የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው የማራቶን ውድድሮች የበርሊን ማራቶን አንዱ ነው፡፡ ባለፈው እሑድ መስከረም 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በተከናወነው በርሊን ማራቶን የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናው ቀነኒሳ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ለክብረ ወሰን የቀረበ ፈጣን ሰዓት አስመዝግቦ ነው፡፡ በዕለቱ ቀነኒሳ በቀለ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች ቀዳሚው ይሆናልም ተብሏል፡፡
የበርሊን ማራቶን ክብረ ወሰን በኬንያው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በ2018፣ 2፡01.39 የተመዘገበው ሲሆን፣ ቀነኒሳ በሁለት ሰከንድ ዘግይቶ የገባው 2፡01.41 ነው፡፡ በቅርቡ ከትራክ ውድድር ወደ ጎዳና ውድድር ፊቱን ያዞረው ቀነኒሳ በቀለ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማራቶን ለመወዳደር የሚያበቃውን ዝግጅት አድርጎ ባደረጋቸው ውድድሮች ይህ ነው የሚባል ውጤት ማስመዝገብ ሳይችል መቆየቱ ይታወሳል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ውድድሮችን አቋርጦ የወጣባቸው ጊዜያት የታየባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡
በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች እንደ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ክብረ ወሰኖችን በማስመዝገብ የሚታወቀው ቀነኒሳ በቀለ፣ በማራቶን ተደጋጋሚ ውድድሮችን ሲያደርግ ቢቆይም፣ እንደ ዘንድሮው የበርሊን ማራቶን የተሳካ፣ ምናልባትም ከዚህ በኋላ በማራቶን የማይታመን ብቃት እንደሚያሳይ ምልክት ያሳየበትን ውጤትና ሰዓት ያስመዘገበበት ወቅት እንደሌለ እየተነገረለት ይገኛል፡፡
በበርሊን ማራቶን በኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ የተያዘውን በማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበር የቀረው ሁለት ሰከንድ ብቻ እንደነበር ውድድሩን ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበውን 2፡01.41 ሴኮንድ በመመልከት መረዳት ተችሏል፡፡ ውድድሩን ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቁት ብርሃኑ ለገሰና ሲሳይ ለማ ሲሆኑ፣ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደባቸው ጊዜ 2 ሰዓት 02 እና 2 ሰዓት 03 መሆኑ ነው፡፡ በሴቶች መካከል በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር እሸት በከሪና ማሬ ዲባባ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ጨርሰዋል፣ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2፡20.14 እና 2፡20.22 መሆኑ ታውቋል፡፡