Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክ‹‹በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር››

‹‹በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር››

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ከወንጀል ሕግ መርሆች ያፈነገጠ፣ ነገር ግን በየአዋጆቹ የቅጣት አንቀጽ ላይ ማስቀመጥ ‹‹መርህ›› የሆነ እስኪመስል ድረስ የቀጠለ አንድ ሐረግ አለ፡፡ ይህ ሐረግ ፍትሕ የማዛባት፣ መሠረታዊ የወንጀል ሕግ መርሆችን በማዛባት ያልተለመደ ልማድ እያሳደገ ይገኛል፡፡ በሐረጉ ሳቢያም ግለሰቦች ለኢፍትሐዊ ውሳኔና ቅጣት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ይህ ሐረግ የቅጣት አወሳሰንን ከታወቀው አሠራር እንዲያፈነግጥ የሚያደርግ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሐረጎች የተሰነቀሩበት አንቀጽን የያዘ አዋጅ ማውጣት የፓርላማው ልማድ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የሐረጎቹ ይዘት ‹‹በሌላ ሕግ ወይም በወንጀል ሕጉ የበለጠ የሚስቀጣ ካልሆነ በስተቀር›› የሚከተሉትን ድርጊት የፈጸመ ወይም በዚህ አዋጅ ላይ የተገለጹትን ክልከላዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው ምን ዓይነት ቅጣቶችን እንደሚቀጣ ይዘረዝራል፡፡

- Advertisement -

የሆነን ጉዳይ የሚያስተዳድር ሕግ በአዋጅ ሲወጣ፣ በአዋጁ የሚቀመጡትን ግዴታዎች ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ ሕጉን የሚተላለፉት ወይም ሳይፈጽሙ የቀሩት ላይ አስተዳደራዊ እና/ወይም የወንጀል ቅጣትን ቀድሞ ማሳወቅ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሕግ መርሆችን ባከበረ እንጂ በጣሰ መልኩ ይፈጸማል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ መርሆች የማይሸፍኗቸው ልዩ ሁኔታዎች (Exceptions) ሊኖሩ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ግን በልዩ ሁኔታ ምድብ ውስጥ የሚወድቅ አይደለም፡፡

ይህ ጽሑፍም ትኩረት ያደረገው የዚህን በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር በሚል መሪ ሐረግ ቅጣት የመደንገግም የመወሰንም አካሄድ ሕጋዊነት መርህም ከሕገ መንግሥታዊነትም አንፃር ፍተሻ ማድረግ ነው፡፡ የቅጣት አንቀጽ ባላቸው አዋጆች ውስጥ በስፋት የተሰነቀረ ሐረግ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ወይም ይህን ሐረግ የያዙትን አዋጆች መዘርዘር ብዙም ፋይዳ ስለሌለው አንድ አምስት አዋጆችን ብቻ ናሙና እንደርጋለን፡፡

ሀ. አዋጅ ቁጥር 660/2002 የንብ ሀብት ልማትና ጥበቃ  አዋጅ  አንቀጽ  8 ‹‹በወንጀል ሕጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር. . .›› ይልና በሥሩ ባሉ ሰባት ንዑስ አንቀጾች የተዘረዘሩ የወንጀልና ቅጣት ዝርዝሮችን ይዟል፡፡

ለ. የግል ድርጅትና ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 አንቀጽ 59 ‹‹የያዘውን ማስረጃ በዚህ አዋጅ መሠረት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም የዚህን አዋጅ ድንጋጌ አፈጻጸም የሚያሰናክል ተግባር የፈጸመ ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግ የበለጠ የሚስቀጣ ካልሆነ በስተቀር እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና እስከ አሥር ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፤››

. ምንም እንኳን አዋጁ በሌላ አዋጅ የተተካ ቢሆንም፣ በ1989 ዓ.ም. የወጣው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 67/1989  አንቀጽ 46 ‹‹በዚህ አዋጅ ልዩ ልዩ አንቀጾች አግባብ ያለው ባለሥልጣን የሚወስዳቸው አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው ወንጀሉ አግባብ ባላው ሌላ ሕግ በለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር. . .›› በማለት በስድስት ንዑስ አንቀጾች የወንጀል ዓይነትና የቅጣት መጠን ዘርዝሯል፡፡

