Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአጣዬ አካባቢ ግጭት የፈጠሩት ታጣቂዎች በተደራጀ ኃይል እንደሚመሩ ተገለጸ

በአጣዬ አካባቢ ግጭት የፈጠሩት ታጣቂዎች በተደራጀ ኃይል እንደሚመሩ ተገለጸ

ቀን:

የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉና ለጊዜው የተኩስ ልውውጡ መቆሙም ተጠቁሟል

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማና ኤፍራታና ግድም ወረዳ ላይ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ የሰው ሕይወት መጥፋቱና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ታወቀ፡፡ ግድያ የፈጸሙትና ግጭቱን የፈጠሩት ታጣቂዎች በተደራጀ ኃይል እንደሚመሩ አመላካች ነገሮች መታየታቸውም ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታቸው በቀለ እንደገለጹት፣ ዛሬ (መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም.) በአጣዬ ከተማ ላይ ተኩስ የለም፡፡ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ግን ፀብ የመጫር ሁኔታዎች አሉ፡፡ አጣዬ ከተማ በተራራ የተከበበች ከተማ በመሆኗ ታጣቂዎቹ ከላይ ሆነው ወደ ታች ይተኩሳሉ፡፡ በእርግጥ ከስድስት ወራት በፊት ተከስቶ እንደነበረው በከተማው ውስጥ የሰው ሕይወት አላለፈም፡፡ ድርጊቱን የሚፈጽሙት፣ ለጊዜው እነማን እንደሆኑና ከየት እንደተላኩ ባይታወቅም ሙሉ ትጥቅ ያላቸው፣ የተደራጁና በተጠናከረ ደረጃ ማጥቃት የሚያስችል ኃይል እንዳላቸው እንደሚያስታውቁ ተናግረዋል፡፡

የታጣቂዎቹ ሁኔታ ዝም ብለው የሚንቀሳቀሱ ሳይሆን የተደራጀ ኃይል እንደሚመራው የሚያመላክት፣ በደንብ የተዘጋጁና የታጠቁ መሆናቸውን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ቅዳሜ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የጀመረው ተኩስ ከስድስት ወራት በፊት በተከሰተው ግጭት የነበረውን ግድያ፣ ንብረት ውድመትና አካል መጉደል በማስታወሱ ነዋሪዎችን እጅግ ያስጨነቀ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ላለፉት ሦስት ቀናት ሱቆች፣ መንግሥታዊና የግል ድርጅቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ትናንት መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም. አንዳንድ ሱቆች ተከፍተው ከመታየታቸው በስተቀር ባንኮችም ሆኑ ሌሎች ድርጅቶች ዝግ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከመስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል ችግሮቹ በተከሰቱባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች በመሰማራታቸው ተኩስ መቆሙንና ለጊዜውም ቢሆን ጠፍቶ የነበረው ሰላም መመለሱን አክለዋል፡፡ ታጣቂዎቹ በኤፍራታ ግድም ወረዳ፣ ዲሌ ጥሞጋና አርጡማ ፋርሲ ቀበሌዎች አካባቢ የመጡ መሆናቸውንና በፊትም ከዚያ አካባቢ የሚመጡ ግለሰቦች እንደነበሩ አስታውሰው፣ በግጦሽና በውኃ ይፈጠር የነበረው አለመግባባት በአካባቢው ሽማግሌዎች ይፈታ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደምሰው መሸሻ ደግሞ እንደተናገሩት፣ ከመስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት ጀምሮ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ቆሞ ሰላም ሰፍኗል፡፡ መስከረም 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በነበረው የተኩስ ልውውጥ ግን አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከታጣቂዎቹ በኩል የሞቱ እንዳሉ ቢነገርም ስንት እንደተገደሉ ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት በአጣዬ ከተማና ዙሪያ ወረዳዎች ተፈጥሮ በነበረው ግድያ፣ የንብረት ውድመት፣ የእምነት ተቋማት ቃጠሎና የአካል መጉደል ምክንያት ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡ በመሆኑም ከአስፋልት መንገድ ግራና ቀኝ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ግን ሁለት ታጣቂዎች ወደ አጣዬ ለገበያ ከእነ ትጥቃቸው ሲገቡ፣ በጥበቃ ላይ የነበረው የክልሉ ልዩ ኃይል ሲይዛቸው ተኩስ በመክፈታቸው ግጭቱ መጀመሩን አቶ ደምሰው ተናግረዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...