Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራል ጉዳዮችን የሚያዩ ፍርድ ቤቶች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲደራጁ ሐሳብ ቀረበ

የፌዴራል ጉዳዮችን የሚያዩ ፍርድ ቤቶች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲደራጁ ሐሳብ ቀረበ

ቀን:

የውርስና የቤተሰብ ጉዳይም በከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች እንዲታዩ ተጠቁሟል

የክልል ፍርድ ቤቶች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 78(2) ድንጋጌን መሠረት አድርጎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው አዋጅ ቁጥር 322/1995 በአምስት ክልሎች አምስት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው በውክልና እያዩ መሆኑ ቀርቶ፣ የፌዴራል ጉዳይን በሁሉም ክልሎች በቀጥታ ማየት እንዲቻል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲደራጁ ሐሳብ ቀረበ፡፡

ሐሳቡ የቀረበው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለ24 ዓመታት የነበረውንና በተለያዩ ማሻሻያ አዋጆች ተደግፎ ሲሠራበት የቆየውን አዋጅ ቁጥር 25/88 በአንድ አዋጅ ለማጠቃለልና ለማሻሻል በቀረበው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ ሐሙስ መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ለአንድ ቀን አዘጋጅቶት በነበረ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በረቂቁ ላይ ቀደም ብሎ በተነሱ አንኳር አንቀጾች ላይ ትኩረት አድርጎ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት በርካታ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ሲሆኑ፣ ለውይይቱ መነሻ የሆኑትን አንቀጾች የዳኝነት ሥርዓት ማሻሻያ አማካሪ ጉባዔ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብደላ ዓሊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሰብሳቢው ትኩረት ካደረጉባቸው በርካታ አንቀጾች ውስጥ አንዱ በሆነው ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ለክልሎች በውክልና የተሰጠው፣ የፌዴራል ጉዳዮችን በክልል ፍርድ ቤቶች የማየት ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የፌዴራል ጉዳይን ለክልል በውክልና መስጠት ቀርቶ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቀጥታ የፌዴራል ጉዳይን እንዲያዩ የሚያስችል አንቀጽ መካተቱን ተናግረዋል፡፡ በእርግጥ የተካተተው አንቀጽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሁለት – ሦስተኛ ድምፅ ማግኘት እንዳለበት አክለዋል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የፌዴራል ጉዳይ በክልል የሚነሳ ቢሆንም፣ በፌዴራል ፍርድ ቤት በቀጥታ መታየት አለበት ከተባለ፣ ተደራሽነቱን መሠረት ያደረገ በከባቢያዊ (በጂኦግራፊ) አከላለል መደራጀት እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

በምሳሌም በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚነሳ ጉዳይ ምዕራብ ትግራይና ጎንደር አካባቢን ያማከለ ሆኖ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የደቡብ ክልል ቤንች ማጂ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ የኦሮሚያን ጅማ፣ አጋሮ ከጋምቤላ መዥንገር አካባቢን ያማከለ የፌዴራል ፍርድ ቤት ቢደራጅ ተደራሽ መሆን እንደሚችል ተብራርቷል፡፡

ሕገ መንግሥቱም በአገሪቱ አካባቢዎች በሙሉ ወይም በከፊል ሊደራጅ እንደሚችል እንጂ በክልሎች ሊደራጅ እንደሚችል ስለማይገልጽ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን ያማከለ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን፣ ዋናው ነጥብ ግን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ይደራጁ የሚል መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በረቂቁ ውስጥ ከተካተቱ ድንጋጌዎች ውስጥ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንዳንድ የፌዴራል ያልሆኑ ጉዳዮችን፣ የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት በውክልና እንዲያይ እንዲሰጥ የሚለው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚነሱ የውርስና የቤተሰብ ጉዳዮች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ቢሰጡ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በፌዴራል ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያግዛል የሚል ሐሳብም ቀርቧል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ የሚነሳ ማንኛውም ጉዳይ የፌዴራል ስለሆነ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች መታየት አለበት የሚል ሐሳብም ተንፀባርቋል፡፡ በተለይ የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ሥልጣን በሚመለከት በቀረበው መቃወሚያ ሐሳብ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰኑ የዳኝነት ሥልጣኖችን ለሌላ የዳኝነት አካል መስጠቱ ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን በሚመለከት ነው፡፡ የዳኝነት ሥልጣን በውክልና ሊሰጥ የሚችለው በሕገ መንግሥት ድንጋጌ ብቻ ወይም በፌዴራል ፍርድ ቤት አዋጅ ጉዳዮቹን በመዘርዘር እንጂ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑም ተገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ የሚነሳም ጉዳይም እንደ ሕገ መንግሥቱ አገላለጽ፣ ‹‹የፌዴራል ጉዳይ እስካልሆነ ድረስ›› የሚል ሐሳብ እስካልተቀመጠ ድረስ ለአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ሊሰጥ እንደማይችል ተገልጿል፡፡

