Thursday, July 25, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ደወለላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ወደ ቢሮ ለመሄድ መኪናቸው ውስጥ ገቡ]

 • አንተ?
 • እ…
 • አንተን እኮ ነው?
 • ማን ነው?
 • ጭራሽ?
 • እ…
 • በጠዋቱ ተኝተሃል እንዴ?
 • ምን ላድርግ?
 • ሰውዬ?
 • ውይ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የት አድረህ ነው?
 • እርስዎ መሆንዎትን እኮ አላወቅኩም፡፡
 • የት አድረህ ነው አሁን የምትተኛው?
 • መቼ ቤት አለን ብለው ነው?
 • ምንድን ነው ደግሞ የሚሸተኝ?
 • ምን ሸተትዎት?
 • መኪናዬን መጠጥ ቤት አድርገኸዋል ልበል?
 • እ…
 • አፍህ ራሱ ጋን ጋን ነው የሚለው፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በቃ እምቢ  አልክ አይደል?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼን መጠጥ ነዋ፡፡
 • እናንተም እምቢ አላችኋ፡፡
 • ምንድነው እምቢ ያልነው?
 • ፖለቲካውን ነዋ፡፡
 • ምን?
 • በቃ በየጊዜው የሚያቃጥል ነገር ነው የምትነግሩን፡፡
 • እ…
 • ስታቃጥሉን እኛም ሁሉን ነገር ለመርሳት ራሳችንን እናቃጥላለን፡፡
 • የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል አሉ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለአንተ ስካርም ተጠያቂው መንግሥት ነው?
 • ምን ጥያቄ አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ማለት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በነጋ በጠባው ፖለቲከኞቻችን የሚነግሩን ነገር የሚያበሳጭ እንጂ የሚያስደስት አይደለም፡፡
 • ምን ይጠበስ ታዲያ?
 • ስለዚህ እኛም ተስፋ እየቆረጥን ማታ ማታ እየደበንን እንገባለን፡፡
 • ለማንኛውም የዲሲፒሊን ዕርምጃ እወስድብሃለሁ፡፡
 • ሊቀጡኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ደመወዝህን ነው የምቆርጥልህ፡፡
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • አሁን ለእኔ ደመወዝ ይጨመራል እንጂ ይቀነሳል?
 • እሱን እንተያያለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ወድጄ አይደለም እኮ የምጠጣው እያልኩዎት ነው፡፡
 • ምንድነው የምትቀባጥረው?
 • መንግሥት በየጊዜው ሲያቃጥለኝ በመጠጥ ካልረሳሁት እኮ አገር ነው የማቃጥለው፡፡
 • እሱንም ታስባለህ?
 • ባይሆን መንግሥት አንድ ነገር ቢያደርግ ጥሩ ነው፡፡
 • ምን?
 • ያው የእኛ ደመወዝ ከቤት ኪራይና ከቀለብ ስለማይዘል ባቃጠለን ቁጥር ቢያስብልን ጥሩ ነው፡፡
 • ምንድነው የሚያስብልህ?
 • አበል ነዋ፡፡
 • የምን አበል?
 • የመጠጥ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ስልክ ይደውሉላቸዋል]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ደኅንነት አለ ብለህ ነው?
 • ምን ሆኑ ደግሞ?
 • ሁሉን ነገር እያየኸው?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ለውጡ ችግር ውስጥ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ለውጡ ችግር ውስጥ ነው፡፡
 • በሉ ሌላ ሰው እንዳይሰማዎት፡፡
 • ለምን?
 • እኛ ራሳችን የምንጠራጠረውን ለውጥ ሌላው እንዴት
  ይቀበለናል?
 • ታዲያ የተነሳንበት ሐሳብና አሁን ለውጡ ያለበት ሐሳብ የተለያየ ነዋ፡፡
 • ምኑ ነው የተለያየው ክቡር ሚኒስትር?
