Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ከአንድ ቀን በላይ የሚቆዩ መንገደኞች ከክፍያ ነፃ ቪዛ እንዲያገኙ ውይይት እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን ረግጠው ወደ ተለያዩ አገሮች የሚበሩ የስቶፕ ኦቨር መንገደኞች ለሚቆዩባቸው ቀናት የሚገለገሉበትን የኢትዮጵያ ቪዛ፣ ከክፍያ ነፃ ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ የስቶፕ ኦቨር መንገደኞች በሚተላለፉባቸው አገሮች አንድ ቀንና ከዚያ በላይ እንደሚቆዩ፣ በእነዚህ ጊዜያትም የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚጎበኙባቸው ፓኬጆች ቢዘጋጁ የአገሪቱን የቱሪዝም ገቢ በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር የዓለም ባንክ ጥናት ያሳያል፡፡

ለዚህም የስቶፕ ኦቨር መንገደኞች ኢትዮጵያን እንደ አንድ መዳረሻ እንዲያደርጉ ለማስቻል ስትራቴጂ ተቀርፆ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝምን ለማጎልበት በተዘጋጀው ስትራቴጂ መንገደኞች ነፃ ቪዛ የሚገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት ዋናው ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ቡክ በማድረጊያ ፎርሙ ላይ የስቶፕ ኦቨር በረራን እንደ ሦስተኛ አማራጭ አድርጎ እንዲያካትት ይጠበቃል፡፡

ይህም አገሪቱ ያሏትን የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች በማስተዋወቅ ከተደገፈ፣ መንገደኞች በኢትዮጵያ ለቀናት ቆይተው ለመውጣት የሚያነሳሳቸው ይሆናል ተብሏል፡፡ ዋናው ነገር ግን መንገደኞቹ የሚንቀሳቀሱበት ነፃ ቪዛ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሆነ ስትራቴጂው ያሳያል፡፡ እንግዶች ቆየት ብለው መዳረሻ ሥፍራዎችን የመጎብኘት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ለቪዛ እንዲከፍሉ የሚጠየቁት 150 ዶላር ገንዘብ ግን ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ እንደሚያደርጋቸው ተነግሯል፡፡

የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን አልፈው ወደ ተለያዩ አገሮች የሚሄዱ 1,000 የትራንዚት መንገደኞች በስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ኢትዮጵያ ውስጥ መቆየት እንደሚፈልጉ ተጠይቀው፣ 84 በመቶ የሚሆኑት ፍላጎት እንዳላቸውና በአብዛኛው ነፃ ቪዛ እንዲኖር መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

በስቶፕ ኦቨር ፓኬጅ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ነፃ ቪዛ እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን፣ በቅርቡም ዕውን እንደሚሆን በቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ ገብረ ትንሳዔ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ 12 ሚሊዮን መንገደኞች በቦሌ ኤርፖርት እንደተጓጓዙ፣ አሥር ሚሊዮኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደበረሩና ስምንት ሚሊዮኖቹ ደግሞ የትራንዚት መንገደኞች እንደ ነበሩ፣ ይህም ኢትዮጵያን በስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርጋት ዕምቅ አቅም እንዳላት በማሳያነት ተወስቷል፡፡ ‹‹አምስት በመቶ ያህሉን መንገደኞች በስቶፕ ኦቨር ቱሪዝምን እንዲጠቀሙ ብናደርግ ለአገሪቱ ትልቅ ገቢ ማስገኘት ይቻላል፤›› ሲሉ አቶ ዓለማየሁ አስረድተዋል፡፡  

አየር መንገዱ የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ፕሮግራምን ባለፈው ዓመት በይፋ ማስጀመሩን፣ 4,150 መንገደኞችም እንደተስተናገዱ ተነግሯል፡፡ ጅምሩን በስትራቴጂ መምራት ከተቻለ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በሙሉ መፍታት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡

አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት፣ የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ስትራቴጂውን ማዘጋጀት ያስፈለገው ለአገሪቱ የተሻለ የቱሪዝም ገቢ ለማግኘት ነው፡፡ የትራንዚት መንገደኞች በኢትዮጵያ የሚኖራቸው ቆይታ ከስድስት እስከ ስምንት ሰዓት ሲሆን፣ የስቶፕ ኦቨር መንገደኞች ደግሞ 24 ሰዓትና ከዚያ በላይ የሚቆዩ ናቸው፡፡ እነዚህ መንገደኞች የሚስተናገዱበት ሥርዓት ባለመዘጋጀቱ፣ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ስታጣ እንደቆየች የዓለም ባንክ ጥናት ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች