Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሙዚቃ ቀማሪው ኤልያስ መልካ (1970 – 2012)

ሙዚቃ ቀማሪው ኤልያስ መልካ (1970 – 2012)

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሙዚቃው ዘርፍ ለትውልድ የሚተላለፉ በርካታ ሥራዎችን ከሠሩ ባለሙዎችም ከቀዳሚዎቹ የሚመደብና ዝናን ያተረፈ ነው፡፡ የሙዚቃ ቅንብርን፣ ግጥምንና ዜማን በአንድ ላይ አጣምሮ መሥራት መቻሉ በኢትዮጵያ ከሙዚቃ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ ተዋናዮች ያሠልፈዋል፡፡ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዲያብብ እንደ መሐመድ አማን ብሎም ሙሉጌታ አባተ ዕውቀቱን ሰጥቷል፡፡

ለሁለት አሠርታት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሁለንተና የነበረው፣ ሕይወቱን በሙሉ ለሙዚቃ በመስጠት ሙዚቃን የናኘው፣ ተወዳጁ ሙዚቀኛ፣ ገጣሚና አቀናባሪ ኤልያስ መልካ፣ በአዲስ አበባ ሰባተኛ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ ከአባቱ ከአቶ መልካ ገረሱና ከእናቱ ከወ/ሮ አፀደ ፈለቀ በ1970 ዓ.ም. ነበር የተወለደው፡፡

የሕይወት ጥሪው ሙዚቃ እንደሆነ የታወቀለት ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ በልጅነት ጨዋታዎቹ ሁሉ ሙዚቃዊነታቸው ወደሚያደሉ ክንውኖች ያዘነብል እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ የልጅነት የሙዚቃ ፍላጎቱና የሕይወት ጥሪው መስመር እንዲይዝ፣ ወላጆቹ አባል የሆኑበት የገነት ቤተ ክርስቲያን የኅብረ ዝማሬ ቡድንና በቤታቸው ይደረግ የነበረው የፀሎት ፕሮግራም መሠረት ጥለውታል፡፡

በገነት ቤተ ክርስቲያን ኅብረ ዝማሬ ቡድን ውስጥ፣ ጊታሪስት የነበረውን ክፍሉ ወልዴን ከመድረኩ ሥር ሆኖ በአትኩሮት መመልከት፣ ኤልያስን በየዕለቱ የሚያስደስተው ተግባር እንደነበር ቤተሰቦቹ ያስታውሳሉ፡፡ በፀሎት ሥነ ሥርዓት ጊዜ ሁሉም ፀሎት ሲያደርስ፣ ኤልያስም፣ ‹‹እኔም በጊታር አንተን እንዳመሠግን ዕርዳኝ፤›› በማለት ጣቶቹን ወደ ላይ ይዞ ይፀልይ እንደነበር በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሯል፡፡

ጊታሪስቱ አቶ ክፍሉ ወልዴም፣ የኤልያስ ፍላጎት ምን እንደሆነ ስላወቀ ጊዜ ሰጥቶ የጊታር አጨዋወት አስተማረው፡፡ ኤልያስ ቀድሞውንም ለሙዚቃ የተፈጠረ ስለነበር፣ ከመምህሩ ያገኛትን ዕውቀት ለመረዳትና ለመተግበር ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ እንዲያውም በችሎታው እምነት ስላገኘ የገነት ቤተ ክርስቲያን መዘምራንን እንዲያጅብ ተደረገ፡፡

በቤተ ክርስቲያን መዝሙሮች ቅንብር ኤልያስ እጅግ አድርጎ ያደንቀው የነበረው ጌታያውቃል ግርማይ ሐድጉ፣ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መክፈቱን ኤልያስ ይሰማል፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱም ሄዶ በመመዝገብ የጊታር ትምህርት ይጀምራል፡፡ የኢያሱ ገነቴና የጌታ ያውቃል ግርማይ በዲሲፕሊን የታነፀ የትምህርት አሰጣጥ በሕይወቱ ሙሉ ሲመነዝረው እንደኖረም ይናገር ነበር፡፡

