Friday, December 1, 2023

መጪው ምርጫና ትኩረት የሚሻው የሲቪል ማኅበራት ሚና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ለአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ መጠናከርና መጎልበት  ከሚያስፈልጉ ተቋማትና አደረጃጀቶች መካከል ነፃ የሆነ የሲቪል ማኅበረሰብ መኖርና በነፃነት ሥራውን መከወን መቻሉ እንደ አንድ መለኪያ የሚቆጠር መሠረታዊ መዋቅር እንደሆነ፣ በዘርፉ የተጻፉ በርካታ ድርሳናት ያትታሉ፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያነት በተለይም ለዘመናት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በተግባር ያዋሉ አገሮች ውስጥ ለመታዘብ እንደሚቻለው እነዚህ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት መዳበር ለአጠቃላዩ የዜጎች የፖለቲካ ንቃተ ህሊና፣ እንዲሁም በየአገሮቹ የሚተገበሩ ርዕዮተ ዓለሞችን ለመረዳትና አንዱን ከአንዱ ለመለየትና ለመምረጥ ዕድል እንደሚሰጥ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የሲቪክ ማኅበራት በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ዓላማዎችን ለማስፈጸም የሚቋቋሙ ቢሆንም፣ የተቋማቱ የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎና ዜጎችን ከማንቃት አንፃር የሚጫወቱትን ሚና ከመገምገም አንፃር፣ ‹‹በአንድ አገር የሚገኙ የሲቪል ማኅበራትን አደረጃጀትና አሠራርን በመቃኘት የአገሪቱን የፖለቲካ ባህልንና የዕድገት ደረጃን መረዳት ይቻላል፤›› የሚለው አስረጂም፣ እነዚህ ተቋማት ከፖለቲካውና ከልማቱ አንፃር ምን ያህል ሚና እንደሚጫወቱ አመላካች ነው፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በተለይ ደግሞ የሲቪል ማኅበራቶችን ሚናና ምንነትን በሚያጠኑ ምሁራን መካከል በጉዳዩ ላይ ወጥ የሆነ ብያኔ እንደሌለ የተለያዩ ጽሑፎች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ በተለይ የሲቪል ማኅበራትንና (Civil Society Organizations) መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን (Non Governmental Organizations) መካከል ግልጽ የሆነ የልዩነት መስመር አለመኖርን በማውሳት፣ በጉዳዩ ላይ ወጥ የሆነ አረዳድ ወይም ብያኔ እንዳይኖር አድርጓል በማለት የሚገልጹም አሉ፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ የየአገሮቹን ቀደምት ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸውን ባህላዊ ተቋማትን በማንሳት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለእነዚህ ተቋማት የተሰጡ ብያኔዎች የእነዚህን ቀደምት ባህላዊ ተቋማትን ባህሪና አደረጃጀት ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ መደራጀት አለባቸው በማለት ይሞግታሉ፡፡

እንዲህ ያለውን ሙግት ለሚያቀርቡ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ሌሎች የዘርፉ ምሁራን የሚሰነዝሩት የመልስ ምት አለ፡፡ በእነዚህ ምሁራን ዓተያይ መሠረት ‹‹ቀደምት ወይም ባህላዊ ተቋማቱ የሚያተኩሩት በዋነኛነት በመረዳዳት መንፈስ ላይ በመሆኑ ‹ዘመናዊ› የሲቪክ ማኅበራት የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ከመፍጠር፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ላይ እንዳይሠሩ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ፤›› ሲሉም የላይኛውን ሙግት ውድቅ ያደርጉታል፡፡

ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃር ሲታይ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፣ የሲቪል ማኅበራቱ ቁመና በየዘመናት የነበሩ መንግሥታትን ባህሪ የሚያመላክቱ ነበሩ፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ባለሙያው አቶ ወንድወሰን ተሾመ እንደሚሉት ደግሞ፣ የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ በባህላዊ አደረጃጀት አማካይነት መሠረቱን የጣለ ነው፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ አብዛኛዎቹ በዕርዳታ ሥራ ላይ ያተኮሩ አገር በቀልም ሆነ የውጭ የሲቪል ማኅበራት ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በአገሪቱ ባህላዊ ዕቁብ፣ ዕድርና ደቦ ወዘተ. የመሳሰሉ አደረጃጀቶች በተለይ እርስ በርስ ከመረዳዳት አንፃር ያለውን የሲቪል ማኅበረሰብ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል በማለት ያስረዳሉ፡፡

በተለይ በንጉሡም ሆነ በደርግ ዘመን የሲቪል ማኅበራት ሚና በሃይማኖት ወይም በሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ የታጠሩ እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደነበር ጽሑፎች ያመላክታሉ፡፡

