Friday, June 21, 2024

ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ተቀያሪ አገር የለንም!

እናታችን ኢትዮጵያ ክፉኛ ታማለች፡፡ የእናት ሕመም ደግሞ ልጆቿን ያስጨንቃቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ልጆች ያላቸው አንድ እናት በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮያ አገራችን የሁላችንም ቤትና መጠለያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለሀብታሙም ሆነ ለደሃው፣ ለተማረውም ሆነ ላልተማረው፣ ለልጅ ሆነ ለአዋቂው እንዲሁ በጠቅላላው ለሁላችንም መኖሪያና መጠለያችን ናት፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን እዚህ በአካል በምድሯ ላለን ብቻ ሳይሆን ከእሷ አፈር ተገኝተው በሕይወት አጋጣሚ ሌላ ቦታ ላሉ ዜጎቿ ሳይቀር የክፉ ቀን መጠለያቸው ናት፡፡ እንግዲህ ለዚህች የጋራ አገራችንና መኖሪያችን እጅጉኑ ልንጠነቀቅላት ይገባል፡፡ አገራችን ኢትጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ አስደሳች ባለመሆኑ፣ ሁላችንም ተረባርበን አገራችን ከገባችበት ችግር ልናወጣት ይገባል፡፡ ያለበለዚያ የአገራችን ዳፋ ለሁላችንም የሚተርፍ ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶችና ባህሎች ያሏቸው ዜጎች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን በማኅበራዊው፣ በፖለቲካዊውና በኢኮኖሚው ዓውድ የተለያዩ ሐሳቦች መንፀባረቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታትም በኢትዮጵያ ያሉ ሕዝቦች ተከባብረውና ተቻችለው በመኖር ተምሳሌት መሆናቸው በይታወቃል፡፡ አሁን አሁን ግን የሚሰሙ ወሬዎች ሁላችንንም የሚያሳዝኑና ጫን ሲልም የሚያስጨንቁ ሆነዋል፡፡ ለዘመናት ተከባብረውና ተቻችለው የነበሩ ሕዝቦችን ወዳልተፈለገ ግጭት የሚከቱ ሙከራዎች እዚህም እዚያም ሲደረጉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው አገራችን ኢትዮጵያ በማኅበራዊው፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፎች ለዘመናት የተከማቹና በጊዜው መፍትሔ ያልተሰጣቸው የቤት ሥራዎች አሉባት፡፡ እነዚህ ከዘመን ዘመን መፍትሔ ሳይሰጥባቸው እየተሻገሩ የመጡ ችግሮች፣ አሁን አዋቂ ነን በሚሉ አክቲቪስቶችና ቁማርተኛ ፖለቲከኞች እየተመዘዙ ሕዝብ እየተሸበረ ነው፡፡ የችግሮቻችን መነሻዎች እኛ እንደመሆናችን መጠን መፍትሔዎቹም በእጃችን መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ከሁላችንም የሚጠበቀው ግን በቅንነትና በመደማመጥ ላሉብን ችግሮች አንድ በአንድ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንገዱ መደማመጥና መተባበር ነው፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አገራችን በጊዜ መፍትሔ ሳትሰጣቸው ያከማቸቻቸው ችግሮች ላይ በየዕለቱና በየቀኑ አዳዲስ ችግሮች እየተጨመሩ የአገራችን በሽታ ከማገገም እየጠና መሄድ ጀምሯል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ዓመት ከመንፈቅ በፊት በአዲስ የለውጥ ጎዳና መጓዝ ስትጀምር፣ ለዘመናት የተከማቹ የቤት ሥራዎቿ መቃለል ይጀምራሉ ተብሎ በብዙዎች ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ለዓመታት በሕዝቦች ላይ የነበረው ጭቆና ተነስቶ ዜጎች ለአገራቸው የበኩላቸውን የሚያበረክቱበት ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ያለመታደል ሆነና አዲስ የመጣው ለውጥ ሁላችንንም ለጥቂት ጊዜያት በተስፋ ጎዳና ካስጓዘን በኋላ፣ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ሐሳቦች እየተሳሳቡ ጭራሽ የባሰ ሥጋት ውስጥ ገብተናል፡፡ ምንም እንኳን ለበርካታ ዓመታት ታፍኖና ተዘግቶ የነበረ ቤት ሲከፈት የተለያዩ መጥፎ ነገሮች ሊሸቱን ይችላሉ፣ ነገሮችም ቀስ በቀስ ሊስተካክላሉ ይችላሉ በሚል ዕሳቤ እስካሁን ቆይተናል፡፡ ሆኖም እንዳሰብነው ነገሮች ከመስተካከል ይልቅ ጭራሽ እየባሰባቸው እየሄዱ ነው፡፡ ለዘመናት ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩ ሕዝቦች ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ ትርክቶች እየተነገሩ የአገራችን ማዕዘን የሆኑ እሴቶች እንዲፈርሱ የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ለዓመታት የነበረው አፈና መተንፈስ መቻሉ ለሐሳብ መንሸራሸር በር ቢከፍትም፣ አሁን ባለው ሒደት ለአገሪቱ ተጨማሪ የቤት ሥራዎችን የመፍጠሪያ መንገድ እየሆነ መጥቷል፡፡ የአገራችን አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች አገራችን ከገባችበት ፈተና የሚያወጡ ሐሳቦችን ከማፍለቅ ይልቅ፣ እንደ ቀድሞው በሴራ ፖለቲካ እርስ በእርስ እየተነዳደፉና ሲችሉም ሕዝቡን ለግጭት እየጋበዙ የለውጡ እንቅፋት መሆናቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ከእነዚህ ፖለቲከኞች ወትሮም ቢሆን ሐሳብ ይፈልቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ሥልጣናቸውን ያገኙት ባላቸው ችሎታና አቅም ሳሆን ሌሎች አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም ነው፡፡

