የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉባዔም ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል
ለኢትዮጵያ ስፖርት ሁለንተናዊ ዕድገት መፍትሔ ይሆናል በሚል በ1990ዎቹ መጀመሪያ የተቋቋመው አገር አቀፉ የኢትዮጵያ ስፖርት ምክር ቤት ስፖርቱ በገጠመው ወጥነት በጎደለው የተጠሪነት ወሰን ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን ተከትሎ ምክር ቤቱን እንደገና ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የስፖርት ምክር ቤቱን መቋቋም አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ የተቋቋመው አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት እንዲቋረጥ ምክንያት የሆነው፣ ስፖርቱ አንዴ ከባህልና ስፖርት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወጣቶችና ስፖርት በሚል ወጥነት በሌለው የመንግሥት የካቢኔ መዋቅራዊ አካሄድን በመከተሉ ነው፡፡
አሁንም የስፖርት ምክር ቤቱን እንደገና ለማቋቋም እንቅስቃሴ የተጀመረው መንግሥት በቅርቡ ባደረገው የካቢኔ አወቃቀር፣ ኮሚሽኑ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት እንዲኖረው በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣን ምክንያት በማድረግ መሆኑ የስፖርት ኮሚሽን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ምክር ቤቱ መጀመሪያ ሲቋቋም ስፖርቱ በኮሚሽን ደረጃ የተዋቀረበት ጊዜ እንደነበር ያከሉት ምንጮች፣ በመሃል ባህልና ስፖርት ተብሎ ሲዋቀር የምክር ቤቱ እንቅስቃሴ ተቋርጦ ቆይቷል ይላሉ፡፡
በመሃልም ከባህልና ስፖርት ተለያይቶ በኮሚሽን ደረጃ ተዋቅሮ የነበረ ቢሆንም የምክር ቤቱ ጉዳይ ተዘንግቶ መቆየቱን ያከሉት ምንጮች፣ ሁለት ጊዜ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሆኖ እንዲዋቀር መደረጉ ስፖርት ምክር ቤቱ እንደገና እንዳይቋቋም ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በአዲሱ የመንግሥት ካቢኔ ስፖርቱ በኮሚሽን ደረጃ እንደገና እንዲዋቀር መደረጉን ተከትሎ በአዋጅ መፍረስ አለመፍረሱ ሳይነገር በስም ብቻ ያለሥራ የቆየውን አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት ለማቋቋም እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ ነው የኮሚሽኑ ምንጮች ለሪፖርተር ያስረዱት፡፡ ምክር ቤቱ የሚቋቋምበት ትክክለኛው ቀን መቼ እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈዴሬሽን ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊያደርገው የነበረውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላልተወሰ ጊዜ ማራዘሙን አስታውቋል፡፡ ጉባዔው እንዲራዘም ምክንያት አድርጎ በመግለጫው ያካተተው፣ ትክክለኛው ቀን ባይገለጽም በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚቋቋም የሚነገርለት የስፖርት ምክር ቤት ከተከናወነ በኋላ ጉባዔውን የሚያደርግበትን ቀን እንደሚያሳውቅ ነው፡፡