Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማሌዥያዋ ሚኒስትር የፓልም ዘይት ጤናን እንደማይጎዳ ይሞግታሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገር ውስጥ አምራቾች ዕድል ይሰጣል ተብሏል

በርካታ ሙግቶችን እያስተናገደ የሚገኘው፣ በአብዛኛው ከማሌዥያ የሚገባውና ከዘንባባ መሰል የዛፍ ፍሬ የሚመረተው የፓልም ዘይት፣ ለጤና ጉዳት የሚያጋልጥ ‹‹ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የለውም›› በማለት የማሌዥያ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ቴሬሳ ኮክ ይሞግታሉ፡፡

ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት ሐሙስ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተካሄደው የኢትዮጵያና የማሌዥያ የንግድ ልዑካን ሴሚናር ላይ ነበር፡፡ የማሌዥያ የፓልም ዘይት አምራቾች ምክር ቤት፣ የመርጋት ባህርይ ያለው ይህ ዓይነቱ ዘይት ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል በኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚሠራጨው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነም ተከራክረዋል፡፡ እንደውም ምርቱ ምንም ዓይነት ጉዳት አያመጣም በማለት ጭምር የምክር ቤቱ አባላት አስተባብለዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባው 94 በመቶ የምግብ ዘይት ውስጥ 86 በመቶው የፓልም ዘይት ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው የሚረጋ ዘይት ሲሆን የሚገባውም ከማሌዥያ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በማሌዥያ የንግድ ልዑካን መካከል የተካሄደው ሴሚናር ይህንኑ የዘይት ምርት ጨምሮ ሦስት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የፓልም ዘይት ምን ዓይነት መሆን አለበት የሚለው ላይ ያተኮረው አንደኛው የሴሚናሩ መወያያ ጉዳይ ነበር፡፡ ሌላኛው አጀንዳ በኢትዮጵያ የሚመረተውን የምግብ ዘይት ከማሌዥያ አመራረት ሒደት አኳያ የንግድ ልውውጡ እንዴት ይጠናከር የሚለው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የመጨረሻው አጀንዳ ለዘይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንዴት መቆጠብ ይቻላል የሚለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የምግብ የመጠጥና የፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ታደለ ስለዚሁ ጉዳይ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

አቶ ሰሎሞን እንደገለጹት፣ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ የምግብ ዘይትን በተመለከተ ደረጃ ወጥቷል፡፡ የደረጃው መውጣት ስለሚሰጠው ጠቀሜታ ሲገልጹም፣ ‹‹የምግብ ዘይት ጥራት የሚሻሻልበት እንዲሁም በአዲስ መልክ የሚመረትበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ደረጃው ምን እንደሚያስገኝ ሲያብራሩም፣ ለምግብነት የምንጠቀመው ዘይት በሰውነታችን ውስጥ  ገብቶ የማይረጋና ፈሳሽ እንዲሆን ለማስቻል የወጣ እንደሆነ አክለዋል፡፡ አያይዘውም ከወጪ የሚገቡ የምግብ ዘይቶች የወጣውን ደረጃ መጠበቅ እንዳለባቸውና ለግዥ የሚወጣው የጨረታ ሰነድም ይኼን ያረጋገጠ መሆን እንዳለበት ተስምምነት መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡

ሴሚናሩ የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾች ከማሌዥያ ተቋማት ጋር አብረው እንዲሠሩ ዕድል እንደሚያመቻችና ከውጭ አገር በከፊል ያልተጣራ ድፍድፍ ዘይት በማስመጣት እዚህ እንዲያጣሩ፣ ከማሌዥያውያንም ልምድ እንዲቀስሙ እንደሚደረግ አቶ ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ከውጭ የሚገቡት ዘይቶች  ፈሳሽና በሰውነት ውስጥ የማይረጉ እንደሆኑ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንድ ሰው በዓመት 5.49 ኪሎ ግራም ዘይት ለምግብ ማብሰያነት እንደሚጠቀም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አሐዙ በነፍስ ወከፍ መጠቀም ከሚገባው በታች እንደሆነ ኃላፊው ይናገራሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በወር 40 ሚሊዮን ሊትር የዘይት ፍላጎት አላት፡፡ ይህም ከሕዝብ ቁጥር መጨመር አኳያ እየጨመረ የመጣ ነው፤›› ቢሉም ከ480 ሚሊዮን እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ለዘይት ግዥ እንደሚውል አክለዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ዘይቶች ስድስት በመቶ የአቅርቦት ድርሻ እንደያሲ ሲገለጽ፣ ይህንን በእጥፍ ከፍ ለማድረግና አምራቾችን ለማብዛት እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች