Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአፍሪካዊው ተራድኦ

አፍሪካዊው ተራድኦ

ቀን:

ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት ከሰባት የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች የጦርነት አውድማ ወደ ሆነች አንዲት አፍሪካዊት አገር ጓዛቸውን ሸክፈው ዘመቱ፡፡ በጦርነት የታመሰችው አገር ግን እንግዶቹን ለመቀበል የሚያበቃ አቅም፣ ሕጋዊ የአስተዳደር ሥርዓቷም ተናግቷልና ሰብዓዊ ድጋፎችን የሚያስተባብር የመንግሥት አካል አልነበረም፡፡ ትራንስፖርትን ጨምሮ አብዛኞቹ መሠረተ ልማት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፡፡ የክፉ ቀን ወዳጅ የሆኑትን በጎ ፈቃደኞች ከናይሮቢ በጦርነት ወደ ታመሰችው ሩዋንዳ ኪጋሊ ያደረሳቸው የካናዳ አየር ኃይል ነበር፡፡

‹‹ጦሩም አገሩን አልተረከበውም፡፡ ኤርፖርት ላይ የሚቀበለን የመንግሥት አካል አልነበረም፡፡ አውሮፕላን ላይ የነበረውን ጓዛችንን በመኪና ጭነን ወደ ከተማ ገባን፤›› አሉ ግብረ ኃይሉን እየመሩ በጦርነት ወደ ታመሰችው ሩዋንዳ የዘመቱት / ዳዊት ዘውዴ፡፡

በመቶ ቀናት ውስጥ ብቻ 800 ሺሕ በላይ ሩዋንዳውያን እንደ ቅጠል በረገፉበት በሁለቱ ጎሳዎች ጦርነት ሩዋንዳ የሞት ቀጣና ሆና ነበር ያገኙዋት፡፡ / ዳዊትሩዋንዳን ዕልቂት  ሰምተው የሚያውቋቸውን አስተባብረው ኪጋሊ የገቡት እ.ኤ.አ 1994 ነሐሴ 10 ነበር፡፡ ያረፉት በከተማው በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ ሆቴሉ አሰቃቂ ግደያ የተፈጸመበት አስፈሪ ቦታ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በሰላሙ ጊዜ መዝናኛ የነበረ የመዋኛ ገንዳ በደም የተጨማለቀ፣ ግድግዳና ወለሉ በግፍ የተገደሉ ሰዎች ጣርና ስቃይን የሚያስተጋቡ ዘግናኝ ገፅታ የተላበሰ ነበር፡፡ ከአንዳንድ የሆቴሉ ሠራተኞች በስተቀር ሰው ዝር የማይልበት ቦታ ሆኖ ነበር ያገኙት፡፡ ሥራ የጀመሩትም ሆቴሉን በማፅዳት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በሩዋንዳ እስከዛሬ የማይረሱትን አሰቃቂ ግድያዎች፣ የሰው ልጆች ሰቆቃ ዓይተዋል፡፡ በወቅቱ የኪጋሊ ጎዳናዎች በወዳደቁ አስከሬኖች የተሸፈኑ ነበሩ፡፡ የወዳደቁትን አስከሬኖች እየዘነጠሉ ረሃባቸውን የሚያስታግሱ ውሾች የተበራከቱበት ቀውጢ ወቅት ነበር፡፡ በየመንገዱ የወዳደቁ አስከሬኖችን ማንሳት የሰዎችን ሕይወት ከመታደግ እኩል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶም ያውቃል፡፡ አንድ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትም ከተማውን የማፅዳት፣ አስከሬኖቹን የመቅበርና ውሾቹን የማስወገድ ተግባር ላይ አተኩሮ ይሠራ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በዚያን ጊዜ በርካታ ሩዋንዳውያን ከመኖሪያ ቄዬአቸው ተፈናቅለው ስለነበር የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጎችን መርዳት ነበር የዘማቾቹ ዋና ዓላማ፡፡ ‹‹አፍሪካን ሒውማኒቴሪያን አክሽን›› የተባለ ስያሜ የያዘው ይህ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን / ዳዊትን ጨምሮ ሦስት ሐኪሞችንና ሌሎች የሕክምናና የሥነ ምግብ ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር፡፡ ለዘመቻው ለመሰናዳት በቂ ጊዜ አልነበራቸውምና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሠሩበት የተፈቀደላቸው 268 ሺሕ ዶላርም እንዲሁ በእጃቸው ነበር የተሰጣቸው፡፡

ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሕክምና ዕርዳታ መስጠትን ዓላማው አድርጎ የተነሳው ቡድኑ፣ ‹‹ከተጠበቀው በባሰ ሁኔታ ላይ ነው የደረስነው፡፡ ውሾች ሰዎችን የሚበሉበት አስፈሪ ነገር ነው የገጠመን፤›› ሲሉ / ዳዊት በኪጋሊ የገጠማቸውን ያስታውሳሉ፡፡

በመጀመርያዎቹ ቀናት በየመንገዱ ቆስለው የሚያጣጥሩ ሰዎችን በሕክምና ለመርዳት ሞክረዋል፡፡ በተለይም ‹‹ከኪጋሊ ወደ ኮንጎ የሚወስደው መንገድ ላይ ብዙ ሰዎችን እየተመላለስን የሕክምና ድጋፍ አድርገናል፤›› ይላሉ፡፡ በዚያ ቀውጢ ጊዜ ምን ያህል ሰዎችን እንደረዱ ቁጥሩን በውል አያውቁትም፡፡ መንገድ ላይ ወድቆ የተገኘ እስትንፋሱ እስካለ ድረስ ተረባርበው ማከም ነው፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን ጤና ጣቢያዎችና ክሊኒኮችን አሠርተው መሥራት ቀጠሉ፡፡ ሰብዓዊ ድጋፉን መስጠት በጀመሩ አንድ ዓመት ውስጥ 70 ሺሕ መድረስ ችለዋል፡፡

በታሪክ ከማይዘነጉ አሰቃቂ እልቂቶች ከተፈጸመባቸው ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ሩዋንዳ ታሪኳ ተቀይሯል፡፡ ዶ/ር ዳዊት ግን አሁንም ‹‹ሩዋንዳ ሩዋንዳ›› ይላሉ፡፡ ‹‹ሩዋንዳ የዛሬ 25 ዓመት ገባን፣ አሁንም እዚያው ነን አልወጣንም፤›› የሚሉት የአፍሪካ ሒማኒቴሪያን አክሽን መሥራችና ፕሬዚዳንት / ዳዊት፣ ድርጅቱ በተለያዩ አፍሪካ አገሮች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን እንደቀጠለ፣ በሩዋንዳ በሚገኙ ስደተኞችና ተቀባይ ማኅበረሰቦች ላይ እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡

የሩዋንዳን ዘር ተኮር ፍጅት ተከትሎ ... 1994 ተቋቁሞ ነሐሴ 10 ኪጋሊ የገባው አፍሪካን ሒውማኒቴሪያን አክሽን፣ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን መድረስ እንደቻለ ይነገርለታል፡፡ ድርጅቱ ልማት ብልፅግና በሰላም ዕውን ማድረግ የሚችሉና በሰው ልጅ ደኅንነት ረገድ ሕዝቦቿንና ማኅበረሰቧን ማብቃትና መያዝ የሚችሉ አገር በቀል ተቋማት ያሏትን አፍሪካ የማየት ራዕይ አለው፡፡  