በ1983 ዓ.ም. የተከሰተው የሥርዓት ለውጥ ግን በፖለቲካ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ በርካታ የሲቪል ማኅበራት እንዲመሠረቱ በር ከፍቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህም ቢሆኑ ዋነኛ ተግባራቸውን ለመወጣት ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለመታዘብ እንደተቻለው እነዚህ ማኅበራትም ቢሆኑ ሥልታዊ በሆነ መንገድ የተቋቋሙለትን ዓላማ ለማሳካት እንዳይችሉ፣ በተለምዷዊው የሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ እንዲያተኩሩና እንዲታጠሩ ሲገደዱ ይስተዋል ነበር፡፡

የሲቪል ማኅበራት ዴሞክራሲን የማጎልበት ሚና ላይ በርካታ ጽሑፎችን ያቀረቡት ካሳሁን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በፊት የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ አትኩሮታቸው በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ያተኮረ እንደሆነ በመግለጽ፣ በእሳቸው ጥናት መሠረት ቅድመ ምርጫ 97 ከነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ 74 በመቶ የሚሆኑት ትኩረታቸው በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ጽፈዋል፡፡

ምርጫ 97

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ካከናወናቸው ምርጫዎች መካከል፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ሊጣልበት የሚችለው አጋጣሚ የተፈጠረው በምርጫ 97 ወቅት ነበር የሚለው ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡

ምርጫ 97ን ልዩ ከሚያደርጉት ክንውኖች መካከል የገዥው ፓርቲ ምርጫውን እንከን አልባ ለማድረግ ቃል መግባቱ ብቻ ሳይሆን፣ በገዥው ፓርቲ መልካም ፈቃድ ገርበብ ያለው በር በርካታ የሲቪል ማኅበራት ዜጎችን ለማንቃትና ለማደራጀት፣ እንዲሁም የመራጮች ትምህርት በማዘጋጀት ዜጎች በፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በምርጫ ላይ የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ከፍተኛ የሆነ የማንቃት ሥራ በማከናወናቸው ጭምር እንጂ፡፡

ምርጫ 97 በተማቋቋ ሁኔታ ተጀምሮ ለብዙዎችም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብልጭታ አሳይቶ አሳዛኝ በሆነ መንገድ በበርካቶች ሞትና በብዙዎች እስር መጠናቀቁ፣ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ወደ ኋላ መልሶታል፡፡

በእስርና በሞት የተቋጨው ምርጫ 97 ከዚህም ባሻገር ለበርካታ አፋኝ ሕጎች መውጣትና መተግበር ዋነኛው ምክንያት ነበር፡፡ በወቅቱ መንግሥት ካወጣቸው ሕጎች መካከል ደግሞ የሲቪል ማኅበራትን አሠራር የገደበው ሕግ አንዱ ነው፡፡

በወቅቱ በወጣው ሕግ መሠረት በሰብዓዊ መብቶች፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበትና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚያከናውን ተቋማት የገቢ ምንጫቸው ከአገር ውስጥ ብቻ እንዲሆን የሚያስገድድ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ የበርካታ ተቋማት አቅም ተሽመድምዶ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን የማያከናውኑበት ደረጃ ላይ ደርሰው በርካቶች መዘጋታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ምርጫውን ተከትሎ ከባድ የሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ የተወሰነባቸው የሲቪል ማኅበራትን አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች የሚሰነዘሩ ሲሆን፣ የደረሰባቸውን መገፋት የሚቃወሙ እንዳሉት ሁሉ የደረሰባቸው መገፋት ምንጩ የራሳቸው ፈር የሳተ የፖለቲካ ተሳትፎ ነው በማለት ተቋማቱን የሚተቹም አሉ፡፡

ከዚህ አንፃር የተቋማቱ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ እንደነበርና የሚጠበቅባቸውንና የባህሪያቸው የሆነውን ለማንኛውም ወገን ያለመወገን ሚናቸውን ዘንግተውት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ሚናን ተጫውተዋል የሚለውን የመንግሥት ወቀሳ የሚጋሩ አሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ተቋማቱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መዳበር ከሚጫወቱት ሚና አንፃር ከፍተኛ በሆነ የመንግሥት በጀት ወደ ምርጫ የገባውን ኢሕአዴግ ሊቋቋሙ የማይችሉትን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሐሳቦች፣ ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንፃር የተጫወቱት ሚና የማይናቅና ተገቢ ነበር ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡

በእነዚህ ሁሉ ሙግቶችና ክርክሮች መሀል ያለፈው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ሚና ተወስኖ ከነበረው ሚናቸው እንዲላቀቁ የሚያስችለው አዲሱ የሲቪል ማኅበራት ሕግ መውጣት ደግሞ በሰብዓዊ መብቶች፣ በዴሞክራሲ፣ እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚያስችላቸው ተስፋ የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው፡፡

