ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የወጣው አዲሱ የግብፅ ምክረ ሐሳብ ነባር ስምምነቶችን የጣሰ፣ የግብፅን የውኃ ድርሻ ለማስጠበቅ ያለመ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጥስና ተቀባይነት እንደማይኖረው ተገለጸ፡፡
ግብፅ አዲስ ባቀረበችው ምክረ ሐሳብ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሱዳንና የራሷ የሃድሮሎጂ ባለሙያዎች ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም፣ ባለሙያዎቹም ግድቡን የመቆጣጠር፣ የመለካት፣ በየቀኑና በየጊዜ መረጃ የመልቀቅ ሥልጣን እንዲኖራቸው መጠየቋ፣ የአገር ሉዓላዊነትን የሚጥስና ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ መሆኑን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ አማካሪ አቶ ተፈራ በየነ ገልጸዋል፡፡
በሱዳን ካርቱም ከመስከረም 19 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ፣ ‹‹የግብፅ ወገን ላለመስማማት ተስማምቶ ወስኖ የመጣ ነበር የሚመስለው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ካልተስማማን በአንድም ነገር ላይ መስማማት አንችልም፣ በሁሉም ጉዳይ ካልተስማማን የሚመዘገብ፣ የሚያዝ ነገር አይኖርም የሚል ጠንካራ አቋም በመያዙ ለሚኒስትሮች ሪፖርት ማቅረብ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡
የግድቡ ባለቤት ኢትዮጵያ በምታቀርበው ዕቅድ ላይ አዲስ ዕቅድ ይዛ የቀረበችው ግብፅ ምክረ ሐሳቧ የሦስትዮሽ ምክክር ሒደቱን ከመጣስና የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ከመንካት ባለፈ ሉዓላዊነትንም የሚጥስ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዲኖር የቀረበው ጥያቄም ፈጽሞ ተቀባይተን የሌለው እንደሆነ አማካሪው አስረድተዋል፡፡
ግብፅ ባቀረበችው ምክረ ሐሳብ የግብፅ የዓባይ የተፈጥሮ ፍሰት በማንኛውም መልኩ ሳይዛባ እንዲቀጥልም ጠይቃለች፡፡ ይህም እስካሁን ያለውን የልማት ሥራ፣ የአሁኑንና የቀጣዩን ትውልድ፣ እንዲሁም በዕቅድ ያሉ የልማት ሥራዎችን የሚዘነጋ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ አንዳችም ጠብታ ውኃ ከግድቡ ራስጌ እንዳይነካ የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹በተፈጥሮ ያለውን ፍሰት ምንም እንዳልተነካ፣ እንዳልተሠራ፣ በድንግልና የቆየ ወንዝ አድርጎ መመልከትና በዚያ ሁኔታ እንዲቀጥል የመጠየቅ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ለእኛ የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው፤›› ያሉት አማካሪው፣ ይህንን ምክረ ሐሳብ መቀበል የዚህን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የተከታታይ ትውልድን መብት አሳልፎ መስጠት ይሆናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ግብፅ ባቀረበችው ምክረ ሐሳብ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንዲለቀቅላት የጠየቀችውም ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የዓባይ ዓመታዊ አማካይ ፍሰት 49 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው ያሉት አቶ ተፈራ፣ ጥያቄው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት የውኃ መጠን መዋዠቅን ያላገናዘበ፣ በራስጌ የሚደደረግ የልማት እንቅስቃሴን ያላማከለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ በከባድ የድርቅ ወቅት የዓባይ ፍሰት እስከ 21 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ድረስ ዝቅ እንደሚል በመጥቀስ፣ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይለቀቅልኝ ስትል ግብፅ ያቀረበችውን ጥያቄ ውኃ የማቋጥር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በምክረ ሐሳቡ ግብፅ የህዳሴውን ግድብ ከአስዋን ከፍታ ጋር እንዲያያዝ ማድረጓም የማይታመን ሆኗል፡፡ የአስዋን ግድብ ከፍታ ሲጎድል ከግድቡ ውኃ እንዲለቀቅ መጠየቋ ግድቡ ለረዥም ዓመታት ሳይሞላ እንዲቆይ፣ ኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫውን ከመጠቀም ይልቅ የአስዋንን ግድብ ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነትና ግዴታ የሚጥልባት በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖው ገልጸዋል፡፡