Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሦስትዮሽ ትብብር ሞዴል አበርክቶ

ፒፕል ቱ ፒፕል የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግና በትምህርት ለመደገፍ በአሜሪካ የተቋቋመና በአዲስ አበባ ቢሮ የከፈተ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ የኢትጵያውያን ዳያስፖራዎችንና ወዳጆችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል መሥራት ከጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1999 በእናውጋው መሃሪ (ዶ/ር) የተመሠረተውና ኢትዮጵያውያን የጤናው ዘርፍ ዳያስፖራዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ወዳጆችን የሚያሳትፈው ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ይተገብራል፡፡ ድርጅቱ ያደረገው አበርክቶ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የሦስትዮሽ ትብብር የሚል ፍልስፍና ትከተላላችሁ፡፡ ምን ያመለክታል?

ዶ/ር እናውጋው፡- ፒፕል ቱ ፒፕል (ፒቱፒ) ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ተቋማትን ከተቋማት፣ ባለሙያዎችን ከባለሙያዎች እንደ ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ የምዕራባውያን በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚገኙ ተቋማትንና በዓለም አቀፍ በሚገኙ ዳያስፖራዎች መካከል ያለውን መስተጋብር የሦስትዮሽ ትብብር እንለዋለን፡፡ ድርጅቱም የዕውቀት፣ የሀብትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እየሠራ ይገኛል፡፡

የምንከተለው የሦስትዮሽ ትብብር፣ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካና በምንሠራባቸው ሌሎች አገሮች የተሰደዱ ምሁራን ከውጭ ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት መልሰው ለአገራቸው እንዲያካፍሉ ይረዳናል፡፡ የድርጅቱ አባላት የኢትዮጵያን ባህልና ወግ እንዲያውቁና ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖርም እየረዳን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዋና ዋናዎቹ ፕሮግራሞቻችሁ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር እናውጋው፡- ጤና፣ የሰው ኃይልን ማበልፀግና ትምህርት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ፕሮግራም ከአጋዥ ተቋማት ጋር በመሆን አባላቶቻችን ችግር ፈቺ  እንዲሆኑ፣ ልምድና ክህሎታቸውን እንዲያካፍሉ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ካንሰር ሕክምና ላይ ለመሥራት መንቀሳቀስ ጀምራችኋል? ከምን ደረጃ ደርሷል?

ዶ/ር እናውጋው፡- በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ደረጃውን የጠበቀ የካንሰር ሕክምና ማግኘት ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡበት ነው፡፡ ጤና ሚኒስቴር በካንሰር ከሚያዙ 150 ሺሕ ሰዎች አንድ በመቶው ብቻ በተወሰነ መልኩ የካንሰር ሕክምና እንደሚያገኙ ይገምታል፡፡ እኛ ይህንን መቀየር እንፈልጋለን፡፡ ፒፕል ቱ ፒፕልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጋራ የተሟላ የካንሰር ሕክምና መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አብረን እየሠራን ነው፡፡ ግባችን ምርመራውና ሕክምናው በአንድ ጣራ ሥር ተሟልቶ የሚሰጥበትን ማመቻቸት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሴቶች ማደሪያ ማዕከል መሥርታችኋል? የሚሰጠውን ድጋፍ ቢገልጹልን?

ዶ/ር እናውጋው፡- እ.ኤ.አ. በ2004 የተመሠረተው አማኑኤል የሴቶች ማደሪያ ማዕከል በደብረ ማርቆስ ይገኛል፡፡ ቤተሰቦቻቸው በኤችአይቪ ኤድስ ምክንያት ቀውስ ውስጥ የገቡ ቤተሰብ ሴት ልጆችን ወደ ማዕከሉ እናስገባና የትምህርትና ሌሎች ድጋፎችን እናደርጋለን፡፡ በሕዝብ ትምህርት ቤት የሚማሩ 50 ሴት ተማሪዎችን እንረዳለን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 20ዎቹ ሙሉ ለሙሉ በማደሪያ ተቋሙ ገብተው እገዛ የሚያገኙ ሲሆን፣ 30 ያህሉ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር ሆነው ማዕከሉ የሚሰጠውን ድጋፍ ማለትም የትምህርት፣ የምግብ፣ የልብስ፣ የመዝናኛ፣ የምክርና በማዕከሉ ከማደር መልስ ያሉትን ድጋፎች በሙሉ የሚያገኙ ናቸው፡፡

