የስፖርት ታላቅነት ከሚለካባቸው መስተጋብሮች አንዱ በሕዝቦች መካከል ወዳጅነትና ወንድማማችነት መንፈስ መፍጠሩ ነው። ይህ ተልዕኮው ግን በዚህ ዘመኗ ኢትዮጵያ ብዙም የሠመረለት አለመሆኑ፣ እግር ኳሱና ባለድርሻ ነን በሚሉ መካከል ያለውን ትርምስና እሰጥ አገባ መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡ የእግር ኳስ ማዘውተሪያዎች በተለይም ስታዲዮሞች የነውጠኞች ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ከሆነ መሰነባበቱ ሳያንስ፣ ከውድድር ሥርዓት (ፎርማት) ጋር ተያይዞ በፌዴሬሽኑና በክለቦች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ከሁለት አሠርታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተዟዙሮ የጨዋታ መርሐ ግብር በተለይም ካለፈው ሦስትና ሁለት ዓመታት ወዲህ የክልል ቡድን ወደ ሌላው ክልል ሄዶ መጫወት የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ውድድሮች በገለልተኛ ወይም በይደር እየተላለፉ ክለቦችን ለከፋ ኪሳራ ሲዳርግ መቆየቱ እንደተጠበቀ፣ ለሰዎች ሕይወትና ንብረት መውደም ምክንያት መሆኑ ለስፖርቱ መጥፎ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ለእግር ኳሱ ውድቀትም የጎላ ድርሻ እንደነበረው የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
በእነዚህና ሌሎችም በተለይ የአዲስ አበባ ክለቦች በ2012 ዓ.ም. የውድድር ዓመት በነበረው መቀጠል እንደማይችሉ መግለጻቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማራጭ ይሆናል ያለውን ሲሞክር ቆይቶ፣ በመጨረሻም በተዟዙሮ ጨዋታ ችግሩን የሚፈጥሩትን መለያየት ማለትም የአማራና የትግራይ፣ ከደቡብ የሲዳማና የወላይታ ከአዲስ አበባ ደግሞ አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች እንዳይገናኙ ማድረግ በሚለው ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ ይህንኑ አቋሙን በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ የተዟዙሮ ፎርማት ባለበት ነገር ግን የክለቦቹን ቁጥር ወደ 24 ከፍ በማድረግና በሁለት ምድብ ማለትም “ሀ” እና “ለ” ከፋፍሎ ውድድሩን ደግሞ በክለቦቹ ሙሉ ፍላጎትና እምነት በሚቋቋም አካል እንዲመራ ለማድረግ ያለመ ውሳኔ ስለመሆኑ ጭምር በመግለጫው ማካተቱ ይታወሳል፡፡ ክለቦቹም ትርፋማና ውጤታማ መሆኑ ይችሉ ዘንድ ከፎርማቱ ጎን ለጎን የሊግ ካምፓኒ ማቋቋሚያ ሰነድ በማዘጋጀት ለክለቦች እንዲደርሳቸው ማድረጉን ጭምር አስታውቆ ነበር፡፡
ውዝግቡን ለማብረድ በሚል በጨዋታ እንዳይገናኙ የተደረጉት የክልልና የአዲስ አበባ ክለቦች፣ ውሳኔው ከስፖርቱም ባለፈ እንደ አገር ሊያስከትል የሚችለውን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን ከመተግበሩ በፊት ክለቦችና የክልል ፌዴሬሽኖች በባለቤትነት ተካተውበት ቀጣዩ የውድድር ሥርዓት እንዴት ይሁን በሚለው ላይ እንደገና ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል።
እስከዚያው ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አዲስ በቀረፀውና 24 ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው እንዲጫወቱ የሚለው የውድድር ሥርዓት (ፎርማት) ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በስፖርት ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሒሩት ጋሻው በተገኙበት መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በዕለቱ በነበረው ውይይት ላይ የክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የክለብ ፕሬዚዳንቶች፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ እንደነበሩም ታውቋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ካቢኔያቸው መካከል እግር ኳሱን በሚመለከት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ ስምምነት እንደሌለ፣ ይህም ለተቋሙ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና አካሄድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ፣ በዚሁ አካል ለቀጣዩ የእግር ኳስ ሰላማዊ እንቅስቃሴና ውጤታማነት ሲባል የሚወጡ መመርያዎችና ደንቦች የባለድርሻ አካላቱን ይሁንታ ሳያገኙ ሥራ ላይ እንዲውሉ ሲደረጉ መቆየቱ ተቋሙን በመድረኩ ካስተቹት ይጠቀሳሉ፡፡
ለፌዴሬሽኑ ተዓማኒነት ማጣት ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየው ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ ክልሎችና ክለቦች ጭምር ሁሉም ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባ ከስምምነት መደረሱ ቢታወቅም፣ በተቋሙ ውሳኔ ለአዲሱ የውድድር ሥርዓት ለቁጥር ማሟያ በፕሪሚየር ሊጉ እንዲቆዩና በቀድሞ መመርያ መሠረት ሥርዓቱን ተከትሎ ካደጉት ክለቦች በተጨማሪ በፕሪሚየር ሊጉ መካተታቸው በደብዳቤ የተነገራቸው ክለቦች ጉዳይ እንዴት ሊሆን ነው የሚለው ግን አሁንም ዕልባት ያላገኘ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በ2011 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርደው፣ ነገር ግን በፌዴሬሽኑ ውሳኔ አለመውረዳቸውን ከማወቃቸውም በላይ በ2012 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጨዋቾችን ያዘዋወሩት መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት፣ እንዲሁም ከከፍተኛው ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጋቸው የተነገራቸው ኢትዮጵያ መድን፣ ነቀምት ከተማ፣ አርባ ምንጭ ከተማና ሌሎችም በተመሳሳይ ቡድናቸውን ለማጠናከር በሚል ከፍተኛ በጀት መመደባቸው ይታወቃል፡፡