Monday, October 2, 2023

ጠቅላላ ምርጫና የሕዝብ ቤት ቆጠራ ከፊቱ የሚጠብቁት ምክር ቤት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከምርጫ 2007 ዓ.ም. በኋላ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና አጋሮቹ አማካይነት የተዋቀረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የመጨረሻ የሥራ ዘመኑን መደበኛ ስብሰባ ለማከናወን የሚቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 ቀን ነው፡፡ በዚህ መሠረት የፊታችን ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ማለትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሚያደርጉት ንግግር ይከፈታል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደሚስተዋለው በዕለቱ ፕሬዚዳንቷ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የመንግሥትን ዓመታዊ የትኩረት አቅጣጫ የሚያሳውቁ ሲሆን፣ ኩነቱም ከየምክር ቤቶቹ አባላት በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ተጋባዥ ፖለቲከኞች በእንግድነት ይታደሙበታል፡፡

ከየምክር ቤቶቹ አባላት በተጨማሪ ሌሎች እንግዶች የሚገኙትም በተለይ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላት የመንግሥትን ዓመታዊ ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫን ለመረዳት፣ በዚህ መሠረትም አሠራራቸውንና ከአገሪቱ ጋር የሚኖራቸውን ቀጣይ የግንኙነት አቅጣጫ ለመቃኘት እንዲረዳቸው በማሰብ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ በነበሩ ሦስትና አራት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ይካሄዱ የነበሩ ሕዝባዊ አመፆችን ለማረጋጋት በማለም፣ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ዕለት ላይ ተገኝተው በሚያደርጓቸው ንግግሮች የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫዎች ይገልጹ ነበር፡፡ አብዛኞቹ በተለይም ከመልካም አስተዳደር እንዲሁም የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማስፋት አንፃር ይገቡ የነበሩ ቃል ኪዳኖች ተፈጻሚነት ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሱ የነበረ ሲሆን፣ ተፈጻሚነታቸውም እንዲሁ ጎዶሎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ለአብነት ያህልም የ2010 ዓ.ም. የምክር ቤቶቹ መክፈቻ ንግግር ወቅት ቃል ገብተውት የነበረው የምርጫ ሥርዓት እስከ መቀየር የሚደርስ ድርድርና ውይይት ከተቃዋሚዎች ጋር ለማድረግ የመንግሥትን ቁርጠኝነት ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት በአስቸኳይ ስብሰባ የፀደቀው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ስለጉዳዩ ምንም አለማለቱና የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት በነበረበት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት መቀጠሉ፣ በምክር ቤቶቹ የሚገቡ ቃል ኪዳኖች ከቃላት እንደማያልፉ ማሳያ ናቸው በማለት የሚሞግቱ አሉ፡፡

የሪፐብሊኩ አራተኛዋና የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ በምክር ቤቶቹ አባላትና በተጋባዥ እንግዶች ፊት ቀርበው የዘንድሮ የመንግሥት አቅጣጫ እንደሚገልጹ ይጠበቃል፡፡ የዘንድሮው የኢሕአዴግ የመጨረሻ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመንም፣ በምን ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣሉ ተብሎ እንዲሁ ይጠበቃል፡፡

የምክር ቤቱ ፈታኝ ሥራዎች

አምስተኛው ዙር ምክር ቤት ከአምና ተንከባለው የመጡ ሕጎችን የማፅደቅ፣ ዘንድሮ ሊካሄዱ ቀጠሮ የተያዘላቸውን ምርጫና የሕዝብና ቤት ቆጠራ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከማድረግ ባሻገር፣ በእነዚህ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣንም በእጁ የሚገኝ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች እንዲቆሙና ሰላማዊ የሆነ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በመላው አገሪቱ እንዲሰፍን፣ እንዲሁም የዜጎች ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዲወጡ የማድረግ የሁለቱም ምክር ቤቶች የቤት ሥራ እንደሚሆን የሚገልጹ አሉ፡፡