ከሙዚቃው ጎን ለጎን ሲከታተለው በነበረው መደበኛ ትምህርት አሥራ አንደኛ ክፍል ላይ እንደደረሰ፣ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ለመቀበል ስላወጣው ማስታወቂያ ይሰማል፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ በመሄድ የነበረውን የመግቢያ ፈተናዎች በጥሩ ውጤት አልፎ፣ በቼሎ ሜጀርና በፒያኖ ማይነር ተማሪነት ተመድቦ የትምህርት ቤቱ መደበኛ ተማሪ ሆነ፡፡ በፍፁም ትጋት የሙዚቃ ትምህርቱን በመከታተል በትምህርት ቤቱ የሚታወስበትን ‹‹የምሥጉን ተማሪነት ስም›› ማትረፍ ችሏል፡፡ በዚሁ የትምህርት አጋጣሚ የተዋወቃቸው ዮሐንስ ጦና፣ ግሩም መዝሙር፣ ሰላም በድሩን የመሳሰሉ ባለተሰጥኦ የሙዚቃ ተማሪዎች፣ የሙዚቃ ዕይታ አድማሱን እንዳሰፉለት ዘወትር ሳይዘነጋ ያስታውስ ነበር፡፡

በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቆይታው ሌላም ዕድል አጋጥሞታል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሙዚቃ ባንዶች ጋር ከነበረው ልምድ በተለየ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹በኮንኮርድ ክለብ›› የምሽት ሙዚቃ የጀመረበትና ‹‹መዲና ባንድ››ን መቀላቀል የቻለበት ጊዜ ነበር፡፡ ተሰጥኦውን የተረዱለት መምህሮቹ እዝራ አባተና አክሊሉ ዘውዴ በጊዜው ከፍተኛ ስምና ዝና ወደ ነበረውና እነሱ ወዳቋቋሙት ‹‹መዲና ባንድ›› ውስጥ ጊታር እንዲጫወት የጋበዙበት አጋጣሚ ሌላው የጥበብ መንገዱን አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገለትና ተሰጥኦን በይፋ ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ የታዩት የኤልያስ መልካ የሙዚቃ ሕይወት ጉዞዎች በስኬትና በሰው መውደድ የታጀቡ ነበሩ፡፡ ማሕሙድ አህመድ አቋቁሞት በነበረው የ3ኤም ባንድ ውስጥ ጊታሪስት በመሆን በተለያዩ የውጭ አገሮች መድረኮች ላይ ተጫውቷል፡፡ ‹‹ሁሉም ይስማ›› የተባለውን የማሕሙድ አህመድን የ1993 ዓ.ም. አልበም መጠሪያ ላይ በአልበሙ ውስጥ የተካተቱትን የጉራጊኛ ሙዚቃ በማቀናበር የቅንብር ችሎታውን ማሳየት ችሏል፡፡

ኤልያስ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ በአፍሮ ሳውንድ ባንድ ከፍ ያለ አድናቆት ያተረፉባቸውን የሙዚቃ መድረኮች ለብዙዎች ትዝታ በሆነ ብቃት ተወጥቷቸዋል፡፡ የአፍሮ ሳውንድ የሙዚቃ አባላት ሁሉም እጅግ ከፍ ያለ የሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸው ሙዚቀኞች በመሆናቸው የኮፊ ሐውስ የሙዚቃ ምሽቶችን የሚያደምቁ ኮከቦች ነበሩ፡፡ የዚህ ደማቅ ጊዜ ፊታውራሪ ኤልያስ መልካ ነበር፡፡ ኤልያስ ዜማ ላስታስ የሚባል ባንድ በማቋቋምም ትልቅ ሥራም ሠርቷል፡፡

ኤልያስ ከመድረክ ሙዚቃ ራሱን ወደ ስቱዲዮ በመውሰድ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ካደረጉ ባለሙያዎች መካከል ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም. ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከሠራው ‹‹አቡጊዳ›› በተሰኘ አልበም አሥር ሙዚቃዎች ያቀናበረው ኤልያስ መልካ ነበር፡፡

ይህ ከ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ወዲህ አንድ አዲስ ሙዚቃዊ መንገድና ፍልስፍና መፈጠሩን ያበሰረ አልበም ነበር፡፡ ከአሜሪካ በአበጋዙ ክብረ ወርቅ ሺዎታና በሔኖክ ተመስገን እንዲሁም በወቅቱ በገናና ስሙ ይታወቅ ከነበረው ከሙሉጌታ አባተ በሙዚቃው የተለየ አስተሳሰብ ያለው አንድ የ23 ዓመት ወጣት መምጣቱን ማመን ለብዙ የሙዚቃ ባለሙያዎችም ሆነ ለሙዚቃ አፍቃሪ ቀላል አልነበረም፡፡

