉዞ የት ያደርሳል ቢባል መልሱ የትም ነው፡፡ ለግል ክብር፣ ጥቅምና ዝና ሲባል የጋራ እሴቶችን መናድ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ወደ ተሻለ መንገድም አይወስድም፡፡

ዘመናዊው ዓለም የሚፈልገው የተማረ፣ ብቃት ያለው፣ በየትኛውም ሥፍራ መወዳደር የሚችልና በተግባር የሚያሳምን ብርቱ ሰው ነው፡፡ ይህ ብቃትና ክህሎት የሚገኘው ደግሞ በትምህርትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በሌሎች ጫማ ውስጥ ራስን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ከሎሌነት የተሻለ ቦታ አያስገኝም፡፡ ወጣቶች ለሌሎች ፍላጎት ተገዥ ሆነው ጥፋት ውስጥ የሚገኙት እንዳይማሩ፣ እንዳያውቁና እንዳያገናዝቡ ሲደረጉ ነው፡፡ ወጣቶች ሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ አድርገው ራዕይ ሲሰንቁ ማንም እየመጣ አይጎትታቸውም፡፡ ወላጆች፣ ማኅበረሰቦች፣ ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት አካላት የወጣቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ባለቤት የሆኑት ወጣቶች ከሱስና ከአልባሌ ድርጊቶች ነፃ ሆነው እንዲያድጉ በብርቱ መሠራት አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ለተለያዩ ፍላጎቶች የተደራጁ ኃይሎች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል ምሁራንና ልሂቃን የነገዋ ኢትዮጵያ ምን መምሰል እንደሚኖርባት ማመላከት አለባቸው፡፡ ዳር ሆኖ ከንፈር መምጠጥ ወይም አሉባልታ ውስጥ ሆኖ ነገር ማቡካት ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም፡፡ የተሻለ መንገድን ማመላከት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ አገር የምታድገው በሁሉም ተሳትፎ ነውና፡፡

ሁሌም የተሻለ መንገድ መኖር አለበት፡፡ የተሻለ መንገድ እንዲኖር ግን መተማመን ይገባል፡፡ ‹‹በዚህ ዘመን በዓለማችን ዋነኛውና ውዱ ነገር ነዳጅ፣ አልማዝ፣ ወይም ወርቅ አይደለም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የተሻለው መተማመን ነው፤›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቀና ጎዳና ለማስገኘት መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ይህ መተማመን መምጣት ያለበት ከዘረኝነት፣ ከቂም በቀል፣ ከሴራ፣ ከክፋትና ከዕብሪት በመላቀቅ ቅን በመሆን ብቻ ነው፡፡ ቅንነት ማለት ሞኝነት ወይም የዋህነት ተብሎ መተርጎም የለበትም፡፡ ቅንነት የብልሆችና የአስተዋዮች ፀጋ ነው፡፡ ይህ ፀጋ በዕውቀትና በክህሎት የሚመራ ከሆነ መተማመን አይከብድም፡፡ የበዳይና የተበዳይ ትርክትን ወደ ጎን ብሎ፣ እንደ ሠለጠነ ሰው በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና መደራደር ባህል ሊሆን ይገባል፡፡ ልዩነትን አክብሮና ዕውቅና ሰጥቶ በእኩልነት መንፈስ መነጋገር መቻል ሊያዳግት አይገባም፡፡ ሕጋዊነትን በሕገወጥነትና በሥርዓተ አልበኝነት ላይ የበላይ በማድረግ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዝ ጨዋነትና ባህሪ በመላበስ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አላስፈላጊ ሽኩቻዎችንና ጥላቻዎችን በማስወገድና ከመሰሪ ራስ ወዳድነት በመላቀቅ ወደፊት መራመድ ይቻላል፡፡ በዚህ መንፈስ ሁሌም የተሻለ መንገድ እንዳለ ማረጋገጥ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...