. በ2002 በወጣውና ከላይ ያለውን አዋጅ የሻረው ሌላኛው የንግድ ምዘገባና ፈቃድ ሕግም አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 60 ተመሳሳይ ነው ይዘቱ፡፡

. የቅጅና ተዛማጅ መብቶች መብቶች ጥበቃ አዋጅም (አዋጅ ቁጥር 410/1996) አንቀጽ 36 ሥር ባሉት ሦስት ንዑስ አንቀጾች እያንዳንዳቸው ‹‹በወንጀል ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር. . .›› በሚል የመግቢያ ሐረግን ይዘዋል፡፡

እነዚህ አዋጆችን አነሳን እንጂ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ቁምነገሩ አንድምታቸው በወንጀል ሕግ ከፍተኛ ቦታ ያለውን የሕጋዊነት መርህ በመጣስ በኢሕጋዊነት መርህ መተካት፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌንም የወደ ጎን ያለ አካሄድ ስለሆነ አፍታተን እንየው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አገላለጽ አዲስ አዋጅ ቢወጣም በቀደመ ሕግ መቅጣትን የማስከተል ዕድል አለው፡፡ የወንጀል ሕጉ ከወጣ በኋላ በወጡ አዋጆች ላይ በግልጽ የቅጣት አንቀጽ እያላቸው ከዚያ በፊት በወጣው ሕግ ለመቅጣት ያስችላል፡፡ በዚህ አልፎም በአጋጣሚ ተመሳሳይ ጉዳይን ወንጀል የሚያደርግ በሆነ አዋጅ ውስጥ የሚገኝ አንቀጽ ከተገኘም በሌላ አዋጅ ከፍ ባለ ቅጣት ለመወሰን በር ይከፍታል፡፡

በወንጀል ድርጊት ኃላፊነት ከሚኖርበት ሰው ይልቅ ለከሳሹ አማራጮችን ይሰጣል፡፡ ሕግ የማስታወቂያነቱን ዓላማ ወደ ጎን ያደርጋል፡፡ የወንጀል ተግባሩ በሚፈጸምበት ጊዜ በግልጽ ወንጀል መሆኑና ቅጣቱም ሊታወቅ ግድ ነው፡፡ የሕጋዊነት መርህ ዋና መሠረቱም ይህ ነው፡፡ የወንጀል ድርጊቱን ገልጾ፣ ቅጣትም አስቀምጦ ሲያበቃ በሌላ ሕግ የተገለጸ ከፍ ያለ ቅጣት ከተገኘም በዚያው ነው ቅጣቱ የሚሆነው የሚል የወንጀል ሕግ መርህ ውስጥ አይገኝም፡፡

የሕጋዊነት መርህ የወንጀል ሕግ መርህ በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 2 ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ የተለያዩ ጉዳዮችን በሥሩ አካቶ ይዟል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምናነሳው ግን በአንቀጽ 5 እና 6 ላይ የተመለከቱትን የዚህን መርህ ክትያዎች ይሆናል፡፡ ከላይ እንደገለጽነው በወንጀል ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር የሚለው አገላለጽ ሕግ ወደ ኋላ ሄዶ ተፈጻሚ እንዲሆን ሊያደርግም ይችላል፡፡ ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች በሌላ ሕግ በማለት የሚገልጿቸው ኋላ ላይ የሚወጡትንም ይጨምራል፡፡

