Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናፓርላማው 88 ዓመት የሞላቸው ሕንፃዎችን ለማፍረስ መወሰኑ ቅሬታ ፈጠረ

ፓርላማው 88 ዓመት የሞላቸው ሕንፃዎችን ለማፍረስ መወሰኑ ቅሬታ ፈጠረ

ቀን:

ሕንፃዎቹ ዕድሜ ጠገብ ከመሆናቸው ውጪ ታሪካዊነታቸውን የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም ተብሏል

የኢትዮጵያ ፓርላማ በውስጡ ካካተታቸው ዕድሜ ጠገብና ሙሉ ለሙሉ ከድንጋይ የተሠሩ የሕንፃ ክፍሎችን ለማፍረስ የፓርላማው ጽሕፈት ቤት መወሰኑ ቅሬታ እንዳስነሳ ታወቀ፡፡

ቅሬታ የተሰማቸው የአስተዳደር ሠራተኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የበላይ አመራር አካላት በቂ ጥናትና ዳሰሳ ሳያደርጉ፣ ለጊዜው የተፈጠረውን የቢሮ እጥረትን ለማስተካከል በሚል ዕሳቤ ብቻ ከተገነቡ 88 ዓመት የሞላቸው የድንጋይ ቤቶችን በማፍረስ ባለአራት ወለል ሕንፃ ለመገንባት ተዘጋጅተዋል፡፡ የማፍረስ ሥራውን ለማከናወንም የማሽነሪና የመሣሪያ አቅርቦት እየተካሄደ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት የድንጋይ ቤቶቹ እንደሚፈርሱ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ፓርላማው ከዚህ በፊት የቢሮ እጥረት ገጥሞት እንደነበርና ተቋሙ ከሚገኝበት ግቢ ወጣ ብሎ በተለምዶ አሮጌው ቄራ በሚባለው አካባቢ በዓመት 18 ሚሊዮን ብር እየከፈለ የግለሰብ ሕንፃ መከራየቱን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ምንጮቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጽሕፈት ቤቱ ሥር የሚገኙ ሠራተኞች ፓርላማው ከተከራየው ሕንፃ ወደ ዋናው ግቢ መመላለሱ አስቸጋሪ ስለሆነባቸውና ለሥራቸውም አመቺ አለመሆኑን ባሰሙት ቅሬታ መሠረት፣ ፓርላማው አዲስ ሕንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት የጽሕፈት ቤቱ አመራሮች አዲስ በሚገነቡትና በሚፈርሱት ነባር ሕንፃዎች ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ክርክር መነሳቱ ታውቋል፡፡ በተለይ ሁለቱ የድንጋይ ቤቶች ‹‹መፍረስ አለባቸው›› በሚሉና ‹‹መፍረስ የለባቸውም በታሪክ ቅርስነት መቆየት ይገባቸዋል›› በሚሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል ከረር ያለ ክርክር ተነስቶ እንደነበር ሪፖርተር ከምንጮች ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ነገር ግን በአመራሮች ውሳኔ ሁለቱም የድንጋይ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰናቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ ምንጮቻችን የኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው ሕገ መንግሥት በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ መፅደቁን ይናገራሉ፡፡ በተለይ በፓርላማው ለበርካታ ዓመታት የሠሩ አንድ ግለሰብ፣ ሁለቱ የድንጋይ ቤቶች አፄ ኃይለ ሥላሴ በጥቅምት 22 ቀን 1924 ዓ.ም. አራዳ ጊዮርጊስ የሚገኘውን የአፄ ምኒልክ ሐውልትና ባስመረቁበት ቀን መመረቃቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ግለሰቡ ለበርካታ ዓመታት ሲነገር የሰሙትን ይግለጹ እንጂ በሰነድ ያቀረቡት ማረጋገጫ የላቸውም፡፡

አዲስ ይገነባሉ የተባሉት ሕንፃዎች ከሁለቱ ታሪካዊ ሕንፃዎች በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎችም እንደሚያስፈርሱ ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ አስተውሏል፡፡ ለአብነትም ያህል የኅትመት ቤት ሆኖ ሲያገለግል የቆየው መደበኛ ቢሮን ጨምሮ ሦስት ታሪካዊ የማይባሉ ያረጁ ቤቶችም እንደሚፈርሱ ታውቋል፡፡

ይገነባሉ ስለተባሉትና ስለሚፈርሱት ቤቶች ሪፖርተር የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋን ምሥራቅ መኮንን (ዶ/ር) ጠይቆ፣ ስለሚገነቡት ሁለት ሕንፃዎችና የዲዛይን ሒደቱን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ስለሚፈርሱት ሁለት ታሪካዊ ቤቶች ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

‹‹እኛ ዝም ብለን የምናፈርሰው ሕንፃ የለም፡፡ አፍርሰን የምንገነባው በአግባቡ ጥናት ተካሂዶና በባለሙያ ታይቶ ነው፡፡ አሁን የምንገነባው ሕንፃ የፓርላማውን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ ተገናዝቦ በተሠራ ዲዛይን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከፓርላማው በላይ ለቅርስ መቆርቆር ያለበት ሌላ አካል የለም፡፡ እንዲሁ ቅርስ እያወደመ ሌላ ነገር አይሠራም፤›› ያሉት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዋ፣ አሁንም ቢሆን ለሚሠራው አዲስ ሕንፃ በተለይ ለዋናው የፓርላማው ሕንፃና ሌሎች ተዛማጅ ሕንፃዎች ታሪካቸውንና ዕድሜቸውን ባገናዘበ፣ እንዲሁም ደኅንነታቸውን በጠበቀ መልኩ ግንባታው እንደሚካሄድ ለሪፖርተር አክለው ገልጿል፡፡

ነገር ግን ታሪካዊ ነው ስለተባሉት ሁለቱ የድንጋይ ቤቶች መፍረስ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኔ ይኼ ሕንፃ ይፈርሳል ወይም አይፈርስም አልልም፡፡ ቅርስ የሚሆኑ ሕንፃዎች ታፈርሳላችሁ ለሚባለው ጥያቄ ግን ከፓርላማው በላይ ለቅርስ ማን ያስባል?›› በማለት መልሰዋል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ የሚገነባው ሕንፃ ባለአራት ፎቅ በመሆኑ ከዋናው የፓርላማ ሕንፃ ከፍ ያለ ቁመት ስለሚኖረው በዕይታው ተፅዕኖ ማድረጉ እንደማይቀር የሚናገሩ አሉ፡፡ በግንባታው ወቅትም በሚደረገው የቁፋሮ ሥራና የግንባታ ዕቃ በሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች የዋናው ሕንፃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንዳይከሰት ሥጋት እንዳላቸው ሠራተኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሪፖርተር የኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩን አቶ አበባው አያሌውን አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ አበባውን ይፈርሳሉ የተባሉትን የድንጋይ ቤቶች ከአንድ ዓመት በፊት በፓርላማው ጥያቄ መሠረት በአካል ሄደው ማየታቸውንና ፓርላማው ቤቶቹን ማፍረስ እንደሚችል ማረጋገጫ ከባለሥልጣኑ እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ሁለቱ የድንጋይ ቤቶች ነባር ሕንፃዎች መሆናቸውን ቢያስተውሉም ያን ያህል ታሪካዊ ይዘት እንደነበራቸው ማረጋገጫ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በሥፍራው ሄደን ማስተዋል የቻልነው ወይም የተረዳነው ሁለቱን ሕንፃዎች ጣሊያን በወረራው ጊዜ እንደሠራቸው ነው፡፡ እሱም ቢሆን በሰነድ ወይም በቃል ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ አልተገኘም፤›› በማለት አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው የበለጠ ታሪካዊና ምልክታዊ ይዘት ላለው የፓርላማው ዋና አዳራሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ንጉሡ (አፄ ኃይለ ሥላሴ) ከመንገሣቸው በፊት ወደ አውሮፓ ሄደው እንደተመለሱ ፓርላማውንና ከጎኑ ያለውን የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ማስገንባት አለብን ብለው ፓርላማውን ማስገንባታቸው መረጃ ቢኖርም፣ ሁለቱ የድንጋይ ቤቶች ግን መጀመርያ ከዋናው ሕንፃው በፊት መገንባታቸውን የሚያሳይ ሰነድ አለመገኘቱን ደጋግመው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ቀድሞ የቤተ መንግሥት ጋራዥ ተብሎ ይታወቅ የነበረው ቦታ ላይ፣ ለፓርላማው አዲስ የጉባዔ አዳራሽን ጨምሮ ግዙፍ ሕንፃ ለመገንባት ታቅዶ ነበር፡፡ ሆኖም ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለዓመታት ታጥረው በቆዩ መሬቶች ላይ ዕርምጃ በመውሰዳቸው፣ መሬታቸውን ከተነጠቁት ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንዱ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቦታው በቅርቡ ይፋ የሆነው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል ሆኖ እየለማ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...