Thursday, July 25, 2024

ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ክብሯ እንመልሳት!

አገራችን ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔዎች ቁንጮ ብቻ ሳትሆን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነችና የቱባ ባህል ባለቤት ናት፡፡ አለመታደል ሆነና ግን በአንድ ወቅት የዓለምን ሥልጣኔ ስትዘወር የነበረችው አገር፣ አሁን በውራ ደረጃ ተቀምጣ በርካቶቻችንን እያሳፈረችን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ዘመን በሕይወት ያለን ሰዎች ይህንን ታሪክ በመመልከታችን እጅግ ያሳዝናል፡፡

በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከተያዙበት የባርነት ቀንበር ነፃ እንዲወጡ ግንባር ቀደም ሚና ስትጫወት የነበረችው አገራችን፣ ይኸው አሁን ሕዝቧ ተከፋፍሎና ተፈራርቶ እየኖረባት ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተነፍጎ በፍርኃት ካባ ተሸብበው ሲኖሩ ማየት ያሳፍራል፡፡ ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በሆነችው አገር ሰዎች በነፃነት መኖር ተነፍገው ማየት በእርግጥም ያሳዝናል፡፡

አውሮፓውያንና ምዕራባውያን እርስ በእርሳቸው በሚጠፋጨፉበት ጊዜ የዓለም የሥልጣኔ ምልክት የነበረችው አገራችን፣ አሁን ወደ ኋላ ተሽቆልቁላ ሕዝቦቿ እርስ በርሳቸው ሲጠቃቁ ማየት ከምንም በላይ ያማል፡፡ በፍቅር ተከባብሮና ተቻችሎ ሲኖር የነበረ ሕዝብ እንደዚህ ተከፋፍሎና ተለያይቶ ከማየት ባለፈ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ፡፡ ሕዝቦች በመካከላቸው ባላቸው የሃይማኖትም ሆነ የዘር ልዩነት ያለ ምንም ችግር በሰላምና በፍቅር ሲኖሩባት የነበረችው አገር፣ አሁን ሰዎች በዘራቸውና በሃይማኖታቸው ብቻ ሲጠቁ ማየቱ እጅግ ያሳፍረናል፡፡

ኢትዮጵያ ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች ነፃነት ከመታገሏና ነፃ ከማውጣቷ ባሻገር፣ ነፃ የወጡትን የአፍሪካ አገሮች አንድ ሆነው ለጋራ ልማትና ብልፅግና እንዲሠሩ የፊት አውራሪነቱን ሚናና የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ሆኖም ግን አሁን ሕዝቦቿ በክልል ተከፋፍለውና ተለያይተው እንደ ጠላት እየተያዩ መሆኑ አሳፋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትን በመመሥረት ለአኅጉሪቷ የንግድ፣ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ትስስር በተጫወተችው ሚና አፍሪካ የዓለም ትኩረት እንድታገኝ ከማድረጉ ባሻገር፣ አኅጉሪቱ በበርካታ ጉዳዮች ተከታይ ከመሆን ይልቅ መሪና ተዋናይ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ይህን ያህል ለአኅጉሪቱ አንድነት ከፍተኛ መስዋዕነት የከፈለችው አገራችን፣ አሁን ላይ ሕዝቧ ተለያይቶ ማየቱ ለማመን ይከብዳል፡፡ እርግጥ ነው አሁንም በአገሪቱ ያሉት ሕዝቦች ተከፋፍለው ሳይሆን፣ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ጥቅም በማሰብ በሕዝቡ ላይ ስለሚቆምሩ ነው፡፡