 • በመጀመርያ አገሪቷ ውስጥ የነበረውን አፈና እናስቆማለን ብለን ነበር፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • በእሱ ፋንታ ግን ሥርዓት አልበኝነት ነው በአገሪቷ የነገሰው፡፡
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
 • እውነቴን እኮ ነው ወዳጄ፡፡
 • ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር፣ ቢያንስ ቀድሞ ከነበረው ሥርዓት የተሻልን ነን፡፡
 • ለሕዝቡ እኮ ቃል የገባነው በርካታ ነገሮች ነበሩ፡፡
 • ታዲያ ሁሉን ነገር በአንድ ጀምበር መፈጸም አንችልም?
 • ሁሉ ነገር ቀርቶብን ጥቂቱንስ መቼ ፈጸምን?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለውጡ እየተቀለበሰ ነው፡፡
 • ያልገባኝ ነገር ከለውጡ ምን ጠብቀው ነበር?
 • በተሻለ መንገድ ሕዝብን እናገለግላለን ብዬ አስቤ ነበራ፡፡
 • እያገለገልን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አገር እየፈራረሰች እያገለገልን ነው ትለኛለህ?
 • እንዳይሸወዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ከእኛ በፊት የነበሩት እኮ  አገሪቷን  ተጫውተውባት ነው የሄዱት፡፡
 • ጥያቄው እኛ ምን እያደረግን ነው የሚለው ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛም የድርሻችንን ይዘን ዞር ማለት ነዋ፡፡
 • በቃ?
 • ምንድነው በቃ ማለት?
 • አገር እኮ ነው የተረከብነው?
 • ለዛ እኮ ነው በአገር አቀፍ ደረጃ እንጠቀም የምንለው፡፡
 • አልገባኝም?
 • መቼም ተረቱን አያውቁትም ብዬ አላስብም፡፡
 • የቱን ተረት?
 • ሲሾም ያልበላ…
 • እንዳትጨርሰው፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን እንደ አንተ የሚያስቡ ሰዎችን ይዘን እንኳን አገር ቤተሰብ መምራት እንችላለን?
 • ስድቡን ያቆዩታ፡፡
 • ስድብ ሲያንስህ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምነው እንደዚህ ተጨነቁ?
 • ለምን አልጨነቅ?
 • ሥልጣኑን የያዝነው እኮ በብቃት እንዳልሆነ እርስዎም ያውቁታል፡፡
 • ታዲያ በምንድነው የያዝነው?
 • ደርሶን  ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው የደረሰን?
 • ተራው!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ቢሮ ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ከቅድም ጀምሮ ተክዘዋል፡፡
 • ምን ላድርግ ብለህ ነው?
 • አዲስ ነገር አለ እንዴ?
 • አይ ሁሉ ነገር ያስጨንቀኛል፡፡
 • ምኑ ነው ያስጨነቅዎት ይንገሩኛ?
 • የአገሪቱ ሁኔታ ነዋ፡፡
 • መጨነቅ ትርፍ አያመጣም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እ…
 • ባይሆን በእጅዎት ያለውን ዕድል ሳይጠቀሙበት እንዳያልፍዎት፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የተቀመጡበትን ወንበር ለመያዝ የከፈሉትን ዋጋ አውቃለሁ፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • የሚፈልጉትን ነገር ሳያደርጉ እንዳያጡት እያልኩዎት ነው፡፡
 • የሰማኸው ነገር አለ እንዴ?
 • ስለምን?
 • ስለወንበሬ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምንም ባልሰማም ሁሉም የሚፈልገው ወንበር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
 • ግን ያው የሚቀመጥበት ሰው እኮ አንድ ነው፡፡
 • እርስዎም የያዙት እኮ ለዛ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ላድርግ?
 • ከበፊቱ ሚኒስትር እኮ መማር ያለብዎት ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የራሱን ወገኖች ይጠቅም ነበራ፡፡
 • እ…
 • እርስዎም እንደዛ ካላደረጉ ቦታው ላይ ላይቆዩ ይችላሉ፡፡
 • ምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ነቃ ይበሉ፡፡
 • እንዴታ?
