ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልን በተመለከተ ኢትዮጵያና ሱዳን የተናጠል አማራጮቻውን የሚቀርቡበት የሦስትዮሽ የጋራ ቴክኒክ ባለሙያዎች ስብሰባ፣ በሱዳን ከተማ ካርቱም ከሰኞ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን የባለሙያዎች ቡድን ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን የህዳሴ ግድቡ በውኃ በሚሞላበት ወቅት ከግምት ውስጥ የሚያስገቡዋቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በመንተራስ፣ ውኃ የመሙላት ሒደቱ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚገልጽ የጥናት ሐሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
የህዳሴ ግድቡን በውኃ ለመሙላት ሦስት ዓመት በቂ እንደሆነ በጥናታቸው ቢያረጋግጡም፣ የተለያዩ ቴክኒካዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ግድቡን ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለመሙላት እንደሚቻል የሚገልጽ የመደራደሪያ ሰነዳቸውን በውይይቱ ላይ እንደሚያቀርቡ ሪፖርተር ከባለሙያዎቹ መካከል አንዱና የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) ከሳምንት በፊት ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
እየተካሄደ ባለው የሦስቱ አገሮች የባለሙያዎቹ ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ፣ በሱዳን የባለሙያዎች ቡድን ግድቡ በውኃ የሚሞላበትን ሒደት የያዘ ሰነድ በተመሳሳይ ቀርቦ ድርድር እንደሚደረግበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በካይሮ ተካሂዶ በነበረው የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ፣ ግብፅ የግድቡ ውኃ ሙሌትን በተመለከተ ሌሎቹን አገሮች ሳታማክር ያዘጋጀችውን ሰነድ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በግብፅ በተናጠል የቀረበውን ሰነድ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጓን መዘገባችን ይታወቃል፡፡
ግብፅ በተናጠል ባቀረበችው በዚህ ሰነድ ከተመለከቱትና በኢትዮጵያ መንግሥት በእጅጉ ከተተቹት ነጥቦች ዋነኛው፣ “የግድቡ የውኃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ እንድትለቅና ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ ዝቅተኛ የውኃ ይዞታ የግድቡን 165 ሜትር መሆኑን ማረጋገጥና የአስዋን የውኃ መጠን በዚህ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውኃ ላይ መልቀቅ ይኖርባታል፤” የሚለው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግብፅ ያቀረበችውን ሐሳብ ሉዓላዊነትን የሚዳፈርና በትብብር ላይ ተመሥርቶ ከተጀመረው ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት መንገድ ያፈነገጠ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ አድርገዋለች፡፡ ይህንኑ የግብፅ ያልተገባ መንገድና የኢትዮጵያን አቋም በተመለከተም የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሒሩት ዘመነ ጋር በመሆን፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችን ሰሞኑን በመጥራት ግልጽ አድርገዋል፡፡
በሱዳን እየተካሄደ በሚገኘው የባለሙያዎቹ ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን በኩል የሚቀርበው ሰነድ፣ በሦስቱ አገሮች መካከል መግባባት እንዲደረስ ወሳኝነት እንደሚኖረው የሚታወቅ ሲሆን፣ ሱዳን በግብፅ ተካሂዶ በነበረው ስብሰባ ላይም ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ ጌድዮን ዶ/ር ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የባለሙያዎቹ ቡድን በዚህ ስብሰባ የጋራ ስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ፣ የሚደርሱበት የስምምነት ሐሳብ በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ይቀርባል፡፡ ሚኒስትሮቹ በሚያርጉት ስብሰባ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ ግን ጉዳዩ ‹‹ቡድን ዘጠኝ›› በመባል ለሚታወቀው የሦስቱ አገሮች መሪዎች፣ የመከላከያ ሚኒስትሮችና የደኅንነት ኃላፊዎች አባል ለሆኑበት አካል እንደሚመራ ለማወቅ ተችሏል፡፡