Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያልተገታው ግርዛት  

ያልተገታው ግርዛት  

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የተለያዩ ግንዛቤዎች ሲሰጡ፣ ፖሊሲዎች ከወጡና መተግበር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ልማዱ እየቀነሰ ቢመጣም አልተገታም፡፡  

የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የክልል ተወካዮች፣ የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት ተደርጓል፡፡  

የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮች ላይ በስፋት የሚተገበር አንዱና ዋነኛው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሲሆን፣ የሴት ልጅ ግርዛት የሴትን መብት ከመጣስም ባለፈ ከፍተኛ የጤና ችግር በማስከተል ለሞት እንደሚዳርግ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ ተናግረዋል፡፡

ግርዛት፣ ከሚፈጥረው ጠንካራ የሕመም ስሜትና የሕዋሳት መጎዳት የተነሳ ለፌስቱላ፣ በወር አበባ ወቅት ለሚፈጠር ሕመም፣ አንዳንድ የሰውነት አካል ላይ ስሜት አልባ መሆንና መደንዘዝ፣ የሚወልዷቸው ልጆችም የቀጨጩ፣ ከሚፈለገው ክብደት በታች እንዲሆኑና በምጥና ወሊድ ጊዜ በሚፈጠሩ ችግሮች ለሞት እንደሚዳርግም ጠቁመዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ የሚገኘው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ወደ 30 የሚጠጉ አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በእስያ በሚገኙ አገሮች ሲሆን፣ በዓለማችን ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናትና ሴት ልጆች ላይ በተለያየ መልኩ ግርዛት ተፈጽሟል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛት እ.ኤ.አ. በ2000 ከነበረው 80 በመቶ፣ በ2016 ወደ 65 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ቢሆንም፣ ለወደፊት ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም. በሶማሌና በአፋር ክልሎች ውስጥ 99 በመቶ ያህል ግርዛት መፈጸሙን፣ በትግራይ ክልል ደግሞ ቁጥሩ 23 በመቶ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ከሌሎች ክልሎች ከፍተኛ ቁጥርን የያዙት ሶማሌና አፋር ስለሆኑ በእነዚህ ክልሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡   

አጎራባች አገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሆነ አኃዝ እንዳላቸው፣ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በቀላሉ በመዘዋወር የሴት ልጅ ግርዛትን እንደሚፈጽሙም በውይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም በተመሳሳይ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል በመሄድ የሴት ልጅ ግርዛት እንደሚከናወን ተነግሯል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመቀነስም ከአጎራባች አገሮች ጋር በጋራ ለመከላከል፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሚኒስትሮች የጋራ ቃል ኪዳን ተፈራርመዋል፡፡ ይህንን የጋራ ቃል ኪዳን ወደ ተግባር ለመቀየር ሁሉም የበኩሉን ማድረግ ይገባል በማለት ሚኒስትር ዴኤታዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን እ.ኤ.አ. በ2025 ለማስቆም ኢትዮጵያም የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች፡፡

የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከአምሪፍ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግ፣ መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ በመሆን መሥራት እንደሚገባቸው ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...