በተለይ በየሥፍራው የሚቀሰቀሱት ግጭቶችን የሚቆጣጠርና የሚያረግብ አሠራር እንዲዘረጋ የሚያስችሉ ሕጎች እንዲወጡ ማድረግ ጠቀሜታው፣ በዚህ ዓመት ይካሄዳሉ ተብለው ለሚጠበቁትና ምናልባትም ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የአገሪቱን አጠቃላይ ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ ተብለው የሚገመቱት ምርጫና የሕዝብና ቤት ቆጠራን በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው በመግለጽ፣ ምክር ቤቶቹ በዚህ ላይ አተኩረው እንዲሠሩ የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

አምና ይፀድቃሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩትና በሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት አማካይነት ጥናትና ውይይት ሲካሄድባቸው የነበሩት የፀረ ሽብርተኝነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን በአስቸኳይ አሻሽሎ ማፅደቅም፣ እንዲሁ ወሳኝ መሆኑን የሚገልጹም አሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም አምና በአስቸኳይ ስብሰባ የፀደቀው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ካስተናገደው ከፍተኛ ተቃውሞ አንፃር፣ እሱንም ሁሉንም ባሳተፈ መንገድ እንደገና መመልከት ቢቻል የሚል ምክር የሚለግሱም አልታጡም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጁን በድጋሚ መመልከት የሚረዳው፣ የዘንድሮው አጠቃላይ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ ድኅረ ምርጫ አለመረጋጋቶችና ስሞታዎችን ለማስቀረት የሚያስችል አቅም ይኖረዋል ከሚል እሳቤ በመነሳት ሲሆን፣ ጨዋታውን የሚዳኘው ሕግ ላይ ከስምምነት ሳይደረስና በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችና አባላት ተቃውሞ የሚያቀርቡበትን ሕግ መሠረት አድርጎ ወደ ውድድር መግባት በራሱ፣ የምርጫውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባው ይችላል ከሚል አጠቃላይ ድምዳሜ የሥጋት ስሜት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ፣ ‹‹እውነቱን ለመናገር ከዘንድሮው ፓርላማ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ምንም አንጠብቅም፤›› በማለት፣ የምርጫው ሕግ ሲፀድቅ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ አሁንም የተለየ ነገር ሊኖር እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡

ለዚህ ሐሳባቸው እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ደግሞ፣ ‹‹ከ65 እስከ 71 የምንሆን ድርጅቶች ሕጉ እንዳይፀድቅና እንዳይተገበር አነጋግሩን እያልን ስንጮህ ሰሚ ሳናገኝ፣ እንዲሁ በአስቸኳይ ተሰብስቦ ሕጉን አፅድቆ ከሄደ ምክር ቤት ምን ልንጠብቅ እንችላለን?›› በማለት ያጠይቃሉ፡፡

ባለፈው ዓመት የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት ጥናት መሠረት ውይይት ከተካሄደባቸው ሕጎች መካከል የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ጉዳዮችን የተመለከቱ አዋጆች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የፀረ ሽብርተኝነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጆች ሳይቋጩ በይደር ለዘንድሮ የተሸጋገሩ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅ እንዲሁም የበጎ አድራጎት አዋጆች ተሻሽለው መፅደቃቸው የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጁ የነበሩ በርካታ ማነቆዎችን በማንሳቱና ተቀዛቅዞ የነበረው የሲቪል ማኅበራት ሚና ዳግም እንዲያንሰራራ በር ይከፍታል በሚል ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅ ግን ምንም የተሻሻለ ነገር እንደሌለው፣ እንዲሻሻሉና በአዋጁ እንዲካተቱ የሰነዘርናቸው ሐሳቦች አልተካተቱም በሚል ምክንያት በርካታ የተቃውሞ ጎራው ፖለቲካ ፓርቲዎች ክፉኛ እየተቹትና እየኮነኑት ይገኛሉ፡፡

