Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፕሮራም (ፒዳ) በመባል የሚታወቀው አኅጉራዊ ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሊፈጥሩ የሚችሉ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በማልማት ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልበት ዕድሎች እንዳሉ ተጠቆመ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የተጀመረው የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፕሮግራም ዋና ዓላማ የአፍሪካ አገሮችን በመንገድ፣ ውኃ፣ በኢነርጂና በአይሲቲ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮጀክቶች በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ኮሪደሮች መፍጠር ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን ሁለተኛውን የፒዳ ፖሊሲ ውይይት፣ ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን በኢኳተሪያል ጊኒ መዲና ማላቦ ከተማ አካሂዷል፡፡

በጉባዔው ላይ የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ጉዳዮች ባለሥልጣን ኃላፊዎች የተካተቱበት ልዑክ ተሳትፏል፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ (ኢነርጂ ዘርፍ) ፍሬሕይወት ወልደሃና (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የመሠረተ ልማት መጓደል የሁሉም የአፍሪካ አገሮች ችግር በመሆኑ በአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመው የመሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ተቋም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት አባል አገር ከፒዳ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደምትሆን ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር የሚያስተሳስሯትን የመንገድ፣ የኢነርጂና የኮሙዩኒኬሸን የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ፕሮግራሞች ለማጠናከር እንደሚያስችላት ተናግረዋል፡፡ ፒዳ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የአፍሪካ አገሮች በመሠረተ ልማት የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶች መርጦ፣ ከአባል አገሮችና ከዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶችና አገሮች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮግራም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

‹‹አሁን ባለንበት ሁኔታ ኮሜርሻል ብድር የመውሰድ ፍላጎት የለንም፡፡ ለእኛ የሚጠቅመን በረዥም ጊዜ የሚከፈል ወለዱ አነስተኛ የሆነ ብድር (Soft Ioan) በመሆኑ፣ ይህን ለማግኘት ፒዳ ሰፊ ዕድል አለው፤›› ያሉት ፍሬሕይወት (ዶ/ር)፣ አንድን ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት አንድ አገር ብቻውን ከሚያከናውነው ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ቢገነቡት በወጪ መጋራት፣ በቁጥጥርና በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በኢነርጂነው ዘርፍ በፒዳ ፕሮግራም አማካይነት በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ማዕቀፍ ውስጥ የኃይል ትስስርን የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ እንደምትችል ገልጸዋል፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ (የውኃ ዘርፍ) ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በፒዳ ፕሮግራም አማካይነት የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን ሊያጠናክሩ የሚያስችሉ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የፋይበር ኦፕቲክስ ዝርጋታ ፕሮጀክቶች ልትተገብር እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡ ፕሮግራሙ የኢኮኖሚ ትስስር ለሚፈጥሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የገንዘብ ምንጭ ለማፈላለግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ኢትዮጵያ የምታስተዳድረው ወደብ ባይኖራትም፣ ፕሮግራሙ አገሮች በኢኮኖሚ ኮሪደሮች አማካይነት ወደቦችን በጋራ መጠቀምን የሚያበረታታ በመሆኑ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ከቪክቶሪያ ሐይቅ ተነስቶ ሜዲትራኒያን የሚደርሰው የውኃ ትራንስፖርት ንድፍ ኢትዮጵያንም የሚያካትት በመሆኑ፣ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ፕሮጀክት እንደሆነ ነጋሽ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በናይል ወንዝ ላይ የሚካሄዱ የውኃ ትራንስፖርት ፕሮጀክቶችን የሚያጠቃልል ስለሆነም፣ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ጥቅም በማስጠበቅ እንደሚካሄድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚወጠኑ ፕሮጀክቶች ቀደም ሲል በነበረው አብዛኛው የዓባይ ተፋሰስ አባል አገሮች የተስማሙበት የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ መቀረፅ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በጥር 2012 በአዲስ አበባ በተካሄደ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የፀደቀው የፒዳ ፕሮግራም 51 ፕሮግራሞች፣ 433 የትራንስፖርት፣ የኢነርጂ፣ የአይሲቲና የድንበር ተሻጋሪ የውኃ ፕሮጀክቶች ያቀፈ ፕሮግራም ነው፡፡ የመሠረተ ልማት ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ በአጠቃላይ 360 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የመጀመርያው ክፍል ብቻ 68 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስፈልገው ተገምቷል፡፡

በመጀመርያው ዙር ከተመረጡት 433 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ 35 በመቶ ያህሉ ተግባራዊ እንደተደረጉ ተገልጿል፡፡ የመጀመርያው የፒዳ ፕሮግራም እ.ኤ.አ. በ2020 የሚጠናቀቅ በመሆኑ እስከ 2030 የሚዘልቀው ሁለተኛው ክፍል በመነደፍ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በማላቦ በተካሄደው ሁለተኛው የፒዳ ፖሊሲ ውይይት ላይ በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፍላጎት ላይ በርካታ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን፣ በተለይ በፒዳ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በሚተገበረው ሁለተኛ ክፍል የፕሮጀክት ምዘና ላይ ሰፊ ምክክር ተካሂዷል፡፡

አፍሪካ በየዓመቱ በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ 75 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ የምታፈስ ሲሆን፣ ከ130 እስከ 170 ቢሊዮን ዶላር ያህል የፋይናንስ እጥረት እንደሚያጋጥም ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች