Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፀረ አበረታች ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት አትሌቶችንና አሠልጣኞችን አስጠነቀቀ

የፀረ አበረታች ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት አትሌቶችንና አሠልጣኞችን አስጠነቀቀ

ቀን:

የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) በናይክ አካዴሚ ውስጥ ታላላቅ አትሌቶችን በማሠልጠን የሚታወቀው አሜሪካዊው አልቤርቶ ሳላዛር ላይ የአራት ዓመት ዕገዳ ማስተላለፉን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት (ናዶ) ለአትሌቶችና ለአሠልጣኞች ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ ዕገዳው የተላለፈበት አሜሪካዊ አልቤርቶ ሳላዛር የዋዳን ፀረ አበረታች ቅመሞች ሕግ በመተላለፍ መሆኑ ታውቋል፡፡

ናዶ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና አሠልጣኞች እንዲሁም የስፖርቱ ሙያተኞች በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ከማናቸውም የአትሌቲክስ እንቅስቃሴና መድረኮች የአራት ዓመት ዕገዳ ከተላለፈበት አልቤርቶ ሳላዛር ጋር የነበራቸውን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ነው፡፡ አትሌቶችም ሆነ አሠልጣኞች እንዲሁም ሙያተኞች ማስጠንቀቂያውን ችላ በማለት ከአሠልጣኙ ጋር መገናኘታቸው ከተረጋገጠ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ቅጣት እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል፡፡

አሜሪካዊ አሠልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር፣ በዋዳ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወርን ጨምሮ የፀረ አበረታች ቅመሞችን እንቅስቃሴ በማወክ የሕግ ጥሰቶች ተጠርጥሮ፣ በአሜሪካ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዩኤስኤዲኤ) ሲጣራ መቆየቱ የጠቀሰው ብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ፣ በምርመራው መሠረት ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ለአራት ዓመት በስፖርቱ ውስጥ እንዳይሳተፍ ዕገዳ ጥሎበታል፡፡

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የቅጣት ውሳኔው ለአተገባበር ያግዝ ዘንድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ማሳወቁን በመግለጫው አካቷል፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፉ የዋዳ ሕግና በኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት መመርያ አንቀጽ 2.10 መሠረት በሕግ ጥሰት ቅጣት ከተላለፈባቸው ግለሰቦች ጋር ያልተገባ ግንኙነት መፍጠር በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፣ ይህን ተላልፎ የተገኘ አካል ወይም ግለሰብ ሁለት ዓመት የሚደርስ ቅጣት ያስከትላል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና አሠልጣኞች ከዚህ በፊት በተለያየ መልኩ ከአሠልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር ጋር አብረው እንደሚሠሩ የሚታወቅ መሆኑን ያስታወቀው ብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ፣ በግለሰቡ ላይ የተጣለው የቅጣት ውሳኔ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ጠይቋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በተጨማሪም ሌሎችም ባለሙያዎች የተቀመጠውን ሕግ በመተላለፍ ቀደም ሲል የነበራቸውን ግንኙነት ለማስቀጠልና አዳዲስ ግንኙነቶችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ጽሕፈት ቤቱ ጉዳዩን በማጣራት አስፈላጊውን የሕግ ዕርምጃ ለመወሰድ የሚገደድ መሆኑን ጭምር አስታውቋል፡፡

አሜሪካው አሠልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍጻሜው ባገኘው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች 10.000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው በትውልድ ኢትዮጵያዊት በዜግነት ኔዘርላንዳዊት ሲፋን ሐሰንን ጨምሮ የቀድሞ የኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ አሸናፊው በትውልድ ሶማሊያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውንና ኬንያውያን ታላላቅ አትሌቶችን ጭምር ሲያሠለጥን መቆየቱ ይታወቃል፡፡     

መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣውን የሚኒስትሮች ደንብ ቁጥር 400/2009 መነሻ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት መቋቋሙን ተከትሎ፣ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በዘላቂነት መከላከልና መቆጣጠር ይቻል ዘንድ ብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በሕግ ከመቋቋሙ በፊት የዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ችግሩ በስፋት ከታየባቸው አምስት የዓለም አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ተደርጋ መጠቀሷ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...