በማዕከሉ ከነበሩት ሴት ልጆች ውስጥ 26ቱ የሕክምና ዘርፍን ጨምሮ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና (ዩኒቨርሲቲ መግቢያ) ከተፈተኑ ስምንት ተማሪዎች ሰባቱ አልፈዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ሕክምና ፌሎውሽፕ መጀመራችሁ ምን አስተዋጽኦ አበረከተ?

ዶ/ር እናውጋው፡- እ.ኤ.አ. በ2005 ለ80 ሚሊዮን ሕዝብ የሚያገለግሉት ስምንት ኒውሮሎጂስት (የነርቭ ሐኪም) እና ሁለት ኒውሮሰርጅን (የነርቭ ቀዶ ሕክምና ሐኪም) ብቻ ነበሩ፡፡ ፒፕል ቱ ፒፕል ከማዮ ክሊኒክና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኒውሮሎጂ ፌሎውሺፕ ሥልጠና መሠረት ጥሏል፡፡ የመጀመርያዎቹ ሠልጣኞች እ.ኤ.አ. በ2006 ገብተው በ2008 ተመርቀዋል፡፡ አሁን ላይ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኒውሮሎጂ ፕሮግራም፣ ሴሚናርና ሌሎችንም እያዘጋጀ ተከታታይ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ፒቱፒ ለዚህ የሚያገለግሉ  ባለሙያዎችን ከዓለም እያሰባሰበ ፕሮግራሙን እንዲያግዙ ያደርጋል፡፡ የድርጅቱ በጎ ፈቃደኞች ቴሌሜዲስን እየተጠቀሙ በኢትዮጵያ ያሉትን ይረዳሉ፡፡ ይህ የሦስትዮሽ ትብብር ሞዴላችን ያስገኘልን ጥቅም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ላይ ያላችሁን አስተዋጽኦ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር እናውጋው፡- እ.ኤ.አ. በ2009 ፒቱፒ ከአሜሪካን ኢንተርናሽናል ሄልዝ አሊያንስ፣ ከዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅተናል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአስቸኳይ ሕክምና ሥርዓተ ትምህርት አልነበራትም፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ በኢትዮጵያ በዘርፍ ፈተና ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ የሰጠ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ መምህራን የአሠልጣኝ ሥልጠና እየሰጡ ይካሄድ ነበር፡፡ በ2015፣ 90 በመቶ የሚሆኑት ትምህርቶች በኢትዮጵያውያን መሰጠት ጀመሩ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመጀመርያውን የድንገተኛ ሕክምና ትምህርት ክፍልም ከፍቷል፡፡ የውጭ አካላት ባይተባበሩን ኖሮ የድንገተኛ ሕክምና ትምህርቱ ውጤታማነት አይፋጠንም ነበር፡፡ አሁን ላይ በድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ማፍራት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ፒቱፒ በኬንታኪ ክሊኒክ ከፍቶ ነፃ ሕክምና ይሰጣል፡፡ ማን ነው ተጠቃሚው?

ዶ/ር እናውጋው፡- በአሜሪካ ካላቸው ገቢ አንፃር ሕክምና ማግኘት የማይችሉ አሉ፡፡ በመሆኑም በኬንታኪ ክሊኒክ ከፍተን መክፈል ለማይችሉና የጤና መድን የሌላቸውን እናክማለን፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 የተከፈተው የሕክምና ማዕከል በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ይሠራል፡፡ የጤና አገልግሎት ማግኘት ሰብዓዊ መብት ሲሆን፣ በአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ግለሰቦችና ሌሎች ድርጅቶች ይረዱናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...