የተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የተመረቀው አንድነት ፓርክ፣ በመደመር እሳቤ ትናንትን መሰብሰብ፣ ዛሬን ማከማቸትና ነገን ማካበት ላይ ተመሥርቶ የተገነባ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንድነት የሚል ስያሜ የተሰጠው ፓርኩ ስድስት መስህቦች ሲኖሩት፣ ከአንዱ በስተቀር አምስቱ ከዓርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለጉብኝት ክፍት ሆኗል፡፡ እነዚህ መስህቦችም የባለ ጥቁር ጎፈር አንበሳ ዋሻ፣ የተለያዩ እንስሳት ማቆያ ቅጥር፣ የዘጠኙ ክልሎች ወኪል እልፍኞች፣ የአገር በቀል ዕፀዋት ማሳያ ሥፍራና የታደሱት የነገሥታት ታሪካዊ ሕንፃዎች ሲሆኑ፣ የእንስሳት ማቆያው ቅጥር ግን እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ ተጠናቅቆ ለጉብኝት ክፍት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሀ መሐመድ (ፎርማጆ) እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዳት ተገኝተዋል፡፡ ጎብኚዎች ፓርኩን ለመጎብኘት ለመደበኛ 200 ብር፣ ለልዩ ጉብኝት (ቪአይፒ) ደግሞ 1,000 ብር መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ሁሉም ዓይነት ክፍያዎች የሚከናወኑት ከወረቀት ገንዘብ ውጪ በኤሌክትሪክ የክፍያ ዘዴዎች ናቸው፡፡