Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሃይማኖቶች መሠረታዊ መርህና አስተምህሮ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላት እንዳሉ ተጠቆመ

ከሃይማኖቶች መሠረታዊ መርህና አስተምህሮ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላት እንዳሉ ተጠቆመ

ቀን:

‹‹ኢትዮጵያውያን ሰላማቸውንና አንድነታቸውን ነቅተው መጠበቅ አለባቸው››

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ

የሃይማኖት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በከፍተኛ የመተባበር መንፈስ ውስጥ ቢሆኑም፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ከሃይማኖቶች መሠረታዊ መርህና አስተምህሮ ጋር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ጽንፈኛ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች በመታየት ላይ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡

ማክሰኞ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ሲያካሂድ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን እንደገለጹት፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን በሃይማኖቶች መካከል ለዘመናት በጥልቅ መሠረት ላይ የተገነባ የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር አኩሪ እሴት አለን፡፡ ይህንንም በተተኪ ትውልዶች ጠብቆ ለማስቀጠል የሃይማኖት መሪዎች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በከፍተኛ መተባበር እየሠሩ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩና እየተገኙ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው፣ ‹‹ችግሩ የብሔር የማንነትና ሃይማኖታዊ እንዲመስል በማድረግ፣ አንዱን በሌላው ላይ ለማነሳሳትና በመካከላቸው አለመተማመን ለመፍጠር በቤተ እምነቶችና በምዕመናን ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን እያደረሱ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ቤተ እምነቶች ሌላ ዓላማ ላላቸው አካላት ጉዳይ ማስፈጸሚያነት እንዳይውሉ የሃይማኖት ተቋማት፣ መሪዎችና አስተማሪዎች ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችንና የጋራ የሆኑ የሃይማኖት እሴቶችን መሠረት በማድረግ፣ ይህንን ሁኔታ በማክሸፍ አገራዊ ሰላምንና አንድነትን ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በአንዳንድ ቤተ እምነቶች ውስጥ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በውስጥ አሠራርና ደንቦች ከመፍታት ይልቅ፣ ‹‹ችግር ደረሰብን›› የሚሉ ወገኖች ወደ ተለያዩ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት መፍትሔ ፍለጋ መሄዳቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

አስተምህሮታቸውን በማይፃረር ሁኔታ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓቶች በመከተልና በማስተዋወቅ የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ፣ ሦስተኛ ወገኖች በሃይማኖት ሽፋን መፈጸም የሚፈልጉትን መፈጸሚያ እንዳይሆኑም ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ መከባበርና ሰላም በኢትዮጵያ ላለው ብዝኃነትና አብሮ ለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ ለዘላቂ ልማትም መሠረታዊና ቁልፍ ቅድመ ሁኔታ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ሃይማኖትንና እውነተኛነትን ወደ ምዕመናን ለማስረፅና የሁሉም የሃይማኖቶች ተከታዮች በፍፁም መከባበርና መዋደድ እንዲኖሩ፣ መሪዎቹ አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ የአገር ሰላምና አንድነት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ማድረግ ከፈጣሪም ሆነ ከሚያገለግሉዋቸው ምዕመናን፣ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ ማስታወስ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አቡነ ጎርጎሪዎስ አክለው እንደተናገሩት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያና በልዩ ልዩ መንገዶች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እየተካሄደ ያለው ግጭት፣ አለመከባበርና ቅስቀሳ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የለውም፡፡ የተወገዘ ተግባር መሆኑን በመረዳትም ሁሉም ኢትዮጵያውያን መከባበርን በማስቀደም፣ ሰላማቸውንና አንድነታቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ በማሳሰብ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታዋን መልዕክት አጠናክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በ11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው፣ የ2011 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርትን አዳምጧል፡፡ ለ2012 በጀት ዓመት የሥራ ዘመን በሚያከናውናቸው ዕቅዶች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...