ዓለማችን በዘመነ ልዑላዊነት የአገሮች ድንበር እየፈረሰ፣ የንግድና የማኅበራዊ ትስስሩ እጅጉን እየጨመረ መጥቷል፡፡ እኛም ቀድሞ ይኼው እውነት ተገልጦልን ነበር አፍሪካን አንድ ለማድረግ ስንታገልና ስንለፋ የነበርነው፡፡ ይህ የአንድነት ጥቅም ከጅምሩ ስለገባን ከአፍሪካ አንድነት ባለፈ ለዓለም አንድነት የተጫወትነው ሚና ታሪክ የሚዘክረው ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመመሥረቱ በፊት በሊግ ኦፍ ኔሽን ስብስብ ውስጥ ብቸኛዋ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን አገራችን መሥራች አባል መሆኗ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ምንም እንኳን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የአንድነትና አብሮ የመሥራት ምልክት ብትሆንም፣ አሁንም በአገራችን ያለው እውነታ ከዚህ የራቀ ይመስላል፡፡ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም የሥልጣኔ፣ የነፃነትና የአንድነት ተምሳሌትና ኩራት የነበረችው አገራችን፣ ሕዝቦቿ የተከፋፈሉና የተለያዩ መስለው መታየቱ ያሳዝናል፡፡ በርካቶች የሚኮሩበት ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሥልጣኔና ሌሎችም በጎ ነገሮች የነበሯት አገር፣ እነዚሁ ቱባ ባህሎችና እሴቶች ለልዩነት ምክንያት መሆናቸው ያሳፍራል፡፡

ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ኩራት የነበረችው አገራችን፣ አሁን ላይ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው፣ በዘራቸውና በሃይማኖታቸው እንዲያፍሩና እንዲሳቀቁ እየተደረጉባት ነው፡፡ የዓለምና የአፍሪካ ኩራት የነበረችው አገራችን፣ በዚህ ሁኔታ ሆና ስትማቅቅ ማየቱም ያሳፍራል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ደግሞ እኛው ራሳችን ነን፡፡

ስለሆነም አሁን ያለውን ጥፋት ራሳችን ካመጣነው፣ መፍትሔውም በእጃችን ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ቀድሞ የነበርንበት የሥልጣኔ ቁንጮነት ምስክር ነው፡፡ ከዘመናት በፊት እንኳን ክልል ኢትዮጵያም ትጠበናለች በሚል ብሂል አገራችን አፍሪካና ዓለም አንድ እንዲሆኑ መሥራቷ ሊታወስ ይገባል፡፡ አሁን ላለንበት ውድቀት የተዳረግነውም በሴራ ፖለቲካ የሚዘወረው ሥርዓታችን የክፋት ሐሳብ ሁሉንም ዘርፍ እንዲቆጣጠረው በመደረጉ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ላለንበት ዝቅጠት የክፉዎች ሐሳብ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን፣ በጎ ሐሳብና አገራቸውን የሚወዱ ሰዎች ዝምታ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡

የአገሪቷ መገጫ የሆነውን ድህነት ለማጥፋት ምንም ጊዜ ሳናጠፋ ሁላችንም ወደ ሥራ መግባት በነበረብን በዚህ ወቅት፣ ጫፍ የረገጡ ሐሳቦችን እያሰላሰልን ከድጡ ወደ ማጡ እየተጓዝን ነው፡፡ ለዘመናት ከወራሪና ከጠላት ጠብቀው አባቶቻችንና አያቶቻችን የሰጡንን አገር ማስቀጠል አቅቶን፣ ውኃ የማይቋጥሩ ታሪክና ትርክቶች ላይ ጊዜያችንን እያጠፋን መልሰን የማናገኛቸውን ዕድሎች እያባከንን እንገኛለን፡፡ በአንድ ወቅት የአፍሪካ ኩራት የነበርን፣ አሁን ላይ የጋራ ታሪካችን ላይ መስማማት አቅቶን በረባ ባልረባው እየተባላን እንገኛለን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ አገሪቷን የበለጠ ይጎዳት ይሆናል እንጂ አይጠቅማትም፡፡ የሚከፋፍሉና የሚለያዩ ታሪኮች ላይ የሙጥኝ ብለን ወርቃማ ጊዜያችንን እያጠፋን መና ከመጠበቅ፣ እጆቻችንን ለሥራ ዝግጁ በማድረግ ሕዝባችንንም ሆነ አገራችንን ወደ ተሻለ ጎዳና እንውሰዳቸው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የነበረን ከፍታ ተባብረን በመሥራት እናስመልሰው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ክብሯ እንመልሳት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...