ለዚህም ነው አቶ ሙሉጌታ ዘንድሮም ቢሆን ከፓርላማው ምንም የተለየ ነገር አልጠብቅም ማለታቸው፡፡ ‹‹ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት በሰከነ መንፈስ መወያየት ጠቃሚ ነው፡፡ ሕጎች ዛሬንና የቅርብ ጊዜ ሁኔታን ብቻ ሳይሆን፣ ዘለቄታዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት በማስተዋል ቢወጡ ጥሩ ነው፡፡ በአስቸኳይ የሚወጣ ሕግ የትም አያደርሰንም፤›› በማለት፣ ፓርላማው ዘንድሮ በሚያወጣቸው ሕጎች ላይ ስክነት እንዲታይበት አሳስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት ፓርላማው በዘንድሮ እንቅስቃሴው በተለይ የፀረ ሽብር ሕጉን በአስቸኳይ እንዲያሻሽልና እንዲተገብር አቶ ሙሉጌታ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መንግሥትም በዘንድሮው አቅጣጫው በተለየ አትኩሮት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ እንዲሁም ሉዓላዊነትን ማስከበርና የሕግ የበላይነት ለማስፈን የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ዕቅዶችን በመተግበር፣ እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶችንና የደቦ ፍርድን ለማረቅ የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ቢሠራ መልካም ነው ብለን እናምናለን፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

በተመሳሳይ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ በበኩላቸው፣ ‹‹የዘንድሮው የምክር ቤቶች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ምርጫና የብሔር ግጭቶችን ማረጋጋት ነው፤›› የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በ2012 ዓ.ም. ቢያንስ የአገሪቱን አንድ አሠርት ሊበይኑ የሚችሉ ኩነቶች የሚከናወኑበት ነው በማለት፣ ፓርላማው በተለይ የብሔር ግጭቶችንና አለመረጋጋቶችን ሊያሰክኑ የሚያስችሉ አሠራሮች እንዲዘረጉ ቢያደርግ መልካም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በማሻሻያ ሒደት ላይ የሚገኙት ሕጎች ከምርጫው አስቀድሞ መጠናቀቅ እንደሚኖርባቸው በመግለጽ፣ በሒደት ላይ የሚገኙት ሕጎች ሳይጠናቀቁና ሳይፀድቁ ወደ ምርጫ መግባት ምርጫውን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል ይላሉ፡፡ ሕጎችን ማሻሻልና የብሔር ግጭቶችን ማረቅ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያሳስባሉ፡፡

አቶ ልዑልሰገድም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞች የብሔር ግጭቶችን ማስቀረት ወይም መቆጣጠር፣ ምርጫው ላይ ሊያጠላ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከማስቀረት አንፃር የሚኖረው ድርሻ ዓይነተኛ እንደሆነ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

‹‹በየአካባቢው የሚነሱ የብሔር ግጭቶችን መቆጣጠር ምርጫው በሰላም እንዲካሄድም ሆነ እንዳይካሄድ ቁልፍ ነጥብ ይመስለኛል፤›› በማለት፣ በተለያዩ ወገኖች የሚሰጡትን አስተያየቶች አቶ ልዑልሰገድ ያጠናክራሉ፡፡

ከዘንድሮው ፓርላማ ዓብይ አጀንዳ መሆን ጋር ተያይዞ የሚነሳውና ከባድ የቤት ሥራ ሊሆን ይችላል የሚባለው ደግሞ፣ በይደር ቆይቶ ዘንድሮ እንዲካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የሕዝብና ቤት ቆጠራ መርሐ ግብር ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሳይካሄድ ምርጫ ማካሄድ ከባድና አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹ አካላት ሲኖሩ፣ በተለይ ባለፉት ዓመታት ከጨመረው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ የምርጫ ክልሎችን ዳግም ማደራጀት ሊጠይቅ የሚችል ከመሆኑ አንፃር፣ ይህንንም ጉዳይ ፓርላማው በቅጡ ሊያጤነው እንደሚገባ የማያሳስቡ አካላት አሉ፡፡

አቶ ልዑልሰገድ፣ ‹‹ዞሮ ዞሮ የብሔር ግጭቶች እንዲወገዱ ምርጫውም ነፃና ፍትሐዊ መሆን የሚችልበትን ስትራቴጂ አስመልክቶ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርበታል፤›› በማለት፣ የዘንድሮ የመንግሥት አቅጣጫ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

እነዚህን ሁሉ ወሳኝ አገራዊ ኩነቶችን ለመከወን ከፍተኛ ድርሻ ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 በፕሬዚዳንቷ ንግግር ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ በሥራ ዘመናቸው ምን ዓይነት ተግባራትን ይከውናሉ? ለየትኛው ጉዳይስ ቅድሚያ ሰጥተው ይሠራሉ? የሚለው ጥያቄ በምክር ቤቶቹ የሥራ ዘመን ሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -