Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር እምን ላይ ነው?

የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ (ሼመንደፈር) የኢትዮጵያ ምድር ባቡር መነሻ ነው፡፡ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ቀድሞ ፍራንኮ ኢትዮጵያ ይባል የነበረው ተቋሙ የ784 ኪሎ ሜትር ርዝመት መስመር አዲስ አበባን ከጂቢቲ ጋር ያገናኘ ነው፡፡ በድሬዳዋ የምድር ባቡርን መቋቋም ተከትሎ ከተማዋ ዘመናዊ የመንገድ ዝርጋታ፣ ውኃ፣ መብራት፣ ድንገተኛ እሳትና መከላከል አደጋ ጊዜ ማጥፊያ፣ እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴ እንድታገኝ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አገልግሎቱ እንደቀድሞም ባይሆን ከድሬዳዋ እስከ ጂቡቲ ወሰን ድረስ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረድን ያሳለፈው ተቋሙ አሁን ስላለበት ሁናቴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኃላፊውን አቶ አብዱላዚዝ አህመድን ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድሬዳዋና ባቡር ያላቸው ዝምድና ምንድነው?

አቶ አብዱላዚዝ፡- ድሬዳዋና ባቡር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ በሥልጣኔ ቀደምት ያደረጋት ዘመናዊ ሆስፒታል፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ የቤት ለቤት ቧንቧ ውኃ፣ ባንክ ቤት፣ ከተማዋ የመንገድ ዝርጋታ ዘመናዊ መሆኑ፣ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ማተሚያ ቤት፣ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የተውጣጡ ማኅበረሰቦች ይኖሩባት የነበረ ከተማ ነች፡፡ ቀፈራ፣ ከዚራ ዓረቦች የሰየሙት የመንደር ስያሜ ሲሆን፣ ሳቢያን ጣሊያኖች፣ ነምበር ዋን እንግሊዞች፣ ግሪክና አርመኖችን ሁሉ የያዘች ከተማ ነበረች፡፡ ይህ ሁሉ የዓለም ሕዝብ የሚኖርበት የበረሃዋ ንግሥት ከተማ የጀርባ አጥንት የሆነው ባቡር ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ድርጅት ለምን እስከ ጂቡቲ ወሰን ብቻ ይሠራል?

አቶ አብዱላዚዝ፡- የጂቡቲ መንግሥት የቀድሞ የባቡር መንገድ መስመር ወደ ሌላ ልማት ስላዋለው መሥራት የሚቻለው እስከ ወሰኑ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር የነበረው ሚና ምን ነበር?

አቶ አብዱላዚዝ፡- የተለያዩ ከተሞ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ አዳማ፣ አዋሽና ሌሎች የባቡሩ መዳረሻዎች መንደር ነበሩ፡፡ ባቡር በመምጣቱ የንግድና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በመፍጠሩ ከመንደርነት ወደ ከተማነት ሊያድጉ ችለዋል፡፡ 26 ትልልቅ ከተሞች ባቡር በመኖሩ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ሌላው ለድሬዳዋ ሕዝብ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነበር፡፡   

ሪፖርተር፡- ድሬዳዋ አሁን የመቀዛቀዟ ምክንያት የባቡር እንደ ቀድሞ አለመንቀሳቀሱ ነው ይባላል፡፡ ስለባቡር አንዳንድ ሰዎችን ስንጠይቅ ስሜታቸው የሚነካው ለምን ይመስልዎታል?

አቶ አብዱላዚዝ፡- አብዛኛው ከፍተኛ ድርሻ ወስደው የንግዱን እንቅስቃሴ የሚመሩት እናቶች ናቸው፡፡ የግብርና ውጤቶች ከገጠር ወደ ከተማ ይገባሉ፡፡ በቅብብሎሽ እስከ ጂቡቲ ድረስ አትክልትና ፍራፍሬ ይገበያዩ ነበር፡፡ በዚህ ዘርፍ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆኖ ነበር፡፡ ንግድን የሚሠሩትም የሚሸከሙትም፣ ገበሬውም፣ ታክሲዎችም ሁሉም ሰንሰለቱን ጠብቆ ምድር ባቡር ላይ ብዙ ቤተሰብ ሕይወቱን የመሠረተበት ነበር፡፡ የድሬዳዋ ሕዝብ የምድር ባቡር በመቋረጡ ነው ቅሬታ የተሰማው፡፡ የነበረውን ታሪክ ሲያጣ ይቆጨዋል፣ ሌላው ቀርቶ ድምፁን ራሱ መስማቱ ያጓጓዋልና፡፡ ማኅበራዊ ለውጥ ያሳየበት በመሆኑ ሕዝቡ ከፍተኛ ቁጭት አለው፡፡ ባቡር የተቀዛቀዘበት ሌላው ምክንያት አለ፡፡ ከ20 ዓመት በፊት አዲሱ ባቡር ሲመሠረት ነበረው ከፍተኛ ጭነት እንዲያጓጉዝ፣ ፈጣን እንዲሆን በሚል የተሻለ ጥናት እናቀርባለን ተብሎ ከቻይና መንግሥት ጋር ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት አዳዲስ የባቡር መንገድ እስኪዘረጉ ድረስ የቀድሞው የምድር ባቡር በተለያዩ አጋጣሚዎች ፈተናዎች ገጥሞታል፡፡ ለአራት ዓመታት ለሠራተኞች ደመወዝ ከመክፈል በቀር ሥራው በመቋረጡ እንደሁም ለቀድሞ ባቡር ብዙ ትኩረት በመነፈጉ ልምድ በሌላቸው የመንግሥት ድርጅቶች በመመራቱና በሌሎች ምክንያቶች ሊቀዛቀዝ ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ጂቡቲ ባቡር አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ አብዱላዚዝ፡- ከድሬዳዋ እስከ ጂቡቲ ወሰን 350 ኪሎ ሜትር በ150 ብር እናደርጋለን፡፡ እስከ 50 ኪሎ ግራም ዕቃ በነፃ ይወሰዳል፡፡ ባቡሩ በመኖሩ ኅብረተሰቡ የትምህርት የጤና ማኅበራዊ ግንኙነትም እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ባቡሩ ከሕዝብ የመጣ፣ ለሕዝብ የሚያገለግል በመሆኑ ለትርፍ የተቋቋመ አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ዘንድ የማይረሳ ትዝታ፣ ትውስታ በመኖሩ እስካሁንም የሚገለገሉ አሉ፡፡ የባቡሩ እንቅስቃሴ ሲዳከም ሕዝቡም ይደክማል ባቡሩ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲኖረው ሕዝቡ በሞራል ይንቀሳቀሳል፡፡ በተጨማሪም አብዛኛው የድሬዳዋ ቤቶች የተገነቡት በመንግሥት ሳይሆን በምድር ባቡር በመሆኑ ለሕዝቡ ከፍተኛ ትሩፋት ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮ ጂቡቲ ባቡር እስከ መቼ ይሠራል?

አቶ አብዱላዚዝ፡- በኢትዮጵያና በጂቡቲ መካከል ያለው የውል ሰነድ 50 ዓመት እንዲያገለግል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም እስካሁን 37 ዓመታት ሠርቷል፡፡ ያሉትን ቀሪ ዓመታት ውሉ እስከሚያልቅ ድረስ ይወስዳል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የመንግሥታቱ ውሳኔ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ጂቡቲ የሚገኘው የባቡሩ የጥገናና ሌሎች መገልገያ ቦታዎች ወደ ሌላ ኢንዱስትሪ ተቀይረዋል፡፡ የአዲስ አበባም እንደዚያው ነው፡፡ ድሬዳዋ ላይ ብቻ ያለው ነው በመሥራት ላይ የሚገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥገና ተደርጎለት ወደ ቀድሞ ሥራ መግባት አይቻልም?

አቶ አብዱላዚዝ፡- አሁንም እስከ ጂቡቲ ድንበር ይሄዳል፡፡ ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ የሚሄድበት የባቡር ሐዲድ ግማሹ ወላልቋል፡፡ ምድር ባቡር በራሱ በጀት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ወይም በመንግሥት በጀት የሚቀሰቀስ ባለመሆኑ በራሱ ማድረግ ይከብደዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት በጀት ይዞለት ወደ ቀድሞ ሥራ ቢመለስ ሁለተኛ አማራጭ መሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በጉብኝት ወቅት ለማየት እንደቻልነው ከፍተኛ የባቡር ጥገና ክፍሎችና መለዋወጫዎችን ለመታዘብ ችለናል፡፡ የምድር ባቡሩ የጥገና ክፍሎች የዕውቀት ቤት እንደሆነ ለማየት ችለናል፡፡ በእናንተ በኩል የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ አላሰባችሁም?

አቶ አብዱላዚዝ፡- በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እነዚህን የዕውቀት ተቋሞቻችንን እንዲያገኙ ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ጥቂቶች ቢመጡም አብዛኛው አልተሳተፈም፡፡ ከአሁን በኋላ የሚመጡ ካሉም በራችን ክፍት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምድር ባቡር ምን ያህል ሠራተኞች አሉት?

አቶ አብዱላዚዝ፡- 83 ቋሚና 160 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉን፡፡ ጡረታ የወጡ አባቶችን ሁሉ ሰብስበናል፡፡ ምክንያቱም ሙያው እነሱ እጅ ስለሚገኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በሳምንት ምን ያህል ቀን አገልግሎት ይሰጣል? ገቢውስ?

አቶ አብዱላዚዝ፡- በሳምንት ሦስት ጊዜ ደርሶ መልስ እስከ ደወሌ ይሠራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ስምንት መዳረሻዎች አሉት፡፡ ገቢውም ከሠራተኞች ደመወዝ ውጪ ብዙም ትርፋማ አይደለም፡፡ ከመንግሥት ሠራተኞች ትንሹ ተከፋይ እዚህ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ቢሆን ጥሩ ነው ይላሉ?

አቶ አብዱላዚዝ፡- ድሬዳዋ ላይ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ጥገና የሚያካሂዱት እዚህ መጥተው ነው፡፡ ምክንያቱም ምድር ባቡር ላይ ያሉ የጥገና ዕውቀትና መሣሪያዎች ያሉት እዚህ ነው፡፡ ሌላው ከፍተኛ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዓመት 150 እስከ 300 የሚደርሱ የኤክትሪካል ኢንጂነሪንግና በሌሎችም የሙያ ዓይነቶች መጥተው ሥልጠና እየወሰዱ ነው፡፡ ሁሉም የባቡር ዓይነቶች በዚህ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ወጣቶችን በማስተባበር የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ በመጨረሻም ማለት የምፈልገው የዕውቀት ሽግግር ማድረግ አለብን፡፡ የዕውቀት ሽግግር ሲባል ተራ ነገር አይደለም፡፡ በውስጡ ትዕግሥት ፈላጊ መሆን ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሚታየው ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ፍላጎት ዛሬ ወጣቱን ብንጠይቅ ስንት ነው የምትከፍለኝ ነው የሚለው፡፡ እኛ ግን የምንፈልገው ምን ያህል ዕውቀት ነው ማግኘት የምችለው የሚለንን ነው፡፡ በውስጣችን ያለውን እንዴት ነው ማስተላለፍ የምንችለው የሚለው ያሳስበናል፡፡ ሁሉም ሙያተኛ የራሱ የሆነ ዕውቀት ስላለው ዕድሉን ተጠቅመው የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ነው፡፡ የምድር ባቡር ከሥራም ባሻገር የምዕት ዓመት ታሪክ ያለው በመሆኑ መጎብኘትና መታደስ ያለበት ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...