እንደሚታወቀው የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሠራባቸው ድንጋጌዎች በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ አንደኛው አንድ ቅጣት ሕግ ከመውጣቱ በፊት እንድ ወንጀል ይቆጠር ያልነበረ ድርጊት ቢፈጸም ሆኖም ግን በአዲሱ ሕግ መሠረት እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የሚያስቀጣ ቢሆን አድራጊው ሕጉ ከመጽናቱ በፊት ለፈጸመው ተግባር በወንጀል ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ሁለተኛው አንድ የቆየ የቅጣት ሕግ በአዲስ ቢተካ አዲሱ ሕገ ከመውጣቱ በፊት የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች የሚዳኙት በተሻረው ሕግ ድንጋጌዎች እንጂ በኋለኛው ሕግ አይደለም፡፡ በማንኛውም መልኩ ሕግ ከፀናበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ድንጋጌዎች ላይ እንጂ ባለፉት ላይ ተፈጻሚነት ኃይል የለውም፡፡ ይህ መሠረታዊ ድንጋጌ ሰዎች ከአሁን በፊት የሚያውቁት ሕግ ብቻ የመዳኘት መብት ይሰጣቸዋል፡፡ ካልተጠበቀና ካልተሳበ ቅጣት ያድናቸዋል፡፡ ሕጉ ሁሌም አብሯቸው እንዲኖር እንዲያውቁትና እንዲጠነቀቁበት ካልሆነም ደግሞ የሚደርስባቸውን የቅጣት ደረጃ ለመገመት እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡

ሕግ በአጠቃላይ እንደ ጊዜው ሁኔታ ያለፈውን ድርጊት ባለፈው ሕግ የአሁኑንና የወደፊቱን ደግሞ በአሁኑ ሕግ እንዲታይ ዕድል ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር የሚል የሕግ አቀራረፅ ከላይ ካየነው ጋር የሚስማማ ሳይሆን የሚቃረን ነው፡፡ በአንድ በኩል የቅጣት መጠንን ቀድሞ እንዳያውቁ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በገንዘብ የሚያስቀጣው በሌላ ሕግ በእስራት ሊሆን ይችላል፡፡ የቅጣትን ተገማችነት በማሳነስ የሕግን የማስታወቂያነት ሚና ማኮሰስ ነው፡፡ ውዥንብር ለመፍጠር የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሕግ ባህሪ አይደለም፡፡

አንድ ድርጊት በቀድሞው ሕግ ሥር ያስከትል የነበረው የቅጣት ክብደት በሌላ አዲስ ሕግ የተጨመረ እንደሆነ ጥፋተኛው የሚቀጣው ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ ለወንጀሉ ተፈጻሚ በነበረው ቅጣት ነው፡፡ ወንጀሉን በተፈጸመበት ጊዜ ለወንጀሉ ተፈጻሚ ከነበረው ቅጣት ጣራ በላይም አይፈጸምበትም፡፡ ይህ የወንጀል ቅጣት በተከሳሽ ላይ የከበደ ቅጣት ለማስፈረድ በየጊዜው የሚያዥቅ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ በሌላ አገላለጽ የወንጀል ቅጣት እንደ ገበያ ዋጋ ከፍና ዝቅ የሚል አለመሆኑን በቁርጥ ማሳወቅ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ አንድ ሰው ወንጀል በሚፈጽምበት ጊዜ የነበረው ሕግ የሚደነገገው የቅጣት ጣሪያ የት ድረስ ነው? የሚለው እንጂ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ (አዲስ) ሕግ የሚደነገገው የቅጣት ጣሪያ የት ድረስ ሊሆን ይችላል የሚል አይደለም፡፡  ይህ እንዳልሆነ ቢታወቅም ቅሉ፣ በሌላ ሕግ ምናልባትም ወደፊት በሚወጣም ጭምር ከፍ ባለ ቅጣት ለመቅጣት መሻት ከሕጋዊነት መርህም ከሕገ መንግሥቱም ማፈንገጥ ነው፡፡

አዲስ የወጣ ሕግና በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ቅጣት የሚወስን በሚሆንበት ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሶ የሚሠራበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ የሚሠራበት አንዱ አጋጣሚ ለተከሳሹ  የሚጠቅም  ከሆነ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ ስድስት ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

‹‹ይህ ሕግ እንዲፀና ከተደረገ በኋላ አድራጊው ሕጉ ከመጽናቱ በፊት ላደረገው ወንጀል ሲፈረድበት ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ በሥራ ላይ ከነበረው ሕግ ይልቅ ይኼኛው ሕግ ቅጣት የሚያቃልለት ሲሆን፣ በዚህ ሕገ ላይ ተመለከተው ቅጣት ይፈጸምበታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህ ሕግ የተሻለ መሆኑን የሚወስነው በእያንዳንዱ ጉዳይ አግባብነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በማመዛዘን ነው፡፡››

