የተለያዩ መጠን ያላቸውን ጥቅል ዕቃዎችን መላክና መቀበል የሚያስችል፣ ተሽከርካሪ ያላቸውን ሁሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ‹‹ባልደራሱ›› የተባለ አገልግሎት ይፋ ሆነ፡፡ የባልደራሱ አገልግሎት በሞባይል ስልክ መተግበሪያ አሽከርካሪውን ከደንበኛ የሚያገናኝ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሎለታል፡፡
በሆራይዘን ኤክስፕረስ ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተጀመረውን የባልደራሱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልግ ደንበኛ የሚገኘው ለምሳሌ መገናኛ አካባቢ ቢሆን፣ መተግበሪያውን አብርቶ በአቅራቢያው ያለ የባልደራሱ አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ ማግኘት ይችላል፡፡ የቤት መኪና ያላቸው ወደ ቢሮ በመግባት ላይ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ እግረ መንገዳቸውን ሰነድ ተቀብሎ በማድረስ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበት እንደሆነ፣ የሆራይዘን ኤክስፕረስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሶፎኒያስ እምቢበል ገልጸዋል፡፡
ለኮንስትራክሽን የሚውሉ ግብአቶችን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ማድረስ የሚችሉ ከባድ ተሽከርካሪዎችም ጭምር፣ የባልደራሱን አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ቤት የሚቀይሩ ሰዎችም የባልደራሱን አገልግሎት ማግኘች የሚችሉበት አሠራር እንዳለ ዋና ሥራ አስፈጻሚው የአገልግሎቱን በይፋ መጀመር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ከሞባይል መተግበሪያ ባሻገር በ6583 የጥሪ ማዕከል የተደገፈ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ የጥቅል ዕቃ የመቀበልና የማድረስ አገልግሎት የሚሰጠው ባልደራሱ ለቀላል ዕቃና ዶክመንቶች ማመላለሻነት የሚውሉ የሞተር ብስክሌት፣ የኋላ መጫኛ ያላቸውን ተሽከርካሪዎች አሰማርቷል፡፡ መካከለኛ ክብደት ላላቸው ዕቃዎችም የሚኒቫንና የፒካፕ ተሽከርካሪዎች፣ ለከባድ ጭነቶች ደግሞ የሚመጥኗቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች እንደተሰማሩ ታውቋል፡፡
ሆራይዘን ኤክስፕረስ የባልደራሱን አልግሎት የሚሰጡ የራሱን 50 ሞተር ብስክሌቶችና፣ አራት ተሽከርካሪዎች ማሰማራቱን፣ አገልሎቱን መስጠት በጀመረ በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥም ከ300 በላይ የተለያዩ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተመዝግበው አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሆነ አቶ ሶፎኒያስ አስረድተዋል፡፡
ለሚያቀርበው አገልግሎት ድርጅቱ በሁለት መንገዶች ገቢ ያገኛል ያሉት አቶ ሶፎኒያስ፣ በራሱ ተሽከርካሪዎች በሚሰጠው አገልግሎት የሚያገኘው ክፍያ የመጀመርያው ገቢ ሲሆን፣ በተዘጋጀው የስልክ መተግበሪያና በጥሪ ማዕከሉ ተሽከርካሪውንና ደንበኛውን በማገናኘቱም ኮሚሽን ያገኛል ብለዋል፡፡ አሽከርካሪው ከሚከፈለው ላይ 12 በመቶ የሚሆነው የሆራይዘን ኮሚሽን ነው ተብሏል፡፡
ባልደራሱ በየትኛውም ቦታ ሆነው ሳይንቀሳቀሱ የሚያገኙት አገልግሎት በመሆኑ፣ ከሌሎች መሰል አገልግሎቶች ለየት ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ፈጣንና ዋጋውም ኪስ የማይጎዳ ነው የሚሉት አቶ ሶፎኒያስ፣ ዶክመንት ተቀብለው የሚያደርሱ ሞተር ብስክሌቶች መነሻ ዋጋ 30 ብር እንደሆነ፣ እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር ድረስ ተጨማሪ ሒሳብ ሳይታሰብ በመነሻ ዋጋ ብቻ እንደሚታሰብ፣ ከሦስት ኪሎ ሜትር በኋላ ግን በኪሎ ሜትር 12 ብር እንደሚቆጥር ገልጸዋል፡፡ አጠቃላይ ክፍያው ግን እንደ ተሽከርካሪው ዓይነትና የሚሰጠው አገልግሎት የተለያየ ይሆናል ተብሏል፡፡
ድርጅቱ ከተለያዩ ተቋማት በጋራ ለመሥራት ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን፣ ከእነዚህ ተቋማት መካከል የራይድ አገልግሎት የሚሰጠው ሀይብሪድ ዲዛይን አንዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ስምምነቱም የራይድ አገልግሎት የሚሰጡ በከተማዋ የሚገኙ ከ6,000 የሚበልጡ ተሽከርካሪዎች የባልደራሱን አገልግሎት እንዲሰጡ እንደፈቅድላቸው አቶ ሶፎኒያስ ገልጸዋል፡፡ የራይድ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የኋላ ዕቃ መጫኛቸውን ለባልደራሱ ደንበኞች ያውላሉ ተብሏል፡፡
ሦስት ዓይነት ባህሪያት እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀው የባልደራሱ መተግበሪያ አሽከርካሪዎች፣ ደንበኞችና እንዲሁም ጫኝና አውራጆች የሚገለገሉበት ነው፡፡ ባልደራሱ አሽከርካሪንና ደንበኛን ከማገናኘት ባለፈ የጫኝና የአውራጅነት ሥራ የሚያከናውኑ ወዛደሮችን ከአሠሪ የሚያገናኝ እንዲሆን ተደርጎ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡ አሠራሩም በወዛደሮችና በአሠሪዎች መካከል ብዙ ጊዜ የሚፈጠረውን ግጭት የሚያስቀር ነው የተባለ ሲሆን፣ ክፍያው በወጣው ተመን መሠረት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
ያሉበት ቦታ የሬስቶራንት ምግብ እንዲመጣላቸው ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎችም፣ መሰል አገልግሎት መስጠት የሚቻልበትን አሠራር በመዘርጋት ላይ መሆኑን አቶ ሶፎኒያስ አስረድተዋል፡፡ አገልግሎቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም አክለዋል፡፡