ሆኖም ይህ የመጀመርያ ስኬታማ ጅማሬ፣ በትዕግስት በቀለ ‹‹ሳቂታው››፣ በይርዳው ጤናው ‹‹ጀንበር››፣ በኃይልዬ ታደሰ ‹‹ሁሌ ሁሌ››፣ በጎሳዩ ተስፋዬና በዓለማየሁ ሒርጶ ‹‹ኢቫንጋዲ›. ፣ በአረጋኸኝ ወራሽ ‹፣በቃ በቃ››፣ በግርማ ገመቹ ‹‹ትመቺኛለሽ››፣ በተሾመ ወልዴ ‹‹አቻዩ መልሴ›› እና ሌሎችን ሥራዎች በመሥራት የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከፍ እንዲል አደረገ፡፡ በስቱዲዮ ካለ እረፍት ውጪውን ሳያይ የሚሠራባቸው ጊዜዎች መጡ፡፡

በሥራዎቹ ብዛት ልክ መርካት ያልቻለው ኤልያስ 1998 ዓ.ም. ላይ ትንሽ ጊዜ ወስዶ የሙዚቃ አካሄዱን ሌላ መስመር ተልሞ፣ አብነት አጎናፍርን፣ ዘሪቱ ከበደን፣ ሚካኤል በላይነህን፣ ሚካያ በኃይሉ፣ ፍቅረ አዲስ ነቅዓ ጥበብ፣ ኢዮብ መኮንን፣ ኃይሌ ሩት፣ ቤሪ፣ ጊቴ አንለይና ሌሎችንም በተለየ ፕሮዳክሽንና በአዳዲስ ተሰጥኦ ይዞ ወጣ፡፡ ይህ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ እረፍት አልባ በሆነ የሌት ተቀን ድካምና እንቅልፍ እስከማጣት ድረስ የሠራባቸውን ጊዜያት ያስታውሳል፡፡

ኤልያስ የእነዚህ አልበሞች ሁለንተና ነበር፡፡ ግጥሙን ጽፎ፣ ዜማውን ደርሶ፣ ሙዚቃውን አቀናብሮ፣ ድምፃውያኑን ለሥልቱ በሚስማማ መልኩ ገርቶ፣ ቀርፆና አዋህዶ፣ መዝፈን ብቻ ሲቀረው፣ ሥራውን አጠናቆ ለሙዚቃ አፍቃሪ ‹‹እንካችሁ›› እስከሚል ድረስ፣ ዕረፍት የሚባል አልነበረውም፡፡

ኤልያስ እነዚህን ሥራዎች በዚህ ድካም እየሠራ ለሙዚቃ አፍቃሪ ቢያቀርብም፣ ለሙዚቀኛውም ሆነ ለኢንዱስትሪ አንዳች ጠብ የሚል ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ሊታየው አለመቻሉን የኤልያስ መልካ የሕይወት ታሪክ የጻፈው የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሠርፀ ፍሬስብሐት አስፍሯል፡፡ በዚህ ጉጉት የሚቸገሩ ጓደኞቹን ሲያይ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች አለመከበር የፈጠረው ችግር ሥር እየሰደደ መምጣቱን ተረዳ፡፡ መላ ሊሆን የሚችል ትልቅ ሐሳብ በማምጣት የሥራ ባልደረቦቹን በማስተባበር ዘመናዊውን የሙዚቃ ግብይት ሥርዓት ለማስተካከል ደፋ ቀና ማለት ጀመረ፡፡ ግን ሐሳቡ ዕውን እንዲሆን መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በ2009 ዓ.ም. ኤልያስ መልካ ለብዙኃን ጥቅም ሊውል የሚችለውን ይህን ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ‹‹የሙዚቃ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር›› ሊቋቋም እንደሚገባ በማመን ከተለያዩ መንግሥታዊ አካላት ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል አደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር አቅሙ እንዲያድግ ወደ ዩኒየንነት እንዲሸጋገር በማሳመን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ጥቅምት 29 ቀን 2009 .ይፋ የሆነው የአውታር መተግበሪያ ብዙ ጥቅሞች ከማስገኘቱም አኳያ ለሙዚቀኞች፣ ለአቀናባሪዎችና ለግጥም ዜማ ደራሲያን ከቅጂ  አደጋ ይታደጋል ተብሎ ታምኖም ነበር፡፡

መተግበሪያው ለብዙ የሙዚቃ ባለሙያዎችም ተስፋ የሰጠ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁን ወቅት በስፋት ከተለመዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ተመሳሳይነት ስላለው በኢንዱስትሪው ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ተጠብቆ ነበር፡፡

መተግበሪያው አንድ አልበም 15 ብር፣  ነጠላ ዜማ ከሆነ ደግሞ በአራት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እንዲሸጥበትም ተደርጎ ነበር የተሠራው፡፡ በአንድሮይድ ስልኮች ላይ የሚሠራው አውታር ከስልክ ቀሪ ሒሳብ ላይ የሚቆረጥ የክፍያ ሥርዓት ተበጅቶለታል፡፡

በአውታር መተግበሪያ ውስጥ ገብተው ሙዚቃን ከሸመቱ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑት ድምፃዊው፣ አቀናባሪው፣ የዜማና የግጥም ደራሲው ሳውንድ ሪከርድ ፕሮውዲሰሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አምስት አካላት የሚገኘውን ገቢ እኩል ይከፋፈላሉ፡፡

ሙዚቃን ለማድመጥ ከሲዲ ማጫወቻ ጋር መታገልን የቀረፈው የአውታር መተግበሪያ፣ ከዚህ ቀደም በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የነበረውን ዙሪያ ጥምጥም የመገበያያ ሥርዓት በዚህ መልኩ በቀልጣፋ አሠራር የሚቀያየር መሆኑም ተነግሮለታል፡፡

ከአውታር መሥራቾቹ የሆነው ኤልያስ መልካ ነሐሴ 2011 . . መገባደጃ ላይ  ከሪፖርተር ጋር በነበረው ቆይታ፣ መተግበሪያው እንደታሰበው ቀላል ባለመሆኑ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን፣  ቀስ በቀስ ወደ ለማስተካከል ጥረት ላይ እንደነበሩ ገልጾ ነበር፡፡

አውታር እየተንገዳገደ ይነሳል የሚል ተስፋ የነበረው ኤልያስ፣ በዚህ መተግበሪያ እስካሁን በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን አስታውሶ ነበር፡፡

ኤልያስ የሙዚቃ ፕሮዳክሽን፣ ቅንብር፣ ግጥም፣ ዜማ፣ የሚደርስበትና የሚዘጋጅበት ጊዜውን ሰውቶ፣ የጥረቱ ውጤት የሆነውን ‹‹አውታር የሙዚቃ መገበያያ›› ሥልት ካስተዋወቀ ከወራት በኋላ፣ የጤንነቱ ሁኔታ በጠንካራ ሰብዕናው ልክ የሚቋቋመው አልሆን አለ፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ ሕክምና በማድረግ ሕክምናው በሰጠው ተስፋ፣ እጅ ሳይሰጥ እስከ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ቤቱን ስቱዲዮው ውስጥ እንዳደረገ ቆየ፡፡ የአካሉ ዝለት የመንፈስ ጥንካሬውን አንዴም ሳይፈታተኑት፣ ፅኑው፣ አይበገሬውነ የሙዚቃ ሁለንተናዋ የነበረው ኤልያስ መስከረም 24 ቀን 2012 ሊነጋጋ ሲል፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እንደ አንድ ክስተት መጥቶ፣ በችኮላ ሠርቶ፣ በችኮላ የተለየው ኤልያስ መልካ፣ ትውልድ የሚመካበት፣ ‹ሙዚቃን በክብሯ ልክ እውነተኛ መንበሯ ላይ ያስቀመጣት›› ወጣት ሙዚቀኛ ነበር ሲል ሰርፀ ይገልጸዋል፡፡ የሙዚቃ ሥራዎቹ የአንድ ትውልድ ሙዚቀኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከእርሱ በፊት የነበሩትንም ሙዚቀኞች በተፅዕኖ ሥር ያደረገ የትውልዱ ድምፅ ነበር፡፡ በሥራዎቹ  ሁሌም እንዲታወስ በሁላችንም ልብ ውስጥ የለኮሰው ‹‹የፍቅር ሻማ››፣ ‹‹የጥበብ ፋኖስ›› ሳይጠፋ አብሮን ይኖራል ሲልም አክሏል፡፡

መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በብሔራዊ ቴአትር የሙያ ባልደረቦቹ፣ ቤተሰቦቹ እንዲሁም ወዳጆቹ በተገኙበት የክብር ስንበት መርሐ ግብር ተካሄዷል፡፡ በስንብቱ ላይ የሙያ አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ንግግር አድርገዋል፡፡ በስሙ መታሰቢያ እንደሚሰየምና ያላለቁ ሥራዎቹም እንደሚለቀቁ ቃል ተገብቷል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም በዕለቱ ጴጥሮስ ወጳውሎስ በሚገኘው የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተፈጽሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...