በረቂቅ አዋጁ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሚለው አንቀጽ ሊተረጎም ይገባል? ወይስ ባለበት መቀጠል አለበት? የሰበር ሰበር መታየት ያለበት ጉዳዩ የፌዴራል ሆኖ በውክልና በክልል ፍርድ ቤት የተወሰነ ከሆነ፣ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብትን የሚጋፋ ውሳኔ ከሆነ ብቻ ለሰበር ሊቀርብ ይገባል የሚሉ አንቀጾች አከራካሪ ሆነዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 80 (3ሀ) ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ ስህተት ያለበትን ማንኛውንም ጉዳይ በሰበር የማረም ሥልጣን እንዳለው ከመደንገጉ አንፃር፣ በረቂቁ የተካተተው ሐሳብ ተቀይባነት እንደሌለውም ተገልጿል፡፡ በዚሁ አንቀጽ መሠረት የክልል ጉዳይ የሕግ ስህተት ካለበት የክልል ሰበር ስለማያርም፣ የሰበር ሰበር አስፈላጊ እንዳልሆነና የፌዴራል ሥርዓት መርህም አይደለም የሚል ክርክር ቀርቧል፡፡

የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሁሉም ጉዳዮች ላይ የመጀመርያ ዳኝነት ሥልጣን እንዲኖረውና በሦስት ዳኞች የሚሰጠው ውሳኔ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እንደሚሆን የሚል ሐሳብም ቀርቧል፡፡ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን (ከተወሰኑት በስተቀር) በሙሉ በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታዩና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እንዲሆን የሚሉ ሰፊ ክርክሮች ተካሂደዋል፡፡

ሰባት ወይም ዘጠኝ ዳኞች የሚሰየሙበት የፓናል ችሎት አስፈላጊነትን  በሚመለከትም ሐሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ የችሎቱ አስፈላጊነት በጣም ውስብስብ የሆኑና አገራዊ የሆኑ ጉዳዮችን ማየት የሚችል ባለአምስት ዳኞች የሰበር ውሳኔን የሚያርም ችሎት ሆኖ፣ ዕርማት የሚሰጠው እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ውሳኔዎች ሲገኙ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በዳኞቹ ብዛት ላይም ሰባት ወይም ዘጠኝ ይሁኑ በሚለው ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በሦስት ዳኞች የሚታየው የሰበር አቤቱታ ቀሪ ሆኖ በቀጥታ ለሰበር ችሎቱ መቅረብ አለበት የሚለው የሥራ ጫና ማብዛት ስለሚሆን፣ በባለሙያዎች ተጣርቶ ይቅረብ በሚል ጉዳይም ክርክር ተነስቷል፡፡ ለችሎቶች የሕዝብ አመኔታ ማጣት በዋናነት የሚጠቀሰው ሦስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ያለ ምንም ማብራሪያ፣ ‹‹አያስቀርብም ወይም ያስቀርባል›› እያሉ መቅረብ ያለበትን ውድቅ በማድረግና አለመቅረብ ያለበትን ያስቀርባል በማለታቸው መሆኑን በመጥቀስ ክርክር ተደርጎበታል፡፡

በአጠቃላይ አዋጅ ቁጥር 25/88ን የሚቀይረው ረቂቅ አዋጅ በስምንት ክፍሎች፣ 43 አንቀጾችና በ126 ንዑስ አንቀጾች ዘርዘር ባለና ሁሉንም አስፈላጊ ድንጋጌዎች አካቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ለማፀደቅም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

ውይይቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ የከፈቱት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ መድረኩን በአወያይነት መርተዋል፡፡ በርካታ ዳኞች በተለይ አዲስ በተካተቱ አንቀጾች ሕጋዊነት ላይ ከሕገ መንግሥቱ አንፃር በመተቸት የሚካተቱ ሐሳቦችን አቅርበዋል፣ አስተያየቶችንም ሰጥተዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...