Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየላቁ ሴቶችን የሚሸልመው ኤውብ ለአምስት እንስቶች ዕውቅና ሊሰጥ ነው

የላቁ ሴቶችን የሚሸልመው ኤውብ ለአምስት እንስቶች ዕውቅና ሊሰጥ ነው

ቀን:

የ2012 የላቀች አምባሳደርም 100 ሺሕ ብር ትሸለማለች

በሔለን ተስፋዬ

ኤውብ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የላቀ ሴቶች ሽልማት አምስት እንስቶችን በዕጩነት ያቀረበ ሲሆን፣ ለስምንተኛ ጊዜ በሚያካሂደው ሽልማትም ከአምስቱ አንዷ የ2012 ዓ.ም. የላቀች አምባሳደር (Women of Excellence) የሚል ስያሜ ይሰጣታል፡፡

ለስምንተኛው የላቀ ሴቶች ሽልማት ውድድር ከቀረቡ በርካታ ሴት ዕጩዎች የተመረጡት አምስቱ በጥበብ፣ በማኅበራዊ አገልግሎታቸው፣ በሕክምና እንዲሁም በመድኃኒት አቅርቦት ላይ የሠሩ ናቸው፡፡

አዜብ ወርቁ፣ ቴአትር ተርጓሚ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይ፣ ጋዜጠኛ፣ የሴቶች ሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የአፍሪካ ሬናሳንስ ቴሌቪዥን (ARTS) ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ቤተልሔም ብርሃኔ የእንጦጦ ቤተ አርቲሳን መሥራች፣ ሰላሜነሽ ጽጌ ለጋስ (ዶ/ር) የጎጆ መሥራችና ፕሬዚዳንት፣ ትዕግሥት ዋልተንጉሥ የእርቅ ማዕድ መሥራችና  ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም ዛፍ ወልደ ጻድቅ፣ የዛፍ ፋርማሲዩቲካል ዋና ሥራ አስኪያጅ መታጨታቸውን የኤውብ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ፈለቀች ቢራቱ ነግረውናል፡፡

የላቁ ሴቶች አከባበር ቆራጥና ዓላማ ያላቸው ሴቶች ዕውቅና የመስጠት፣ የማክበርና የማድነቅ ባህልን ለማሳደግ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ መልካም ሥራዎች የሚሠሩ ሴቶችን ለሕዝብ ለማሳወቅ፣ ሴቶችንና ወንዶችን ይበልጥ ለሥራ ለማነሳሳት የተጀመረ በጎ መድረክ መሆኑን ወ/ሮ ፈለቀች አስረድተዋል፡፡

የምርጫ መሥፈርቱ ያለችበትን ቦታና ሙያ ለበጎ ምክንያት የምትጠቀም ሴት፣ ድንቅ ተቋም ወይም ድርጅት ለመገንባት የምትጥር፣ ሌሎች ባለሙያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የምታግዝ፣ ታታሪ ሠራተኛ መሆን ዋነኞቹ ናቸው ያሉት ወ/ሮ ፍፁም ኪዳነ ማርያም፣ ለውጤታማ አስተዳዳሪነት ምሳሌ የሆነችና ሌሎችን ለማገዝ ፍላጎት የምታሳይ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት የምትሳተፍ ሌላኛው ለዕጩነት የሚያበቃ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የላቁ ሴቶች ሽልማት ጥቅምት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ከአሥር ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህም ከአምስቱ ዕጩዎች አንዷ የ2012 የላቁ ሴቶች አምባሳደር የሚል ስም ይሰጣታል፡፡ የ100 ሺህ ብር ሽልማት የምታገኝ ሲሆን፣ ገሚሱን አሊያም ሙሉውን ለዕርዳታ ድርጅት እንድታበረክትም ይጠበቃል፡፡

ኤውብ ኢትዮጵያ ‹‹Association of Women in Boldness›› ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለ53 ሴቶች ዕውቅናና በሙያቸው ለማኅበረሰቡ ላበረከቱት መልካም አገልግሎት ሦስት ሴቶችንና አንድ ተቋምን የሕይወት ዘመን ስኬት ተሸላሚ እንዳደረገችም ይታወቃል፡፡

ኤውብ ሴቶች በራስ ተነሳሽነት አባል በመሆን ውስጣዊ ጥንካሬያቸውን ለማውጣት፣ በሙያቸው እንዲጎለብቱ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የኢትዮጵያ ሴቶች ተገኝተው እንዲወያዩ፣ በጋራ እንዲሠሩና ወደ መሪነት እንዲያድጉ የምታግዝ ተቋም እንደሆነች ተነግሯል፡፡

በ2011 ዓ.ም. በኤውብ ከተሸለሙት አምስት ሴቶች መካከል ወ/ሮ ክብራ ከበደ ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ክብራ በፓርኪንሰን ሕመም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ ለሕመምተኞች የተለያዩ ድጋፎችንና ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የፓርኪንሰን ሕመም ‹‹ምን እንደሆነ እኔ ስለደረሰብኝ አውቃለሁ፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ በኢትዮጵያ ችግሩ እንደበረታ ገልጸዋል፡፡

ኤውብ እንደ ወ/ሮ ክብራና መሰል በጎ የሠሩ፣ በሥራቸው ታታሪ የሆኑ እንስቶች ለኅብረተሰቡ የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለበት ወ/ሮ ፈለቀች ገልጸዋል፡፡

‹‹ኤውብ ከዚህም ባለፈ በሴቶች የተቋቋመች በሴቶች የምትመራ፣ ለሴቶች የምታገለግል ድርጅት ናት›› የሚሉት ፕሬዚዳንቷ፣ በሴቶች ዙሪያ የሚደረጉ ሳምንታዊ፣ ወርኃዊና ዓመታዊ ውይይቶች፣ የተለያዩ ሙያዊ ተሞክሮአቸውን የሚያቀርቡበት መርሐ ግብር እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...