‹‹ይህ ሕግ›› በማለት የተገለጸው የወንጀል ሕጉን ቢሆንም ይኼ ሁኔታ በሌሎች ሕጎችም ይፈጸማል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በግልጽ የሰፈረ መርህ ነው፡፡

ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመው የቀደመው የወንጀል ሕግ በሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ ቢሆንና  ድርጊቱም በሁለት የወንጀል ሕጐች የተከለከለና የሚያስቀጣ በሚሆንበት ጊዜ ቅጣቱ በሚመለከት ኋለኛው ሕግ በፊት ከነበረው የተሻለና ቀለል ያለ ድንጋጌ ካስቀመጠ ተከሳሹን ለመጥቀም ሲባል በኋለኛው ሕግ ላይ የተቀመጠው ቅጣት ይፈጸምበታል እንጂ የቀደመው አይፈጸምበትም፡፡ ይህ የሚያሳየው የወንጀል አንቀጽ የያዘው ሕግ በሥራ ላይ ባልነበረበት ወቅት የተፈጸመን ድርጊት ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲሠራ የሚደረግበት ልዩነት ነው፡፡

በአዲሱ ሕግ ቢያንስም በቀድሞ ሕግ የበለጠ መቅጣትም ይሁን በቀድሞው ሕግ ያነሰ ቅጣት እያለው በአዲስ ሕግ ቅጣቱ ከፍ ስላለ ኋለኛውን ሕግ መርጦ ቅጣት መወሰን የሕጋዊነትን መርህም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ነው፡፡ የሕግን መሠረታዊ ዓላማም የሚጥስ ነው፡፡  ሕግ በግልጽ ቆርጦ ማስቀመጥን እንጂ ከሳሽ ከፍተኛ የቅጣት መጠን ያለውን ከየትም ፈልጎ ለማስቀጣት እንዲችል ሕግ አሠራር መዘርጋት ያልተለመደ ነው፡፡ ተከሳሽ ዝቅ ባለው ቅጣት እንጂ ከፍ ባለ እንዲቀጣ ለፍርድ ቤት ሥልጣን፣ ለዓቃቤ ሕግ ምርጫ መስጠት የለበትም፡፡

በእርግጥ አዋጆቹ ‹‹በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር›› የሚለው ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ያለማድረግ ሥልጣን አላቸው፡፡ የወንጀል ክስ የቀረበበትን አንቀጽ መቀየር የሚያስችል ሥልጣን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ስለተሰጣቸው፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች ከፍ ያለ ቅጣት ባለው ሕግ በተከሰሱ ጊዜ ዝቅተኛ ቅጣት ያለው ተፈጻሚ እንዲሆን መከራከር ይችላሉ፡፡

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤት በራሱ አነሳሽነት ወይም በተከሳሽ ተቃውሞ አማካይነት መወሰን ላይ የተንጠለጠል ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ ከፍተኛ ቅጣት ባለው የመቀጣት ዕድል ያጋጥማል፡፡ ሕግ አውጭው ሰዎችን የበለጠ በማስፈራራት ለሕግ ተገዥ እንዲሆኑ የማድረግ ፍላጎት ኖሮት የሚያደርገው ነው ቢባል እንኳን ተከሳሾችን ኢፍትሐዊ ለሆነ ውሳኔ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ በፍሬ ጉዳይ ከመከራከር ይልቅ በእንዲህ ዓይነት መከራከሪያዎች ጊዜ፣ ጉልበትና ሀብት ማበከንን ያስከትላል፡፡ የሕግን መሠረታዊ ዓላማና ሚናም የሳተ ነው፡፡

መፍትሔው ደግሞ ‹‹በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር›› የሚል ይዘት ያዘሉ ሐረጎችን የቅጣት አንቀጾችን በያዙ አዋጆች ጉያ መሰንቀርን ማስቀረት ነው፡፡  

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...