የሰላም የይቅርታና የምሥጋና በዓል የሆነው ኢሬቻን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) አደረጃጀት መጥለፉ ሳያንሰው የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሰባሪ/ተሰባሪ ትርክት ማቀንቀኑ አገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትትና የሚበርዝ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፍትሕና የነፃነት ጥያቄ በግዴለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይጠለፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል፤›› ብሏል፡፡ የአገር አንድነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሒደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት በማለትም ፓርቲው አሳስቧል፡፡
በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የአዲስ አበባ ሕዝብ ያሳየውን ትዕግሥት እንደሚያደንቅ የገለጸው ኢዜማ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደ ሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም፣ ይህን ያልተረዱ ወገኖች ትዕግሥቱን እንደ ፍርኃት ጨዋነቱን እንደ የዋህነት እየወሰዱ ማኅበረሰቡን መተንኮስ እየተለመደ መጥቷል፤›› በማለት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ መብቱ እንዲከበርለትም ፓርቲው በአጽንኦት ጠይቋል፡፡
ፓርቲው በማከልም፣ ‹‹ይህ የአገራችንን ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ የያዘና ከዚያም በላይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሆነ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ከተማን በጥንቃቄና በአክብሮት መያዝ ይገባል፤›› ብሏል፡፡ የከተማው ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም ዕውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን ኢዜማ እንደማይቀበል አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡
ስለሆነም የከተማው ሕዝብ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደሚደግፍም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስተዋወቀው የደንብ ልብስ ለከተማ የፖሊስ አገልግሎት የሚመች ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል አሳስቧል፡፡ ‹‹የከተማዋ ፖሊስ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ፣ እንዲሁም በማኅበረሰብ ፖሊስ ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት እያለውና የፌዴራል ፖሊስ ኃይል በቋሚነት በሚገኝበት ከተማ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ማቋቋም ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ከዚህ ይልቅ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ መንገድ የከተማዋን ኅብረተሰብ ደኅንነት ማስጠበቅና አባላቱ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም በአማራ ክልል የተከሰቱ የወንድማማች ሕዝብ ግጭቶችን ተከትሎ ሁኔታው እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ፣ ‹‹ሥራዬ ብለው ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአስቸኳይ አስተማሪ ዕርምጃ እንዲወስድባቸው እናሳስባለን፤›› በማለት ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ፓርቲው ከሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር መደላድል ለመፍጠር፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ገልጾ፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖች የሚሠሩትን ነውረኛ አካሄድ ማየቱ ለመግለጫው ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል፡፡