 • ጊዜ ሳያልፍብዎት እንጠቃቀም፡፡
 • ይኼን ወንበር የያዝኩት እኮ ሕዝብን እንዳገለግልበት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በርካቶች ከኋላዎት የተሠለፉት ያልፍልናል ብለው ነው፡፡
 • ሰው ሳይሠራ እንዴት ያልፍለታል?
 • ስነግርዎት የውድድሩ ሜዳ ከባድ ስለሆነ ሲደግፍዎት የነበሩ ሰዎችን ካልጠቀሙ ለራስዎትም ይስጉ?
 • የሰማኸው ነገር አለ ማለት ነው፡፡
 • አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ የራሴን ድርሻ እየነገርኩዎት ነው፡፡
 • የምን ድርሻ?
 • የእኔን የሥራ ድርሻ ነዋ፡፡
 • እኮ ምንድነው?
 • እርስዎን ማሸጋገር ነው፡፡
 • ከየት ወደ የት ነው የምታሻግረኝ?
 • ከሚኒስትርነት…
 • እ…
 • ወደ ኢንቨስተርነት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ደወለላቸው]

 • ሰላም ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አገር እንዲህ እየታመሰ ምን ሰላም አለ?
 • የቻልነውን እየሠራን ነው እኮ፡፡
 • ኧረ እየሠራን ነው ስንል ሰው እንዳይሰማን፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሪቷ አሁን ያለችበት ሁኔታ እኛ ስንረከባት ከነበረችበት እየባሰባት ነው፡፡
 • ሥራ እየሠራን አይደለም እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የሚጠበቅብንን ያህል እየሠራን አይደለም፡፡
 • እርስዎ ራሱ አላሠራ ብለዋል እኮ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ መጠቀም ያለብንን ያህል እየተጠቀምን አይደለም፡፡
 • እ…
 • ለዓመታት የታገልነው እኮ የተበደልነውን ያህል ለመጠቀም ነው፡፡
 • ምን ይላል ይኼ?
 • ክቡር ሚኒስትር ባለተራ የመሆናችንን መጠን ጥቅማችን እየተጠበቀ አይደለም፡፡
 • ስማ ሥልጣን የያዝነው ሁሉንም ዜጎች ለማገልገል እንጂ የራሳችንን ወገን ለመጥቀም አይደለም፡፡
 • እንደዚህ የሚባል ጨዋታ አይሠራም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ጥቅማችን የሚያስጠብቁ ከሆነ ያስጠብቁ፡፡
 • እያስፈራራኸኝ ነው?
 • እያስጠነቀቅኩዎት ነው፡፡
 • ያለበለዚያስ?
 • ያለበለዚያማ የሚከተልዎትን ያውቃሉ፡፡
 • ምን ልታርጉኝ?
 • ይነሳሉ፡፡
 • ከምን?
 • ከሥልጣን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ። ይህንን ደብዳቤ እየውና በጠየቁት መሠረት እንዲፈጸምላቸው አድርግ። ጉዳዩ ምንድነው? ከአንድ ክልል የቀረበ የትብብርና ድጋፍ ጥያቄ ነው። የምን ትብብር...

[ክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጃቸው ከሆነች አንድ ባለሀብት የተደወለላቸውን ስልክ አንስተው በኮሪደር ልማቱ ላይ የምታቀርበውን ቅሬታ እየሰሙ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እኔ የኮሪደር ልማቱ ላይ ተቃውሞም ሆነ ጥላቻ እንደሌለኝ የሚያውቁ ይመስለኛል? በዚህ እንኳን አትታሚም።  የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር። አውቃለሁ ስልሽ? ለኮሪደር ልማቱ አዋጡ ሲባልም ያለማመንታት አምስት ሚሊዮን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]

ለምንድነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው? ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም። መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስልዎህ ከሆነ ተሳስተሃል። አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር? ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ...