የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ማስጀመርያ የጋራ ስብሰባን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የመደመር ዕሳቤን መሠረት ያደረገ የለውጥ ጉዞ በዘንድሮ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ የመደመር ዕሳቤ በሦስት ዋነኛ አገራዊ ዓላማዎች ላይ መመሥረቱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ በአገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ አገሪቱ የያዘችው የለውጥ ጉዞም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተገበረ በሚገኘው የመደመር ዕሳቤ እንደሚጓዝም ገልጸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም በቀጣዮቹ ወራት አደረጃጀቱን ቀይሮ አንድ አገራዊ ፓርቲ ይሆናል እየተባለ ባለበት ወቅትና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል በመደመር ፍልስፍና ይዘትና ምንነት ላይ የጋራ መግባባት ሳይደረስ ፕሬዚዳንቷ የለውጡ ጉዞ በመደመር ዕሳቤ ይመራል ማለታቸው እያስተቻቸው መሆኑን የሚያስቃኘውን የዮሐንስ አንበርብር ዘገባ በገጽ 14 ላይ ይምልከቱ፡፡ በምስሉ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ጋር ይታያሉ፡፡