ስደተኞችን፣ ከስደት ተመላሾችን፣ ተፈናቃዮችን እንዲሁም ተቀባይ ማኅበረሰብን በተመለከተ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ግጭት በተከሰተባቸው፣ ሰብዓዊ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ደርሶ ምላሽ የመስጠት ተልዕኮ አለው፡፡ አፍሪካን በሚመለከት ሰብዓዊ ጉዳዮችም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥትና የመሳሰሉት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ያሳውቃል፣ ያማክራልም፡፡

... 1994 ሩዋንዳ ላይ የሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ሌሎች አፍሪካዊ አገሮች መከሰታቸውን ተከትሎ ተደራሽነቱን ሰፊ ማድረግ ችሏል፡፡ ... እስከ 2018 ድረስ በአልጄሪያ፣ በአንጎላ፣ በብሩንዲ፣ በካሜሩን፣ በቻድ፣ በጂቡቲ፣ በዴሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ፣ በኢትዮጵያ፣ በጊኒ፣ በኬንያ፣ በላይቤሪያ፣ በናምቢያ፣ በሴራሊዮን፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ መደበኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመዝግቧል፡፡

በእነዚህ አገሮች ለሚገኙ እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውን የመጀመርያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ያደርጋል፡፡ በቂ ውኃና የፅዳት መገልገያዎች ተደራሽነትን የማረጋገጥ ተግባርም ያከናውናል፡፡ በኤችአይቪ ላይም የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ቀርፆ ይሠራል፡፡ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸውንና ለወንጀሉ ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ ከስደት ተመላሾች የሕክምና ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ይሰጣል፡፡ ‹‹የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት አባል መሆኑ ስደተኞችን፣ ተፈናቃዮችንና ከስደት ተመላሾቸን በተመለከተ በሚሠራው የአድቮኬሲ ሥራ ተሰሚነት አግኝቷል ይባላል፡፡

... 1994 በሩዋንዳ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦችና ስደተኞች መጠለያ ገንብቷል፡፡ ... 1996 የአንጎላን ቀውስ ለመፍታት በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ዘርፍ ብዙ መርሐ ግበር በመተግበር ረገድ ተሳታፊ ነበር፡፡ ከተባበሩ መንግሥታት ድርጅትና ከአንጎላ መንግሥት ጋር የስደተኞች የጤና መርሐ ግብር መተግበር ድርሻው ነበር፡፡

... 1997 በሩዋንዳና አንጎላ ብቻ ተወስኖ የነበረውን ተደራሽነቱን ወደ ብሩንዲ፣ ኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን አሰፋ፡፡ በላይቤሪያ ሆስፒታሎችና የገጠር ጤና ማዕከሎች አስገነባ፡፡ .ኤአ. 1999 በአልጄሪያ የደረሰውን ርዕደ ምድር ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ መርሐ ግብሩ አስፈጻሚ ሆኖ ሠራ፡፡ በኢትዮጵያም 30 የገጠር ቦታዎች የሥነ ተዋልዶና የኤችኤቪ ኤድስ ፕሮጀክቶችን አቋቋመ፡፡ ... 2000 ላይ ከአንጎላ፣ ብሩንዲ፣ ኮንጎና ሩዋንዳ በአንድ ጊዜ በርካታ ስደተኞች ወደ ዛምቢያ በጎረፉበት ወቅት አፍሪካ ሒውማኒቴሪን አክሽን ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በዚህም 27 ሺሕ ዜጎችን እንደደረሰ ታሪኩ ያስረዳል፡፡

በሩዋንዳ የጀመረውድርጅቱሰብዓዊ ድጋፍ ጉዞ እንዲህ እንዲህ እያለ አገልግሎቱን በብዙ የአፍሪካ አገሮች ማድረስ ችሏል፡፡ በተለያዩ በታሪክ በማይዘነጉ የሰብዓዊ ቀውሶች ምላሽ ሲሰጥ ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ጋር አብሮ የሚሠራው ይህ ተቋም፣ ሥራውን የጀመረበትን 25 ዓመት ለማክበር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ መሥራቹ / ዳዊት ተናግረዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...