በተለይ የተለያዩና ፅንፍ የረገጡ ፖለቲካዊ ዓተያዮችና አረዳዶች ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ ነገሮችን ከማላዘብና ከማረጋጋት አንፃር ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ በሚል የሲቪል ማኅበራት በመጪው ምርጫ ላይ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የሚመክሩና የሚያሳስቡም እንዲሁ በርካቶች ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ ቃል የገቡ ሲሆን፣ ቃል ከተገባላቸው የሕግ ማሻሻያዎች መካከል ሒደቱን ጨርሶ የተሻሻለው ይህን ዘርፍ የሚመለከተው ብቻ መሆኑ ተቋማቱ ለመጪው ምርጫ የተሻለ ሚና እንዲጫወቱ በር ከፋች ነው በማለት የሚገልጹትም አሉ፡፡

ከዚህ አንፃር መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ከተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ጋር በቀጣዩ ምርጫ ላይ የውይይት መርሐ ግብር ያካሄደው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)፣ በቀጣዩ ምርጫ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ማስመዝገብ የሚችል አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲመረጡ እሠራለሁ በማለት ሚናውን ለመጫወት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

በርካታ ማኅበራትን ያቀፈው ኮንፌዴሬሽኑ በሥሩ በርካታ ሠራተኞች ከመኖራቸው አንፃር፣ እንዲህ ያለውን ተነሳሽነት ወስዶ ከአሁኑ የዜጎችን ሰላምና ልማትን ለሚያስቀድም ሥርዓት መዘርጋት እንደሚሠራ መግለጹ በመልካም ጎኑ የተነሳለት ጉዳይ ነው፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን የሲቪል ማኅበራት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ግቡን እንዲመታ፣ የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን የሚሰነዝሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰቡ ዓይነተኛ ሚናውን ይጫወት ዘንድ ወጥ የሆነ ፍኖተ ካርታ እንደሚያስፈልግ የሚገለጽ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበራት በጋራ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ወጥ የሆነ አቋምና አረዳድ በመያዝ፣ በመጪው ምርጫ በዜጎች የምርጫ ትምህርትና ፖለቲካ ንቃተ ህሊና መፍጠር ላይ ተገቢውንና የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ይመክራሉ፡፡

ከእነዚህ ባለሙያዎች የሚሰነዘረው ምክረ ሐሳብ የሲቪል ማኅበራት የሚጠበቅባቸውን እውነተኛ ሚና ይጫወቱ ዘንድ፣ የመንግሥትን ቅቡልነት መቀበልና ይህንን ማስተማርና ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ከምርጫ 97 ወዲህ መንግሥት የሚመሠርተው ኢሕአዴግ የቅቡልነት ጉድለት (Legitimacy Deficit) እንዳለበት የሚነገር ቢሆንም፣ የሲቪል ማኅበራቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ከማተኮርና ከመንግሥት ጋር ባላንጣነት ውስጥ ገብተው እንቅስቃሴያቸው ከሚታጎል፣ በምርጫ የሚያምን ዜጋን በማብቃት ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዲመሠረት መሥራት እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ፡፡

ለዚህ መከራከሪያቸውም በድኅረ ምርጫ 97 በመንግሥትና በሲቪል ማኅበራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና መካከር ተቋማቱን ምን ያህል እንዳሽመደመዳቸው በማስታወስ፣ አሁን እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሲቪል ማኅበራት በብልኃት ሚናቸውን እንዲወጡም ያሳስባሉ፡፡

ሌላው የሚሰነዘረው ማሳሰቢያ ደግሞ ሲቪል ማኅበረሰቦቹ የቆሙለትን ዓላማ በግልጽ በማስረዳት መንግሥትን መጠየቅና መደራደር መጀመር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በየዘርፉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲኖሩ ማግባባትና የመሳሰሉ ሐሳቦችን በማንሳት፣ ውይይትና ድርድር ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው ይመክራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ማኅበራቱ ከመንግሥትም ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ጥብቅ ትስስር መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባሉ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ግን ነፃነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማስጠበቅ እንደሚኖርባቸውም ያስጠነቅቃሉ፡፡ እንዲሁም እነዚህ ማኅበራት በተጨባጭ መረጃና ማስረጃዎች መሠረት፣ ዜጎችን የማስተማርና የማንቃት ሥራቸውን ማከናወን እንደሚኖርባቸው ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

ከላይ በዋነኛነት የተጠቀሱት ምክረ ሐሳቦችን መተግበር በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ 2012 የሲቪል ማኅበራት ዓይነተኛ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል ተብሎ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ሐሳቦችን አካተው የሲቪል ማኅበራት ሚናቸውን መጫወት ይችላሉ ብሎ የሚጠብቁም በርካቶች ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን በተለያዩ አገሮች እንደታየው የአገሪቱን የፖለቲካ ባህል ከመለወጥ አንፃር ሲቪል ማኅበራት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ መሠረት የአገሪቱ ሲቪል ማኅበራት ይህንን ሚናቸውን ለመጫወት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? የሚለው ጥያቄ የምላሽ ፍንጭ የሚያሳየው በሚጠበቀው ምርጫ 2012 በሚያደርጉት ተሳትፎና ውጤት ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -