በአዲስ አበባ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚማሩ 300 ሺሕ ያህል ተማሪዎችን ለመመገብ የተዘጋጀው መርሐ ግብር በዚህ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ እንደሚጀመር የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በሳምንቱ የተሠሩ ሥራዎችን በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ ከየዘንድሮው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተጀመረ ሲሆን፣ ከጥቅምት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይተገበራል።
የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራሙ ከዚሁ ቀደም በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በተለያየ መልኩና በተለያዩ አካላት ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ በ2011 በጀት ዓመትም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 51 ሺሕ ያህል ተማሪዎችን እየመገበ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከተለያየ የኑሮ ደረጃ የሚመጡ ተማሪዎችን በተመሳሳይ መልኩ ለማስተናገድ ሲባል ሁሉም ተማሪዎች በተማሪዎች ምገባ እንዲስተናገዱና ተመሳሳይ የደንብ ልብስ እንዲለብሱ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡
በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ ከአሥር ሺሕ በላይ እናቶች ምግብ በማዘጋጀትና በማቅረብ የሥራ ዕድል የሚያገኙ ሲሆን፣ የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ተማሪዎች እናቶችን በማሳተፍ የምግብ አቅርቦቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆንና ትምህርት ቤቶች በሚገኙባቸው ወረዳዎች ላይ የሚገኙ እናቶችም በማኅበር ተደራጅተው የሚሳተፉበት አካሄድ ተመቻችቷል፡፡
ለተማሪዎች ምግብ በማቅረብ ሥራ የሚሳተፉ እናቶች በሚመሠርቱት ወይም በመሠረቱት ማኅበር አማካይነት ከሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር እንዲተሳሰሩ፣ በሚሠሩባቸው ትምህርት ቤቶችም ማብሰያ ቦታ እንዲያገኙ፣ መብራትና ውኃ በነፃ እንዲጠቀሙ እንደሚደረግና ምግብ አቅራቢ ማኅበራትም በሚሰጣቸው የምግብ ዓይነትና ዝርዝር መሠረት ቁርስና ምሳ እንደሚያቀርቡ ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወቃል፡፡