Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 260 ሚሊዮን ዶላር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ራዕይ 2035 የዕድገት መርሐ ግብር ለቦርድ አቀረበ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 260 ሚሊዮን ዶላር አተረፈ፡፡

በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመቱ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲያገኝ፣ 189 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ እንዳገኘ ታውቋል፡፡

አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 12.1 ሚሊዮን መንገደኞችና 432,000 ቶን ጭነት ሲያጓጉዝ፣ የመንገደኞች ቁጥር በ17 በመቶ እንዳደገ ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህም መሠረት የመንገደኞቹ ቁጥር በ17 በመቶ በማደጉ 12.1 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም አየር መንገዱ በታሪኩ ያጓጓዘው ትልቁ የመንገደኞች ቁጥር እንደሆነ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የ2011 በጀት ዓመት ፈታኝ ወቅት ነበር፡፡ ‹‹ምን አልባትም በታሪካችን ትልቁ የፈተና ወቅት ነበር ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የተከሰተው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አሳዛኝ አደጋ፣ አየር መንገዱ የገጠመው ከባድ ፈተና እንደነበር አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የምንወዳቸውን የሥራ ባልደረቦቻችንንና የምናከብራቸውን ደንበኞቻችንን በአደጋው አጥተናል፡፡ እስካሁንም በየዕለቱ እናስታውሳቸዋለን፤›› ብለዋል፡፡

ከአደጋው በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የነበሩትን ማክስ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ 30 ማክስ አውሮፕላኖች ከቦይንግ ኩባንያ ለመግዛት የተዋዋለው አየር መንገዱ፣ አምስት ማክስ አውሮፕላኖችን ተረክቦ አንዱን በአደጋው አጥቷል፡፡ የተቀሩትን አራት ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ በማገዱ፣ በአጠቃላይ አምስት አውሮፕላኖች ከሥራ ውጪ ሆነውበታል፡፡ ይህም አየር መንገዱ ላይ የአውሮፕላን እጥረት እንደፈጠረበት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሮልስ ሮይስ ሞተሮች የተገጠሙላቸው የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች የቴክኒክ ችግር የገጠማቸው በመሆኑ የአውሮፕላን እጥረቱን አባብሶታል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ የሮልስ ሮይስ ኩባንያ ካሳ እየከፈለን ቢሆንም በሥራችን ላይ ጫና አሳድሮብናል፤›› ብለዋል፡፡

በአሜሪካና በቻይና መካከል ባለው የንግድ ጦርነት ሳቢያ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስና የነዳጅ ዋጋ መናር አየር መንገዱ የገጠሙት ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑ አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በ21 በመቶ መጨመሩ የአየር መንገዱን አጠቃላይ ወጪ እንዳናረውም አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ንግድ መዳከም አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረው፣ ይህንን ችግር ለመቋቋም አየር መንገዱ የጭነት አውሮፕላኖቹን ወደ አውሮፓና ቻይና መስመሮች ማሰማራቱን ገልጸዋል፡፡

ሌላው አየር መንገዱ የገጠመው ትልቁ ፈተና በአፍሪካ አገሮች የሸጠውን ሽያጭ በዶላር ቀይሮ ወደ አገር ቤት ማስገባት አለመቻሉ ነው፡፡ አየር መንገዱ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች በአገሬው ገንዘብ የሸጠውን የአየር ቲኬት ገንዘብ፣ ወደ ኢትዮጵያ በዶላር መንዝሮ ለመላክ ተቸግሯል፡፡

‹‹በበርካታ የአፍሪካ አገሮች በተፈጠረው የዶላር እጥረት ሳቢያ ገንዘባችን ተይዞብናል፡፡ በዚህ መካከል በሚፈጠር የምንዛሪ ለውጥ የምናወጣው ገንዘብ ይቀንሳል፡፡ ይህም በትርፋችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚምባቡዌ፣ በአንጎላ፣ በሱዳንና ኤርትራ ገንዘብ እንደተያዘበት ገልጸዋል፡፡

በአንጎላ 40 ሚሊዮን ዶላር፣ በሱዳን 30 ሚሊዮን ዶላር፣ በዚምባቡዌ 15 ሚሊዮን ዶላር፣ በኤርትራ ስምንት ሚሊዮን ዶላር እንደተያዘበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ ችግር ተቋቁመን ትርፋማ በመሆናችን ደስተኞች ነን፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪው 15 ዓመታት የሚመራበትን ራዕይ 2035 የተሰኘውን የዕድገት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ለኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ አቅርቧል፡፡

አቶ ተወልደ ጉዳዩ በሒደት ላይ ያለ በመሆኑ ዝርዝሩን ከመግለጽ የተቆጠቡ ቢሆንም፣ በራዕይ 2035 አየር መንገዱን 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ያለውና ከ200 በላይ አውሮፕላኖች ባለቤት ለማድረግ እንደተወጠነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቦርዱ አዲሱን የዕድገት መርሐ ግብር በመገምገም ላይ ሲሆን፣ በመጪው ጥቂት ሳምንታት ፀድቆ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች