ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት መጋቢት 2010 ዓ.ም. አንስቶ እስካሁን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ባደረጓቸው ንግግሮች፣ ይፋዊ ውይይቶችና መሰል ጉዳዮች ላይ ከአንደበታቸው ተለይቶ የማያውቅ ነገር ቢኖር “መደመር” የሚለው ቃል ነው፡፡
“ኢትዮጵያውያን ያላቸው ምርጫ ሁለት ነው፤ መደመር ወይም መበተን ነው፤ እኛ መደመርን እንመርጣለን፤” ከሚለው ቅድመ ሥልጣን ንግግራቸው አንስቶ፣ በኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ዘንድ የሚታወቀው ይኸው ቃል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ በኋላም በስፋት ከአንደበታቸው የማይነጥሉት ቃል መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህም አልፎ አገሪቱ የምትመራበት ፍልስፍናና አገር እያስተዳደረ የሚገኘውና በቅርቡም ውህደት በመፈጸም መጠሪያ ስያሜውን ይቀይራል የተባለው ኢሕአዴግ ቀጣይ የፖለቲካ ፕሮግራም እንደሚሆንም ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ “መደመር” የሚለው ቃል፣ ከቃልነቱ ባለፈ አገር የመምራት ፍልስፍናውና ይዘቱ ምን እንደሆነ እንኳን በኢትዮጵያ፣ አገር የማስተዳደር ኃላፊነት በተሰጠው በገዢ ፓርቲው ኢሕአዴግ መሥራች አባል ፓርቲዎች ዘንድም በቅጡ አይታወቅም፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በቀጣዮቹ ወራት አደረጃጀቱን ቀይሮ አንድ አገራዊ ፓርቲ ከሆነ በኋላ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለሙን ጥሎ አዲስ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ይሆናል የተባለው የመደመር ፍልስፍና ይዘትና ምንነትን ለገዢው ፓርቲ መሥራች አባላት ለማስተዋወቅ የተለያዩ መድረኮች በክልሎች እየተዘጋጁና ገና ውይይቶች እየተካሄዱበት ይገኛል፡፡
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነገቡት የመደመር ፍልስፍና መንግሥት በመሠረተውና እርሳቸው በሚመሩት ኢሕአዴግ ዘንድ በጥልቀት ሳይታወቅ፣ መግባባት ሳይደረስበትና የገዥውን ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ገና ሳይተካ፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ማስጀመሪያ የጋራ ስብሰባን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የመደመር ዕሳቤን መሠረት ያደረገ የለውጥ ጉዞ በዘንድሮው ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸው ለትችት ዳርጓቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ ሥርዓትና በኢኮኖሚ ዘርፍ የነበረውን አገራዊ ጉድለት ማስተካከል የተጀመረበት ወቅት እንደነበር አንስተዋል፡፡ ይሁንና ጉድለቱ በተሟላ የተቃኘበት ደረጃ ላይ ገና አለመደረሱን፣ አንዳንዶቹም በባህሪያቸው መዋቅራዊ በመሆናቸው ከአንድ ዓመት አለፍ የሚል ምክንያታዊ ጊዜን የሚጠይቁ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡
“በ2012 ዓ.ም. የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል። እንደሚታወቀው የለውጡ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የመደመርን ዕሳቤ መሠረት አድርጎ የሚጓዝ ነው፤” በማለትም ለውጡ የሚመራበት መርህ መደመር እንደሆነ እውቅና ሰጥተዋል፡፡
ይህ የፕሬዝዳንቷ ንግግር ትችት ያስከተለበት ምክንያትም፣ የመደመር ፍልስፍናን በተመለከተ በገዥው ፓርቲም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚወክሉት ኦዴፓ ውስጥ ስምምነት የተደረሰበት የጠራ አቋም ሳይኖር፣ የአገሪቱ የለውጥ ጉዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸው ባፈለቁት የመደመር ፍልስፍና እንደሚመራ እውቅና መስጠት ተገቢ አይደለም በሚል ነው፡፡ ይኸው ትችት በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች እየተንፀባረቀ ይገኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ፕሬዚዳንቷ ይህንን ያልጠራና ገና በገዥው ፓርቲ አባላት መካከል እያጨቃጨቀ ያለ ጉዳይ ሳያነሱ ንግግራቸውን ቢያደርጉ ተሻለ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
አመክንዮዋቸውን ሲያስረዱም በኢትዮጵያ አገር የመምራት መንግሥታዊ ሥልጣን የሚመሠረትበትን ሕገ መንግሥታዊ መርህ ይጠቅሳሉ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥት የመመሥረት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን መሠረት በማድረግ የመንግሥት ኃላፊነትን የሰጠው በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር ላለው ለኢሕአዴግ መሆኑና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመረጠው ግለሰብም የመንግሥት ሥልጣንን የተረከበው ፓርቲ ፕሮግራሞች አስፈጻሚ እንደሚሆን የሚጠቅሱት የፖለቲካ ተንታኙ፣ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ አግባብ መንግሥት የመሠረተው ገዥው ፓርቲ (ኢሕአዴግ) ስለመደመር ፍልስፍና ተወያይቶ አቋም ባልያዘበት ወቅት የለውጥ ጉዞው የሚመራው በዚህ ፍልስፍና ነው ማለታቸው መርህን የሚጥስ፣ ገለልተኝነታቸው ላይም ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የመደመር ፍልስፍና ምሰሶዎችን በተመለከተ ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው ያስቀጧቸው ነጥቦች መንግሥት ቢከተላቸውና ቢፈጽማቸው ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ስለመሆናቸው አጠራጣሪ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባደረጉት ንግግር የመደመር ዕሳቤ በሦስት ዋነኛ አገራዊ ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም፣ በአገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በአገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት የሚለውን የመደመር ፍልስፍና ቀዳሚ ምሰሶን በተመለከተም የሚከተለውን ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ዛሬ አልተጀመረችም፣ የሺሕ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ናት። በዚህች አገር ታሪክ ውስጥ ያከማቸናቸውና ለዛሬና ለነገ ሊጠቅሙን የሚችሉ መነሻ ሀብቶች አሉን። ካከማቸናቸው ሀብቶችና ፀጋዎች መካከል ነፃነትን አስከብረን መኖራችን፣ የረዥም ዘመናት የታሪክና የቅርስ ሀብቶችን ማከማቸታችን፣ እርስ በርስ የተቆራኘ ኅብረ ብሔራዊነትን መፍጠራችን፣ በውጭ ግንኙነት መስክ ያዳበርነውን ተሰሚነት፣ በአፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ዘንድ ያለን የነፃነት አጋርነት ታሪካችን፣ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የገነባናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ያስመዘገብነው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እያዳበርነው የመጣነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ወዘተ. መጥቀስ ይቻላል። እነዚህን ሀብቶቻችንን አካብተን ለዛሬና ለነገ ብልጽግናችን በመጠቀም የጀመርነውን ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፤” ብለዋል።
“ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረም” የተሰኘው የመደመር ፍልስፍናው ሁለተኛ ምሰሶን በተመለከተም ፕሬዚዳንቷ የሚከተለውን ብለዋል፡፡ “ያለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎቻችን መልካም ፀጋዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስህተቶችም አሉት። እኩልነትን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን፣ አካታችነትን፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን፣ የፍትሕ ሥርዓት መዛነፍን በተመለከተ የተፈጸሙ ስህተቶች አሉ። በቅርቡ ታሪካችን እንኳን ልዩነቶቻችን ላይ የሠራነውን ያህል አንድነታችን ላይ አልሠራንም፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በሚገባው ልክ አላረጋገጠም፣ በሰብዓዊ መብት አያያዛችንና በፖለቲካዊ መብቶቻችን ላይ ሰፊ ጉድለቶች ተመዝግበዋል። እነዚህ የተወዘፉ ዕዳዎቻችን ናቸው። ውዝፍ ስህተቶቻችንን ያለ ምሕረት ማረም ይኖርብናል፤” በማለት በመደመር ፍልስፍናው ሁለተኛ ምሰሶ ትኩረት እንደሚደረግበት አስገንዘበዋል።
የመደመር ፍልስፍናው ሦስተኛ ምሰሶ ደግሞ የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት ላይ እንደሚያጠነጥን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን መልካም ሥራዎች ይዞ፣ ያጋጠሙ ውዝፍ ዕዳዎችን አርሞ በመጓዝ የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና መጪውን ሁኔታ ብሩህ በማድረግ ኢትዮጵያ በርግጥም የሕዝቦቿ በተለይም የወጣቶቿ አገር እንድትሆን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
“አገር በትውልዶች ቅብብሎሽ የምትገነባ በመሆኗ፣ እኛ በትናንቶቹ መሠረት ላይ እንደቆምነው ሁሉ እኛም ለቀጣዩ ትውልድ ከእኛ የተሻለ ሥራ ሠርተን ማስረከብ አለብን። ነገ ከዛሬ የተሻለ መሆን አለበትና፤” ብለዋል። የእነዚህ ዓላማዎች ዋነኛው ማጠንጠኛም ሦስት ግቦችን ለማሳካት እንደሚያስችል፣ እነዚህም ግቦች የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሕዝቦችን ክብር ከፍ ማድረግና ብልጽግናን ማምጣት እንደሆኑ ተናግረዋል።
“በዘንድሮው ዓመት የሚተገበሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻ ሁሉ ቅኝቶቻቸው፣ ዓላማዎቻቸውና የአገር ክብር፣ ግቦቻቸውም የመደመር ግቦች መሆን ይጠበቅባቸዋል፤” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ የሚከናወኑት ተግባራት ሁሉ በእነዚህ ዓላማዎችና ግቦች ላይ የሚያጠነጥኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ግቦቹን ለማሳካት ያላቸውን ድርሻ መገምገም ይኖርብናል ሲሉ ለምክር ቤቶቹ አሳስበዋል።
ከላይ የተጠቀሱትን እሴቶች፣ ዓላማዎችና ግቦች መሠረት በማድረግ መንግሥት በ2012 ዓ.ም. ትኩረት አድርጎ ሊከውናቸው ይገባል ካሏቸው ተግባራት መካከል በቀዳሚነት ያነሱት የአገሪቱ ሰላምና የዜጎች ደኅንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ከመጣው ለውጡ ዋዜማ ጀምሮ አገሪቱን ወጥረው ከያዟት ችግሮች መካከል አንዱ የውስጣዊ መረጋጋት እጦትና በየቦታው የሚከሰቱ የተለያየ ይዘት ያላቸው ግጭቶች መፈጠርና በዚህም ሳቢያ የተከሰተው የውስጥ መፈናቀል በአገሪቱ ታሪክ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ መሆኑን በማስታወስ፣ መሰል ክስተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ መፍትሔ አምጪ ሥራዎች ዘንድሮ እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡
የደኅንነት ተቋማት ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ቀድመው የማነፍነፍ አቅማቸው እንዲያድግና ችግር ሲከሰትም በአጭር ጊዜ የማስቆም ብቃታቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራትን ማከናወን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የዘንድሮ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ፌዴራል ፖሊስ ብቁ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ጥናት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገርና በሒደቱም በአጭር ጊዜ በጠንካራ ዶክትሪን የሚመራ ጠንካራ የፌዴራል ፖሊስ ኃይል እንደሚገነባ ጠቁመዋል፡፡ የክልል ፖሊሶችም አቅማቸውን እንዲያጠናከሩ እንደሚደረግና የመከላከያ ሠራዊቱም በሙያ አቅሙ የላቀ ለማድረግ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናረዋል፡፡ በአጠቃላይ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን የሕጋዊ ማዕቀፎችና አቅሞችን በማዳበርና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ አሁን ያለውን አንፃራዊ ሠላም ወደ አስተማማኝ ሠላም ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸው፣ በቀጣይ በአገሪቱ የሚከናወነው አገራዊ ምርጫና ሌሎች ክስተቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር አስረድተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በእርጋታው፣ በአርቆ አስተዋይነቱና ስንዴውን ከእንክርዳዱ በመለየት ብቃቱ ነው፡፡ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ይመዝናል፣ ከዕለት አልፎ ዘላቂውን አርቆ ያስባል፣ የሚሰማውንና የሚያየውን እየመዘነ ምርቱን ከገለባ ይለያል፡፡ ይህንን ታላቅ ሕዝብ እዚህም እዚያም የሚወረወሩ አሉባልታዎች ሊፈትኑት አይገባም፤” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ “የሐሰት መረጃዎችን ሳይመዝኑ መነሳትና ግብታዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ የዚህ ታላቅ ሕዝብ መገለጫዎች እንዳይሆኑ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፤” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ መንግሥትም የሕግ የበላይነትን ከማክበርና ከማስከበር ጎን ለጎን የመረጃ ተደራሽነት እንዲሰፋ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራና ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ለሚሠሩ ጋዜጠኞችም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብሎም ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትም እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
ፖለቲካዊ መብቶችንና ተሳትፎን አስመልክቶ አገሪቱ ልትከተለው የሚገባ መንገድ በመግባባት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ ያተኮረና የአገርን አንድነት በሚያጠናክሩ እሴቶች የተቃኘ እንደሚሆን ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው የጠቀሱ ሲሆን፣ መንግሥትም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በሕግ፣ በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በሥርዓት ቀረጻ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የጠላትነትና የቡድን ፍረጃ አካሄዶች ቀርተው የመግባባት ፖለቲካ እንዲሰፍን፣ የመነጠልና የመለያየት አካሄዶች ታርመው የትብብርና የአንድነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት ጎልቶ እንዲወጣ እንደሚያበረታታም አመልክተዋል፡፡
በዚህ ዓመት የሚከናወነው አገራዊ ምርጫ ሦስት እሴቶችን መሠረት አድርጎ እንዲፈጸምም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሠራና ምርጫው መሠረት የሚያደርግባቸው ሦስት እሴቶችም፣ ባለፉት ምርጫዎች ያጋጠሙ ግድፈቶች ማረም፣ ነፃ፣ ዴሞክራያዊ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው ማድረግና የፖለቲካ ልሂቃንንና የምልዐተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
ከአገራዊ ምርጫው ባሻገር የሚከናወነው የሕዝበ ውሳኔ ሒደትም፣ ምርጫውን በተመለከተ በተቀመጡት መሠረት እንደሚከናወን በሁለቱም ክንውኖች ወቅትም መንግሥት ላይ የተጣለው ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ተግባር በዚያው ልክ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን በተመለከተ የዚህ ዓመት ትኩረት የሚሆነው የፍርድ ቤት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግና ባለፉት ዓመታት እንዲሻሻሉ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ሕጎችን ማሻሻል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የፍርድ ቤት ማሻሻያዎችን ለማከናወን የሦስት ዓመታት መርሐ ግብር ተቀርጾ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑንና በዚህም መሠረት በሦስት ዘርፎች የሚከናወን የፌዴራል ፍርድ ቤቶችና የዳኝነት ማሻሻያ ዕቅድ እንደተቀረጸ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ በማሻሻያውም የዳኝነት