ወትሮንውም ቢሆን እነዚህ ፖለቲከኞች ሕዝብን ሊያገለግሉበት የሚችሉበት አቅሙም ሆነ ችሎታው ስለሌላቸው፣ የለመዱት ጥቅም ብቻ እንዳይቀርባቸው በአገርና በሕዝብ እየቆመሩ ራሳቸው የለውጥ አርበኛ በማድረግ በየማኅበራዊ ሚዲያው መርዛቸውን ይረጫሉ፡፡ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ መሣሪያ መሆኑን ረስተው፣ የራሳቸውን ጥቅም እያሳደዱና ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጩ የራሳቸውን ሥልጣን እያራዘሙ ከመሆኑ ባለፈ፣ አገሪቷን ለከፋ ችግር እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የፖለቲካ ቁማርተኞች አገሪቷ ያሉባትን የተከማቹ የቤት ሥራዎች ከማቅለል ይልቅ፣ በየጊዜው ሌላ የቤት ሥራ በመስጠት አደጋ እየፈጠሩ ነው፡፡ ሕዝብን በቅንነት ከማገልገል ባዶና ቅፅበታዊ ታዋቂነትን ለማግኘት ሲፍጨረጨሩ ማየቱም ያሳዝናል፡፡ ምንም ፋይዳ የሌለው የብሽሽቅ ፖለቲካ ራሳቸውን አናውዟቸውም ሕዝብን ወዳልሆነ አቅጣጫ እየመሩ ነው፡፡ እንደ አገር ከፊታችን በርካታ ፈተናዎች ይጠብቁናል፡፡ ያሉብንን የተከማቹ የቤት ሥራዎች ሳንሠራ ከፊታችን ያሉ ፈተናዎች እየጨመርን መሄድም አዳጋች ስለሚሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ በኋላ ነገሮች እንደዚህ መቀጠል የለባቸውም፡፡ ጊዜ ያለፈባቸውንና ከፋፋይ ትርክቶችን የሚያላዝኑ የፖለቲካ ቁማርተኞች በቃ ሊባሉ ይገባል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉም ሆኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ተመሽገው ለሕዝቡ በየጊዜው አጀንዳ እየሰጡ አገሪቷን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስዱ መደዴዎች በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ አገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለችና ሁላችንም ተባብረን ይኼን አስቸጋሪ ጊዜ ማለፍ ይገባናል፡፡ ለሁላችንም ያለን አንድ አገር በመሆኑ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡ አንድ ዓይን ያለው በእንጨት እንደማይጫወት ሁሉ፣ እኛም በአንድ አገራችን መቀለድ የለብንም፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ተቀያሪ አገር የለንም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...