የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የ2022 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ እንድታዘጋጅ ሲመርጣት ያልተባለ ነገር የለም፡፡ በርሃማነቷ ዓለም እንደ አይኑ ብሌን ለሚሳሳለት እግር ኳስ “ምቾት አይሰጥም” በሚል ፊፋ ውሳኔውን እንዲያጤን ግፊት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ የእስያ አኅጉር አካል የሆነችው ኳታር በርሃማነቷ ጎን ለጎን ተፈጥሮ ያጎናጸፋት ፀጋ ግን ከሰሞኑ አንቱታን ያተረፈላትን ታሪክ አስመዝግቦላታል፡፡ 17ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በስኬት ማጠናቀቋ የፊፋን ውሳኔ ትክክለኛነት ማሳያ ሆኗል፡፡
የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይኤኤኤፍ) በባለቤትነት በየሁለት አመቱ የሚያሰናዳው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ያዘጋጀችው ኳታር ባለፉት አሥር ተከታታይ ቀናት ያልተጠበቁ አስደናቂ አሸናፊዎችን ብቻ ሳይሆን በተለይ ከኢትዮጵያውያን ውጪ ሆኖ ለሁለት አሥርታት ያህል ርቆ ለቆየው የማራቶን ውጤት ወደ ቤቱ እንዲመለስ ምክንያት ሆኖ ባለፈው እሑድ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በሁለት ወርቅ፣ በአምስት ብርና በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ በኬንያ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ፣ በኳታሩ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበችው የማራቶን ውጤት እ.ኤ.አ በ2001 ኤድመንተን ላይ ገዛኸኝ አበራ ካስመዘገበው የወርቅ ሜዳሊያ በኋላ የተገኘ መሆኑ ውጤቱን ልዩ እንደሚያደርገው እየተነገረ ይገኛል፡፡ በኳታሩ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማጠናቀቂያ ላይ በወንዶች መካከል በተደረገው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የርቀቱ አሸናፊዎች ሌሊሳ ዲሳሳና ሙስነት ገረመው የወርቅና የብር ሜዳሊያ ባለቤቶች የሆኑበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ይህ ውጤቱ ልዩ እንዲሆን በዋናነት ምክንያት የሆነው፣ አትዮጵያውያን አትሌቶች በግል በሚደረጉ የጎዳና ላይ ውድድሮች በውጤታማነታቸው የሚታወቁ ቢሆንም፣ በዓለም አትሌክስ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ግን እንዲህ እንደ አሁኑ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን 18 ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሏቸው መቆየቱ ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያ በሴቶች 10,000 ሜትር በለተሰንበት ግደይ የብር፣ በ5,000 ሜትር ወንዶች በሙክታር እንድሪስና ሰለሞን ባረጋ አማካይነት የወርቅና የብር፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል በለሜቻ ግርማ የብር፣ በ1,500 ሜትር ጉዳፋይአፍ ጸይዬ የነሐስና በ10,000 ሜትር ወንዶች ኦሪገን በናይኪ አካዴሚ እየሠለጠነ በሚገኘው ዮሚፍ ቀጀልቻ የብር ሜዳሊያዎች መመዝገባቸው፣ ኢትዮጵያ በደረጃ ሰንጠረዡ ከተካተቱት አገሮች ተርታ እንድትጠቀስ ያስቻሉ ሆነዋል፡፡
በዘይት ሀብቷ የበለፀገችው ኳታር ከተፈጥሮ ጋር ታግላ ባሳናዳችው በዚህ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ አስገራሚና አስደናቂ ገጠመኞች ሲስተናገዱ ታይቷል፡፡ ከገጠመኞቹ መካከል በመክፈቻ በሴቶች መካከል በተደረገው የማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ ለአሸናፊነት ትልቅ ግምት የተሰጣቸው ብዙዎቹ እንስቶች ሩጫው ተጀምሮ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ብቻ ሮጠው ማቋረጣቸው የውድድሩ ባለቤት አይኤኤኤፍን ጨምሮ በርካቶችን ያስደነገጠ መሆኑ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያን የወከሉት ሦስቱም ማቋረጣቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶቹ ለሦስት ወራትና ማናቸውንም ውድድር እንዳያደርጉ ክልከላ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ከዓለም ሻምፒዮናው ከፍ ብሎ ከ200 በላይ አገሮች በተለያዩ የውድድር አይነቶች የሚሳተፉበት ኦሊምፒክ ደግሞ ከዘጠኝ ወር በኋላ በጃፓን ቶኪዮ በሚመጣው ክረምት እንደሚካሔድ ይጠበቃል፡፡ የ2020 ኦሊምፒክ አስተናጋጇ ቶኪዮ ከኳታር ያልተናነሰ ሞቃታማ የአየር ፀባይ እንደሚኖራት ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ሁሉ በኦሊምፒክም የሚኖራት ተሳትፎ ከአትሌቲክሱ የዘለለ እንደማይሆን የሚናገሩ የዘርፉ ሙያተኞች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈዴሬሽንም ሆነ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይመክራሉ፡፡