ነፃነትን፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነት እንደሚጠናከር፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ማስፋትና የሕግ ዕውቀት እንዲዳብር እንደሚደረግ፣ እንዲሁም የዳኝነትን ውጤታማነትና ቅልጥፍና እንዲሻሻል ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። የዳኝነት ነፃነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥም የዳኝነት አስተዳደር ዓዋጅ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም እንዲያጎለብቱ እንደሚሠራ፣ የፌዴራል ዳኞች የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ደንብ እንደሚወጣ፣ በተጨማሪም ለዳኞች አመቺ የሥራ ሁኔታ እንዲመቻች አስፈላጊ ዕርምጃዎችን እንደሚወሰዱ ገልጸዋል፡፡ ውጤታማና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር በተያዘው ዕቅድ ደግሞ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አደረጃጀትና ሥልጣን የሚወስኑ አዋጆችን ለማሻሻል የተጀመረውን ሥራ ማጠናቀቅ፣ የአዋጁን ማሻሻያ ተከትሎ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን የተሻለ ለማድረግ አስፈላጊ አደረጃጀትን የመዘርጋትና ደንቦቹን ማውጣት ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚያቀርበውን ከፍተኛ የአገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል፣ በዓመት እስከ 250,000 መዛግብት ለማስተናገድ የሚያስችል አወቃቀር እንደሚፈጠር፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መምሪያ፣ የቁጥጥርና ክትትል ክፍሎችን በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋምና የማደራጀት ሥራ እንደሚተገበርም ጠቁመዋል፡፡ አዲስ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግን፣ አዲስ የንግድ ሕግንና አዲስ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግን አፀድቆ ሥራ ላይ ማዋል በዚህ ዓመት በፍትሕ ሥርዓቱ ከሚተገበሩ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ትኩረት የሚሰጣቸው እንደሆኑ አመልተዋል፡፡
ኢኮኖሚውን በተመለከተው ንግግር ደግሞ መሠረታዊ ዓላማው የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት መጠበቅ፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግና ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠርን ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካትም የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ እነዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማስተካከል፣ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን ማሻሻልና የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙ ትኩረት የሚሰጠው የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ማሻሻል፣ የኃይል አቅርቦትን፣ የቴሌኮም ዘርፍን ማሻሻልንና የሎጅስቲክስ ሥርዓትን ማቀላጠፍን እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ትኩረት ደግሞ የግብርና ምርታማነትን፣ የአምራች ዘርፉንና የቱሪዝም ዘርፍን ለማሻሻል እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ሀብት ግኝትን ማስፋትና የአገልግሎት ዘርፉን ማቀላጠፍ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የተመረጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይንም በሙሉ ወደ ግል የማዘዋወር እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን የመተግበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ የቴሌኮም ሴክተር እንዲሁም በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኙ የተወሰኑ ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት በከፊል ወይንም በሙሉ ወደ ግል እንደሚዛወሩ ገልጸዋል፡፡
ሌላው በ2012 በጀት ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ የሕገወጥ ንግድን መልክ የማስያዝ ሥራ እንደሆነ፣ በዚህ ረገድ ተጠባቂ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመፈጸም አቅም በማሳደግ ኮንትሮባንድ፣ ታክስ ማጭበርበርንና ታክስ መሰወርን፣ እንዲሁም በህቡዕ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት በማምጣት ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ጤንነት የማሸጋገር የተቀናጀ ሥራ የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አገራዊ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትና በዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ድሬዳዋ ላይ ለማቋቋም ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ሽርክና (Joint venture) በመፈራረም ሥራውን በቅርቡ ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑ በኢኮኖሚ ዘርፍ ይከናወናሉ ካሏቸው መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